ፈልግ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኒውዮርክ የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኒውዮርክ የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ   (ANSA)

ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ አገራት ተስፋቸውን እና እምነታቸውን እንዲያድሱ ጥሪ አቀረቡ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ ድርጅታቸው የተመሠረተበትን 77ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሰኞ ጥቅምት 14/2015 ዓ. ም. ንግግር አድርገዋል። እ. አ. አ በ1945 ዓ. ም. የተመሠረተው ድርጅቱ፣ የሰው ልጅ በአብሮነት ሊያገኘው በሚችለው ነገር ላይ ተስፋውን እንዲያድስ እና እምነትም ሊኖረው ይገባል በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እ. አ. አ. በየዓመቱ የሚውለው ጥቅምት 24 የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር የጸደቀበት ዕለት እንደሆነ ይታወቃል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት የተመሠረተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የጸጥታው ምክር ቤት አምስት ቋሚ አገራትን ጨምሮ በአብዛኞቹ ተፈርሞ በጸደቀው ስምምነት የተመሠረተ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል። ዋና ጸሐፊው አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እ. አ. አ. በ2022 ዓ. ም. መልዕክታቸው፣ ድርጅታቸው የዓለም መንግሥታት የሚሰባሰቡበት፣ በጋራ ችግሮች ላይ ተወያይተው የጋራ መፍትሄዎችን የሚያገኙበት እና ከዓለም አቀፍ ግጭት ወጥተው ወደ ዓለም አቀፍ ትብብር የሚሻገሩበት “የተስፋ ውጤት ነው” ሲሉ ገልጸውታል።  

ድርጅቱ የተፈተነበት ጊዜ ነው!

“ድርጅታችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየተፈተነ ይገኛል” ያሉት አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በእንደዚህ ዓይነት ጊዜያት በመቀራረብ ለችግሮች የጋራ መፍትሄዎችን ለማግኘት መመሥረቱን ገልጸው፣ “የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር እሴቶችን እና መርሆዎችን ዛሬ ከምን ጊዜውም በላይ በሁሉም የዓለም ማዕዘናት በገሃድ ወጥተው እንዲታዩ ማድረግ ይኖርብናል" ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም ደረጃ ያለውን አስፈላጊ ሚናን በማጉላት የገለጹት አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ ለሰላም እና ለሕይወትን ዕድልን በመስጠት የወደፊት እጣ ፈንታን እና ዓለም አቀፍ ዕድገትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ግጭቶችን ማስቆም እንደሆነ አስረድተዋል። በየዓመቱ የሚከበረው የመንግስታቱ ድርጅት ቀን የጋራ አጀንዳዎችን ለማጉላት እና ድርጅቱ ላለፉት 77 ዓመታት ሲመራበት የቆየውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ዓላማ እና መርሆችን ለማረጋገጥ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል።

ድህነትን እና የኑሮ አለመመጣጠንን መቀነስ

አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በማከልም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድህነትን እና የኑሮ አለመመጣጠንን ለመቀነስ እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ከውድቀት በማዳን ላይ ያለውን ሚና አመልክተዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት፣ የቅሪተ አካል ነዳጅን የመጠቀም ልማድ በማስቀረት የታዳሽ ኃይል አብዮት ከማስጀመር በተጨማሪ የጋራ መኖሪያ ምድራችን ከጉዳት ለመጠበቅ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ድርጅቱ ለእናቶች እና ለልጃገረዶች የሚሰጥ የዕድል እና የነፃነት ሚዛንን ለማስተካከል፣ ሰብዓዊ መብቶችን ለሁሉ ሰው ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አብራርተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ቀንን ስናከብር፣ በትብብር ሲሰራ የሰው ልጅ ሊያገኘው የሚችለውን ተስፋ እና እምነት ማደስ የሚቻል መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ በድርጅቱ ምሥረታ 77ኛ ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል።

25 October 2022, 17:07