ፈልግ

በዩክሬን በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የተወለደ ሕጻን በዩክሬን በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የተወለደ ሕጻን  (ANSA) ርዕሰ አንቀጽ

አቶ ማሲሚሊያኖ ሜኒኬት፣ “ሴቶች የተስፋ ምሳሌዎች፣ ኃይል እና ፍቅር” መሆናቸውን ገለጹ

የቫቲካን ሬዲዮ ዳሬክተር አቶ ማሲሚሊያኖ ማኒኬቲ በዛሬው ዕለት የተከበረውን “ማርች 8” ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በገለጹት ሃሳብ፣ ሴቶች ተስፋን የሚሰጡ፣ ብርታትን እና ፍቅርን የሚጨምሩ መሆናቸውን አስረድተው፣ የሚከተለውን ጽሑፍ አቅርበዋል፥

በዩክሬን ውስጥ በጦርነት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ለስደት በተዳረጉበት መሆኑ ይታወቃል።

ዛሬ የካቲት 29/2014 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን፣ በዩክሬን ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ያሳዩትን ድፍረትን፣ ጥንካሬን እና ባሁኑ ጊዜ እያሳለፉ የሚገኙበትን ፈተና እና ልጆቻቸውን ከሞት ለማትረፍ ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ የተገደዱበት ጊዜ መሆኑ ይታወቃል። በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየታካሄደ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር ሆነው ሴቶች ጸሎት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

በዩክሬን ውስጥ ታንኮችን እና የሚፈነዱ ሮኬቶችን ለመቋቋም ከባሎቻቸው ጎን ለመቆም የወሰኑ ሴቶች እንዳሉም ተመክቷል። በጥይት ፍርስራሽ ውስጥ እና በሞርታር እሳት መካከል ልጆቻቸውን ጡት የሚያጠቡ፣ ዕርዳታን የሚያቀርቡ፣ ምግብ የሚያዘጋጁ፣ የሚወልዱ፣ አዲስ ተስፋን በመሰነቅ በየአገራቱ ድንበሮች ላይ ለብዙ ሰዓታት የሚጠብቁ ሴቶች መኖራቸውም ታይቷል። አገራቸው ዩክሬን በከባድ ጦርነት ውስጥ ስለምትገኝ መኪናቸውን እየነዱ ከአደጋው ለማምለጥ በሽሽት ላይ የሚገኙ ሴቶችም ታይተዋል።  የሰበሰቡትን ጥቂት ነገር ይዘው በብርድ እና በበረዶ መካከል የሚጓዙ ሴቶችም ታይተዋል።

በጦርነቱ መካከል ሕይወታቸውን ያጡ፣ የሚደፈሩ ልጃገረዶች፣ በቦምብና በጥይት የተመቱ ሴቶች መኖራቸው ተሰምቷል። ይህን ሁሉ አስፈሪ እና እስደናጋጭ ሁኔታን ማን በቀላሉ ሊቀበለው ይችላል? በሌላ ወገን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ከዩክሬን ውጭ፣ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎቻቸው ዕርዳታ የሚያሰባስቡ፣ በፖለቲካው እና በዲፕሎማሲው ሥራ ተሰማርተው መፍትሔ ፍለጋ ላይ የሚገኙ፣ በየጎዳናው ላይ ተቃውሞ የሚያሰቡ፣ የሚታሰሩ እና ድብደባ የሚደርስባቸው ሴቶች መኖራቸው ይታወቃል።

ሴት ልጆች፣ እህቶች፣ እናቶች፣ ሚስቶች፣ ጓደኞች፣ ማኅበረሰብን የሚገነቡ፣ ኤኮኖሚን የሚደግፉ፣ ትምህርት እና የፈጠራ ችሎታን ለማሳደግ ጥረት የሚያደርጉ ሴቶች፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት ለመከላከል፣ የሰውን ልጅ ከአደጋ ለማትረፍ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ በርካታ ሴቶች መኖራቸውም ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በያዝነው የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ "ሴትን መጉዳት እግዚአብሔርን ማስቆጣት ነው" ማለታቸውም ይታወሳል። ይህን መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በአውሮፓ ውስጥ የጦርነት ጥላ ገና ባልታየበት ጊዜ መሆኑ ይታወቃል። በዓለም ላይ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በጨመሩበት ባሁኑ ጊዜም ዝምታው ቀጥሏል። የተለያዩ ስነ ልቦናዊ እና አካላዊ ጥቃቶች በዝምታ የሚያሳልፉ ሴቶች፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻን እንዲፈጽሙ የሚገደዱ፣ ለሴትኛ አዳርነት ሕይወት የሚዳረጉ፣ ከአቅማቸው በላይ የሆነውን ሥራን እንዲሰሩ የሚገደዱ፣ የትምህርት ዕድልን የተከለከሉ፣ የሚገደሉ፣ ልጆቻቸው በጦርነት ሲሞቱ በዓይናቸው የሚመለከቱ በርካታ ሴቶች መኖራቸው ይታወቃል።  

እንዲህ ዓይነቱን አጸያፊ ድርጊት ማን በዝምታ ሊያልፈው ይችላል? ይህን በዝምታ ማለፍ የማይችሉት በዓለማችን ክፍሎች ያሉ፣ መለያየትን እና ጠላትነትን የሚቃወሙ፣ ለአንድነት እና ለፍቅር የሚሰሩ ሴቶች ናቸው። በቤተክርስቲያን ታሪክ፣ በዘመናቸው የኢየሱስ ክርስቶስን የማዳን ብርሃን ወደ ዓለም ያመጡ፣ በግፍ እና በፍርሃት የቆሰሉ ብዙ ቅዱሳት ሴቶች በአውሮፓ ውስጥ ይገኛሉ። ከእነዚህ ቅዱሳት ሴቶች መካከል የአውሮፓ አህጉር ደጋፊዎች እና ጠባቂዎች እንደ ቅድስት ብሪጅድ፣ የቢንገን ቅድስት ሂልድጋርድ፣ የቅዱስ መስቀል ቅድስት ቴሬዛ ቤኔዴታ እና የሲዬናዋ ቅድስት ካታሪናን መጥቀስ ይቻላል።

በዚህ አስጨናቂ ወቅት በዩክሬን እና በሌሎች የዓለማችን  ክፍሎች የሚካሄዱ ጦርነቶች እንዲያቆሙ፣ ሕዝቦች በሙሉ በሰላም እንዲኖሩ፣ የእውነተኛ ሰላም ባለቤት የእግዚአብሔር እናት ወደ ሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የአደራ ጸሎታችንን እናቀርባለን።

08 March 2022, 16:53