ፈልግ

ፌስቲቫሉን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጥበት ወቅት ፌስቲቫሉን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጥበት ወቅት 

ክርስቲያናዊ ሙዚቃ ፌስቲቫል በሰሜን ጣሊያን የሚቀርብ መሆኑ ተገለጸ

የሰሜን ጣሊያን ከተማ በሆነች ሳንሬሞ ከጥር 26-28/2014 ዓ. ም ድረስ የሚቆይ ክርስቲያናዊ ሙዚቃ ፌስቲቫል መዘጋጀቱ ታውቋል። ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚቀርበውን ይህን ክርስቲያናዊ ሙዚቃ ፌስቲቫል በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የቫቲካን ዜና አገልግሎት ሃላፊ አቶ ማሲሚሊያኖ ሜኒኬቲ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስ አጎስጢኖስ “የሚዘምር ሁለት ጊዜ ይጸልያል” ያለውን የጠቀሱት የቬንቲሚሊያ-ሳንሬሞ ከተማ ጳጳሳ ብጹዕ አቡነ አንቶኒዮ ሱዌታ፣ በሀገረ ስብከታቸው የሚቀርበውን ክርስቲያናዊ ሙዚቃ ፌስቲቫል ውበት ለማስረዳት ባደረጉት ንግግር፣ ፌስቲቫሉ ልዩ ከሆነው ጥበባዊ እና ሙዚቃዊ እሴት ጎን ለጎን የእምነት ምስክርነት ታላቅነት እና ሃብት የሚያጎላ መሆኑን አስረድተዋል። ፌስቲቫሉን በበላይነት ከሚከታተል ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቱ በተጨማሪ የሳንሬሞ ማዘጋጃ ቤትም መተባበሩን ገልጸዋል። የተማው ከንቲቫ ክቡር አቶ አልቤርቶ ቢያንኬሪ፣ ዘንድሮ የተጀመረው የክርስቲያናዊ ሙዚቃ ፌሲቫሉ በሚቀጥለው ዓመትም የሚዘጋጅ መሆኑን አስታውቀዋል። የፌስቲቫሉ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅት ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ፋብሪዚዮ ቬንቱሪ በበኩላቸው በፌስቲቫሉን ዝግጅት የተሰማቸውን ስሜት ሲገልጹ፣ ይህ ከፍተኛ መንፈሳዊ የሙዚቃ ዘውግ የጸሎት ታላቅነትን ለማሳየት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል። የቫቲካን ኒውስ ዋና ሃላፊ የሆኑት ክቡር አቶ ማሲሚሊያኖ ሜኒኬቲ በበኩላቸው፣ ክርስቲያናዊ ሙዚቃን በማስታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሩትን በመጥቀስ፣ “ከእግዚአብሔር ጋር የመነጋገሪያ ዕድል እና ተመሳሳይ ቋንቋ በሚናገሩ ሰዎች መካከል ያለውን ወንድማማችነት የሚያስታውስ ነው” በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የመጀመሪያ ዝግጅት ነው

“ከተማችን የመጀመሪያውን የክርስቲያን ሙዚቃ ፌስቲቫል ማስተናገድ በመቻሏ ደስተኛ ነኝ” ያሉት የሳንሬሞ ከተማ ከንቲቫ ክቡር አቶ አልቤርቶ ቢያንኬሪ፣ በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ በሰጡት የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫቸው እንደገለጹት፣ ሃሳቡ የሚመሰገን መሆኑን ከገለጹ በኋላ ከፌስቲቫሉ ዳይሬክተር ጀምሮ ለአዘጋጆቹ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።

የእምነት ምስክርነት ነው

ከከተማው ማዘጋጃ ቤት በኩል ለተደረገላቸው ድጋፍ እና ተነሳሽነት ልባዊ ምስጋናቸውን የገለጹት የቬንቲሚሊያ-ሳንሬሞ ከተማ ጳጳሳ ብጹዕ አቡነ አንቶኒዮ ሱዌታ፣ "ሳንሬሞ በትክክል 'የሙዚቃ ከተማ' ተብላ መጠራቷ እውነት እየሆነ መጥቷል!” ብለው  የዘንድሮው ተነሳሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄዶ መልካም ፍሬ የሚገኝበት እና በመስኩ ላይ ያሉትን መልካም እና ውድ የኃይል አንድነት የሚሰበሰብበት እንደሚሆን አምናለሁ" ብለዋል።   ጳጳሱ ቀጥለውም ተፎካካሪ አርቲስቶቹ "ዜማቸውን እና ጥበባቸውን ከትክክለኛው የእምነት ልምድ ጋር በማዛመድ ጠቃሚ እና ግልጽ መንፈሳዊ እሴቶችን አጉልተው የሚያሳዩበት ይሆናል” ብለዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜ መጽናኛ ነው

የፌስቲቫሉ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅት ዳይሬክተር ክቡር አቶ ፋብሪዚዮ ቬንቱሪ፣ “ሙዚቃ እንደ ነፋስ ሊቆም የማይችል ነው” ብለው “በዚህ አስቸጋሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት መጽናናትን በመስጠት ፈውስ የሚሰጥ ነው” በማለት ገልጸዋል። በወረርሽኙ ምክንያት ብዙ ቤተሰቦች በሐዘን ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው፣ “ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ክርስቲያናዊ ሙዚቃ ዛሬ ላይ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል፣ ምክንያቱም በተግባር ሊኖሩበት ከሚችሉት ውብ የጸሎት ዓይነቶች መካከል አንዱ ነው” ብለዋል።

ክርስቲያናዊ ሙዚቃ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች ሰፊ ቦታ እንዳለው እና በጣም የተከበረ መሆኑን አስረድተዋል።

ክርስቲያናዊ ሙዚቃን በተመለከተ በጣሊያን ውስጥ ገና ብዙ የሚቀር ሥራ እንዳለ ገልጸው፣ ዓላማቸውም ትኩረትን በመስጠት በሳንሬሞ በሚቀርብ ክርስቲያናዊ ሙዚቃ ፌስቲቫል አስደናቂ ሥራን ለማቅረብ መመኘታቸውን የፌስቲቫሉ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅት ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ፋብሪዚዮ ቬንቱሪ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

የደስታ እና የምስጋና መግለጫ

“የቫቲካን ሬዲዮ የተመሠረተበት ቀዳሚ ዓላማ እና ተልዕኮ የእግዚአብሔርን ቃል ማወጅ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ድምጽ ለዓለም ማዳረስ ነው” ያሉት የቫቲካን ኒውስ ዋና ሃላፊ ክቡር አቶ ማሲሚሊያኖ ሜኒኬቲ፣ የምሥራቹን ቃል በዝማሬ ማስተላለፍ ሬዲዮ ጣቢያው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሲቀርብ የቆየ መሆኑን ገልጸዋል። ዋና ሃላፊው አክለውም፣ የቫቲካን ዜና አገልግሎት የፌስቲቫሉ ዋና ሚዲያ መሆኑ ገልጸው፣ ክርስቲያናዊ ሙዚቃ ፌስቲቫሉ የእምነትን ደስታ የሚገለጽበት፣ የፌስቲቫሉ ታዳሚዎች በወንድማማችነት እርስ በእርስ በመደማመጥ መንፈሳዊ ሕይወትን በመኖር ሲኖዶሳዊነትን እንዲጋሩ መመኘታቸውን ለመዘምራኑ ባቀረቡት መልዕክት አስረድተዋል።

02 February 2022, 15:20