ፈልግ

(ፋይል) ጥር  27 ፥ 2023  ታይላንድ ፥ ባንኮክ ከተማን ሸፍኖ የነበረው መርዛማ ጭጋግ (ፋይል) ጥር 27 ፥ 2023 ታይላንድ ፥ ባንኮክ ከተማን ሸፍኖ የነበረው መርዛማ ጭጋግ   (AFP or licensors)

የአሲያን አባል ሃገራት ድንበር ተሻጋሪ ጭጋግ ላይ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥሉ አስታወቁ

በክረምቱ ወቅት የሚከሰተውን ከባዱ የድንበር ተሻጋሪ ጭጋግ ስጋት እየጨመረ ባለበት ወቅት አምስት የአሲያን (ASEAN) ‘የደቡብ ምስራቅ ኢስያ ህዝቦች ህብረት’ አባል ሀገራት ነቅተው ለመጠበቅ እና ጭጋጋማውን የአየር ንብረት የመከላከል ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
አስር ሃገራትን ያቀፈው የደቡብ ምስራቅ ኢስያ ህዝቦች ህብረት ዉስጥ አምስቱ ሃገራት በክልሉ በደረቅ ወቅት የድንበር ተሻጋሪ ጭጋጋማውን የአየር ንብረት ለመከላከል የክትትል እና የመከላከል እርምጃዎችን ለማጠናከር ቃል ገብተዋል። ይህን ቁርጠኝነት ያሳዩት ባለፈው ሰኔ 1 2015 ዓ.ም. በ24ኛው የንኡስ ክፍላተ ግዛቶች የሚኒስትሮች አስተባባሪ ኮሚቴ በወሰን ተሻጋሪ ጭጋግ ብክለት ላይ ባደረጉት ስብሰባ ነው።
ይህ በሲንጋፖር በተካሄደው ስብሰባ የብሩኔ ዳሩሳላም ፣ የኢንዶኔዢያ ፣ ማሌዥያ ፣ ሲንጋፖር እና ታይላንድ ተወካዮች ተገኝተዋል። የክልሉ ሃገራት በኤልኒኖ ምክንያት ባጋጠማቸው የደን ቃጠሎ ሳቢያ የተከሰተውን ጭጋግ ለመከላከል ከፍ ያለ ድጋፍ እያደረጉም እንደሆነ ታውቋል።
የኤልኒኖ ስጋት
በስብሰባው ወቅት የ ‘አሲያ ስፔሻላይዝድ የሜቲዎሮሎጂ ማዕከል’ (ASMC) ከ70% እስከ 80% ኤልኒኖ ሊከሰት እንደሚችል እና አዎንታዊ የህንድ ውቅያኖስ ዳይፖል እድልን በመተንበይ በመጪዎቹ ወራት ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ እንደሚኖር ተናግሯል።
እንደ ማዕከሉ ወቅታዊ ትንበያዎች ከሆነ በሚመጣው ነሀሴ ወር የሰሜናዊው አሴን ሃገራት ክልል ሰፊ እና ቀጣይነት ያለው ካፊያማ የዝናብ ሁኔታዎች ሊያጋጥመው እንደሚችል ይጠቁማል። ደቡባዊ ማሪታይም አህጉር ደግሞ ከመደበኛው ሞቅ ያለ የሙቀት መጠን እንደሚከሰት ይጠበቃል ብሏል። በእነዚሁ ደቡባዊ አካባቢዎች የአሸዋ እና የደን ቃጠሎዎች በሚከሰቱበት ጊዜ አከባቢው ላይ ሰፋ ያለ ጭጋግ የሚያስከትል ይሆናል።
እንደ ክልሉ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃ በደቡብ አሴን ክልል ያለው ከፍተኛ ሙቀት እና ጭጋግ እ.አ.አ. ከ 2019 ጀምሮ ከተከሰቱት በላይ በጣም ኃይለኛ የመሆን እድሉ ከፍ ያለ ነው። ማዕከሉ ረዘም ያለው ደረቃማ የአየር ንብረት የሙቀት መጠን መጨመር እና ጭጋጋማውን የአየር ሁኔታ እንደሚያባብስ አስጠንቅቆ ፥ የድንበር ተሻጋሪው ጭጋግ በክልሉ ክፍሎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል በማለት ገልጿል።
በልማት ውስጥ ያሉ ማዕቀፎች
በነዚህ የአየር ንብረት ሁኔታዎች መካከል ፥ አምስቱ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ተፅእኖ ተገንዝበው በንቃት መጠበቅን ፣ የመከላከያ እርምጃዎችን እና የእሳት ማጥፊያ ሂደቶችን ለማሻሻል ጠንካራ እርምጃ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።
ለሁለት ቀናት በተካሄደው ውይይት አገሮቹ የአሴን ስምምነትን በድንበር ተሻጋሪ ጭጋግ ብክለት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ እ.አ.አ ከ2023-2030 ‘ከጭጋግ-ነጻ ፍኖተ ካርታ’ ፣ የአሴን የመሬት አስተዳደር ስትራቴጂ እና ዘላቂ የመሬት አያያዝ የኢንቨስትመንት ማዕቀፍን ለማጠናቀቅ በጉጉት ይጠባበቃሉ።
በኢንዶኔዥያ ‘የደቡብ ምስራቅ ኢስያ ህዝቦች ህብረት’ ለድንበር ተሻጋሪ ጭጋጋማው የአየር ንብረት ብክለት መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስተባባሪ ማዕከል ስለ መቋቋሙም ትኩረት ተሰጥቶታል።
COP 18 ተብሎ የተሰየመው በወሰን ተሻጋሪ ጭጋግ ብክለት ዙርያ የሚወያየው ጉባኤ 18ኛውን ስብሰባ በነሃሴ ወር 2023 በላኦ ከተማ ለማካሄድ ዕቅድ ሲያዝ ፥ በ2024 የሚደረገው 25ኛው ስብሰባ ደግሞ በታይላንድ እንዲካሄድ ተወስኗል።
ተመሳሳይ የሆኑ የአየር ጥራት አመልካቾች
ስብሰባው የድንበር ተሻጋሪ የጭጋግ ብክለት እንዲቀጥል የሚፈቅዱ አንዳንድ ጉዳዮችን የዳሰሰ ቢሆንም ፥ አገራቱ አሁንም የአየር ጥራት አመልካቾችን በቀጣናው ደረጃ የማውጣት እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ገና ያልጀመሩ ይመስላል ተብሏል።
የማላያ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ሄለና ቫርኬ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት “አንድ ወጥ የሆነ የቁጥጥርና የጭጋግ መጠን ሪፖርት ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል። የአካባቢያዊ ፖለቲካ ኤክስፐርት የሆኑት ዶ/ር ቫርኪ እ.አ.አ. ከ2016 እስከ 2020 በክልሉ የተከሰተውን የድንበር ተሻጋሪ ጭጋግ ለመከላከል የተደረገውን የመጀመሪያ የአሴን ፍኖተ ካርታ ውጤት ግምገማ እንዲያካሂዱ በአሴን የተሾመ የባለሙያዎች ቡድን አካል ነበሩ።
“የአሴን ፍኖተ ካርታ ተመልክተህ እንደሆን ፥ ‘የድንበር ተሻጋሪ ጭጋግ አካባቢን መቀነስ’ የመሳሰሉ ጠቋሚዎች አሏቸው ፥ ግን ይህ ምን ማለት ነው? መነሻው ምንድን ነው? ይህ ሁሉ በግልጽ ሊገለጽ ይገባል” ሲሉም ያለውን ብዥታ አመላክተዋል።
የአሴን አባላት በአሁኑ ጊዜ የአየር ጥራት አመልካቾችን በተመለከተ አንድ ወጥ የሆነ ክልል አቀፍ መመሪያዎች የላቸውም። ዶ/ር ቫርኬይ እንደሚሉት ‘በአሁኑ ወቅት እያንዳንዱ አገር የራሱን ዘዴ ይከተላል’ ብለዋል። ታይላንድ የአየር ጥራት መረጃ ጠቋሚን (AQI) ትጠቀማለች ፣ ሲንጋፖር የብክለት ደረጃዎችን (PSI) ትጠቀማለች እንዲሁም ማሌዢያ የአየር ብክለት መረጃ ጠቋሚ አላት።
"እያንዳንዱ ኢንዴክስ ወይም ጠቋሚ ከሁሉም አባል ሃገራት ጋር እኩል ተናቦ መስራት አለበት ፥ እንደዚህ ሲሆን በክልላዊ ደረጃ ጭጋጋማውን የአየር ንብረት በተሻለ ሁኔታ መከታተል ፣ ሪፖርት ማድረግ እና ማረጋገጥ እንችላለን ፥ ችግሩን በደንብ ከተረዳህ ወደ መፍትሄ መሄድ ትችላለህ” ሲሉም ሃሳባቸውን ደምድመዋል።
 

12 June 2023, 13:42