ፈልግ

ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር ቀን ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር ቀን  

የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑት አዳዲስ አገልግሎቶችን አስተዋወቀ

ሚያዝያ 30/2014 ዓ. ም. የሚከበረው ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ቀንን ምክንያት በማድረግ በጣሊያን ውስጥ አንድ ሳምንት የሚቆዩ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ታውቋል። በተለያዩ ችግሮች ለተጎዱ ተጋላጭ ማኅበረሰብ የሚሆኑ አዳዲስ የአገልግሎት መስጫ መንገዶችም የተዘጋጁ ሲሆን፣ ከአገልግሎቶቹ መካከል አንዱ በስልክ ቁ. 1520 የሚሰጥ የመረጃ እና የምክር አገልግሎት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“እያንዳንዱ ሰው የግል ታሪክ ያለው፣ የሁሉም ሰው ታሪክ ይጠቅመናል” የሚለውን የዘንድሮ መሪ ቃል በማስቀደም መጭው እሑድ ሚያዝያ 30/2014 ዓ. ም. የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ቀንን ለማስተናገድ በጣሊያን ውስጥ ዘመቻ መጀመሩ ታውቋል። ዕለቱ የማኅበሩ መሥራች ሄንሪ ዱናንት እ. አ. አ. በ1828 ዓ. ም. የተወለደበት ቀን መሆኑ ታውቋል።

በዓለማችን ውስጥ ግዙፍ የተባለለት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት፣ ቀይ መስቀል ማኅበር ዘንድሮ በጣሊያን ውስጥ የሚከበረው ለአንድ ሳምንት በሚቆይ ልዩ ዝግጅት ሲሆን፣ በተጨማሪ ዘንድሮ በጣሊያን ውስጥ የሚከበረው አዳዲስ ሰብዓዊ የአገልግሎት ዘርፎችን በማስተዋወቅ እንደሆነ ታውቋል። በጣሊያን ከተሞች ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችን በማካሄድ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ዝግጅቱ ያለፈው እሑድ ሚያዝያ 23/2014 ዓ. ም. የተጀመረ ሲሆን የሚጠናቀቀውም ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ቀን በሚከበርበት እሑድ ሚያዝያ 30/2014 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል። 

ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ቀንን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚቀርቡ ዝግጅቶች አገልግሎቱን የሚያገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እርስ በእርስ ለማገናኘት እና ለማቀራረብ ያለመ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ማኅበሩ ዘንድሮ ይፋ ያደረገው የበዓሉ መሪ ሃሳብ፥ እንደምን አለህ? እንደምን አለሽ? ስምህ ማነው? ስምሽ ማነው? የት ትገኛለህ የት ትገኚያለሽ? የሚሉ ጥያቄዎችን ያካተተ እንደሆነ ታውቋል። እነዚህ ሦስት ጥያቄዎች በአስቸጋሪ ወቅት የሚሰሙ ስሜቶችን ለመግለጥ፣ የሰዎችን ማንነት ለማወቅ እና በአደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙትን ለመለየት የሚረዱ ጥያቄዎች መሆናቸው ታውቋል። 

ለዩክሬን እና ለወረርሽኙ ቀውስ ቅድሚያን መስጠት

ዘንድሮ ሚያዝያ 30/2014 ዓ. ም. የሚከበረው ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ቀን፣ የማኅበሩ መሥራች ሄንሪ ዱናንት የተመለከታቸውን ወቅታዊ የሆኑ ሰብዓዊ ቀውሶችን የሚያታውስ ሲሆን፣ ቀውሶቹን ለመቅረፍ በዓለማችን ውስጥ ባሉ የማኅበሩ አባል አገራት ውስጥ አሥራ አራት ሚሊዮን በጎ ፈቃደኞች እንደሚገኙ ታውቋል። ከእነዚህም መካከል ከ 150,000 የሚበልጡ አባላት በጣሊያን ውስጥ እንደሚገኙ የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚደንት እና ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ፍራንቸስኮ ሮካ ገልጸው፣ በጎ ፈቃደኞቹ ባሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ያስከተለውን ቀውስ ለማስወገድ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

አዳዲስ አገልግሎቶችን መክፈት

እሑድ ሚያዝያ 23/2014 ዓ. ም. የተጀመረው "የቀይ መስቀል ሳምንት" ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችን በማካሄድ የሚከበር ሲሆን፣ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመርዳት በማለም አዳዲስ አገልግሎቶችን ማስተዋወቁ ታውቋል። በጣሊያን ውስጥ በሚገኙ ማዘጋጃ ቤቶች ትብብር የማኅበሩ ሰንደቅ ዓላማ እንደሚውለበለብ እና ታሪካዊ ሕንጻዎች ውስጥ ቀይ መብራቶች እንደሚበሩ ታውቋል። የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር ከልዩ ልዩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር “ከአደጋ የመከላከል መብት” በሚል ርዕሥ በሮም ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች የመጀመሪያ ዕርዳታ አገልግሎቶችን በነጻ ማቅረብ መጀመሩ ታውቋል። ለማኅበረሰብ ጤና እና ድንገተኛ አገልግሎት የሚውል የስልክ መስመር ከዓርብ ሚያዝያ 28/2014 ዓ. ም. ጀምሮ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር ሲሆን፣ የአገልግሎት መስጫ ማዕከሉ ዋና መሥሪያ ቤት በሮም እንደሚከፈት ታውቋል።

ከአደጋው ተጠቂዎች ጋር መሆን

የቀይ መስቀል ማኅበር ዓላማን በመከተል ያለ ልዩነት የአደጋው ተጠቂዎች ፍላጎትን ለማሟላት እና ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ እንደሚጥሩ የገለጹት የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ሮዛሪዮ ቫላስትሮ፣ እያንዳንዱ የማኅበራቸው ተነሳሽነት ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንደሚከናወን አስረድተዋል። ከዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ቀን አስቀድሞ ለአንድ ሳምንት የሚቆየውን ዝግጅት እንዲያቀርቡ ያደረጋቸውን ምክንያት የገለጹት አቶ ሮዛሪዮ፣ ማኅበሩ በጣሊያን እና በመላው ዓለም የሚያቀርባቸውን ሰብዓዊ አገልግሎቶች ለማስታወስ የሚያስችል በቂ ጊዜን ለማግኘት እንደሆነ አስረድተዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በተለይም በገጠራማው አካባቢ የክትባት መርሃ ግብሮችን ሲካሂዱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። በጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር ሥር የሚያገለግሉ በጎ ፈቃደኞች በየዕለቱ የሚያበረክቱት ተግባራት እንዳሉ ያስታወሱት አቶ ሮዛሪዮ፣ በተለይም ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚናገሩትን የሕይወት ታሪክ ሲያዳምጡ እና ምላሽ ሲሰጡ መቆየታቸውን አስረድተዋል።

የቀይ መስቀል ማኅበር የተለያዩ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አቶ ሮዛሪዮ ገልጸው፣ ከጤና እንክብካቤ ጀምሮ ሌሎች ማኅበራዊ ችግሮችን፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አቅርቦትን የመሳሰሉ ተግባራትን እንደሚያካትት አስረድተዋል። ማኅበሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጣሊያን የኮቪድ-19 ወረርሽኙን ለመከላከል በንቃት መንቀሳቀሱን ገልጸው፣ ሁለት ሚሊዮን ከግማሽ ለሚደርሱ ዜጎች የመከላከያ ክትባትን በማዳረስ እና በሌሎች ማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ የወደቁ ሰዎችን ለመደገፍ ዕቅዶችን በማውጣት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ገልጸው፣ ይህም ቀይ መስቀል ማኅበር በሕዝቡ ዘንድ ያለውን የእምነት እና የግንዛቤ ደረጃ ከፍ እንዲል ማድረጉን የጣሊያን ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ሮዛሪዮ ቫላስትሮ አስረድተዋል።       

04 May 2022, 15:43