ፈልግ

መንግሥታት ውቅያኖሶችን ከብክለት ለመከላከል ስምምነት ላይ ደረሱ መንግሥታት ውቅያኖሶችን ከብክለት ለመከላከል ስምምነት ላይ ደረሱ  (ANSA)

መንግሥታት ከዓመታት ድርድር በኋላ ውቅያኖሶችን ከብክለት ለመከላከል ስምምነት ላይ ደረሱ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት ከአሥር ዓመታት ድርድር በኋላ ከብሔራዊ የአስተዳደር ክልል ባሻገር የሚገኙ የውቂያኖስ ውስጥ ብዝሃ-ሕይወትን ከጉዳት ለመከላከል እና በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያስችላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ስነድ በማዘጋጀት ስምምነት ተፈራርመዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በባሕር አጠቃቀም ውል ላይ የሚደረጉ ድርድሮች፣ በገንዘብ ወጭ እና በአሳ ማጥመድ መብቶች ላይ በነበረው ልዩነት ምክንያት ለዓመታት ተቋርጠው እንደ ነበር ተነግሯል። ኒውዮርክ በሚገኝ የድርጅቱ ጠቅላይ ጽሕፈት ረጅም ውይይት ከተደረገ በኋላ የስምምነት ሰነድ መፈረሙን የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በደስታ ተቀብለውታል። አዲሱ ስምምነት ከብሔራዊ የአስተዳደር ክልል ባሻገር የሚገኙ የውቂያኖስ ውስጥ ብዝሃ-ሕይወት ጥበቃ እና ዘላቂ ጥቅም ለማረጋገጥ ያለመ እንደሆነ ተነግሯል። ከውቅያኖስ ክፍል ሁለት ሦስተኛውን የሚሸፍነው ስምምነቱ፣ ወደ ሁለት አሥርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ተሰራ ሥራ ፍጻሜ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ስምምነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ታውቋል።

ታሪካዊ ስኬት ነው!

እንደ አካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ገለጻ መሠረት፣ የመጣው ስኬት በውቅያኖስ ላይ የሚደርሱ የዛሬ እና የነገ ውድመቶችን ለመከላከል ሲደረግ የቆየ የዓለም አቀፍ ጥረት ውጤት እንደሆነ ተገልጾ፣ በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን፣ የብዝሃ ሕይወት መጥፋትን እና ብክለትን ለመቅረፍ አስፈላጊ ነው ተብሏል። እንዲሁም ከውቅያኖስ ጋር የተያያዙ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳ ግቦችን እና ውጥኖችን ለማሳካት አስፈላጊ ነው ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አቶ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ ሁሉም ወገኖች ላሳዩት ቁርጠኝነት፣ ፍላጎት እና ጽናት ምስጋና ማቅረባቸውን፣ ጤናማ፣ የበለጠ ጠንካራ እና ምርታማ ውቅያኖስን ለማረጋገጥ፣ የአሁኑን እና የወደፊት ትውልዶችን ለመጥቀም ከሁሉም አካላት ጋር ተባብሮ ለመሥራት ጽኑ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ቃል አቀባያቸው ተናግረዋል። 

06 March 2023, 14:43