ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ምስጋና ቀረበላቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ምስጋና ቀረበላቸው  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ስፖርትን ለሰላም ግንባታ በማስተዋወቃቸው ምስጋና ተሰጣቸው

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ቶማስ ባች፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለስፖርት አጽንዖት በመስጠት ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ሰዎችን አንድ ለማድረግ እና ሰላምን ለማምጣት የሚጥሩበትን መንገድ በማድነቅ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ስፖርት ለሁሉም” በሚል መርህ በቫቲካን ውስጥ ከመስከረም 19–20/2015 ዓ. ም ዓለም አቀፍ ስብሰባ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ዓርብ መስከረም 20/2015 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከስብሰባው ተሳታፊዎች ጋር መገናኘታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ለስብሰባው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር ስፖርት በማኅበረሰቦች መካከል ውህደትን ለማጎልበት የሚጫወተውን ሚና በማጉላት የሰላም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ “የስፖርቱ ዓለም አንድነትን እና መተሳሰብን የሚያሳድግ ከሆነ ለሰላም ግንባታም አጋር ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

አንድነት ይሻላል!

ከስብሰባው በኋላ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ክቡር ቶማስ ባች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት መሠረት በማድረግ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባ ስቴፋኒ ስታልሆፈን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ማኅበር ሰላምን ለማስፈን ያላቸውን ፍላጎት እንደሚጋሩ ገልጸው፣ ስፖርት የተለያዩ ባሕሎች እና አገራት ለወዳጅነት ውድድር የሚገናኙበት ቦታ እንደሆነ ጠቁመው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “ከፍተኛ፣ ፈጣን እና ጠንካራ” የሚለውን የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ማኅበር መፈክርን ለቡድኑ አባላት በማስታወስ፣ በቡድን መጫወት እና ተባብሮ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ መናገራቸውንም አስታውሰዋል።

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን አስተያየት በደስታ የተቀበሉት የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ክቡር ቶማስ ባች፣ የሰው ልጅ በሙሉ አንድነቱን ካጠናከረ "ፈጣን፣ ከፍ ያለ እና ጠንካራ" ሊሆን ይችላል ብለዋል። “ፈጣን፣ ከፍተኛ እና ጠንካራ” የሚለው የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ማኅበር መሪ ቃል በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ፈረንሳዊ ዶሚኒካን ካኅን ሄንሪ ዲዶን መሪ ቃል እንደነበር ይታወሳል። ዓለም አቀፍ ማኅበሩ ይህን መሪ ቃል እ. አ. አ  በ1894 ዓ. ም እንደ መፈክር የተቀበለው ሲሆን፣ እ. አ. አ. ሐምሌ 20/2021 ዓ. ም. “በአንድነት” የሚለውን ቃል ተጨማሪ ማድረጉ ታውቋል።

ወደ ንግድነት የመቀየሩ ስጋት

“የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ከተሞች ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚጠየቁት ለምንድነው?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ቶማስ ባች፣ የስፖርት አንዱ ክፍል “በከፍተኛ ንግድ ላይ የተደገፈ” እንደሆነ ገልጸው፣ በሌላ ወገን “ለመዝናኛ ንግድነት” አደጋ የተጋለጠ መሆኑን አምነዋል። ሆኖም ግን በእነዚህ ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ በሚደረግባቸው ስፖርቶች ውስጥ እንኳን ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ሕጎችን እንደሚያከብር፣ ሁሉም እኩል እንደሆኑ፣ ዳኛውንም የሚያከብሩ መሆናቸውን እና የስፖርት ዋና ዋና እሴቶች አሁንም ተጠብቀው መቆየታቸውን አስረተዋል። ክቡር ቶማስ ባች በመጨረሻም፣ ሕጎች ያላቸውን ክብር ገንዘብ እንዲሽር ለማድረግ ጥረቶች ቢደረጉም፣ በአጠቃላይ ግን ስፖርት የራሱ እሴቶች ያሉት እና እሴቶቹም እየተጠበቁ መሆናቸውን በመግለጽ ቃለ ምልልሳቸውን ደምድመዋል።

01 October 2022, 17:11