ፈልግ

የአፍጋኒስታን ሴቶች በማኅበራዊ ዕድገት ተግባር ላይ ሲወያዩ የአፍጋኒስታን ሴቶች በማኅበራዊ ዕድገት ተግባር ላይ ሲወያዩ 

በአፍጋኒስታን የታሊባን አስተዳደር 500,000 ሰዎችን ከሥራ ገበታቸው ማስወገዱ ተነገረ

የዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት በዘገባው እንዳታወቀው በአፍጋኒስታን ውስጥ የታሊባን አስተዳደር ከተመሠረተ ከአጭር ወራት ወዲህ 500,000 ሰዎች ከሥራ ገበታቸው መወገዳቸውን ገልጾ ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ገልጿል። ይህ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ መጨመር ሊያስከትል እንደሚችል አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአፍጋኒስታን ውስጥ የታሊባን አስተዳደር በተሠረተ በ5 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከሥራ ገበታቸው መፈናቀላቸው ተገምቷል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረቡዕ ጥር 11/2014 ዓ. ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ አስታወቀ። እ. አ. አ በነሐሴ ወረ 2021 ዓ. ም. አጋማሽ ላይ በአፍጋኒስታን ውስጥ የተደረገውን የአስተዳደር ለውጥ ተከትሎ የተፈጠረው ቀውስ የአገሪቱን ኤኮኖሚ ሽባ በማድረግ በሥራ ገበያው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (አይኤልኦ) በዘገባው አስታውቆ፣ በሥራ እና በሥራ ሰዓት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ መድረሱን አመልክቷል።

የሴቶች የሥራ ዕድል

ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅቱ እ. አ. አ በ2022 ሁለተኛ ሩብ ላይ በሥራ ላይ የሚደርስ ኪሳራ ወደ 700,000 እንደሚጠጋ ገልጾ፣ የሥራ ተቋማት ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ ሲታገሉ በሌላ ወገንም የሥራ ዕድል እየቀነሰ መምጣቱን ገልጿል። ሴቶችን ከሥራ ገበታ ማፈናቀሉ ከቀጠለ እና ስደት ከጨመረ እ. አ. አ በ2022 ሁለተኛ ሩብ ዓመት ላይ በሥራ ስምሪት ላይ የሚደርስ ኪሳራ ከ900,000 በላይ ሊደርስ ይችላል ተብሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴቶች የሥራ ስምሪት ደረጃ እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም እ. አ. አ በ2021 ሶስተኛ ሩብ ላይ 16 በመቶ እንደሚቀንስ እና በ2022 አጋማሽ ላይ ከ21 በመቶ እስከ 28 በመቶ መካከል ሊቀንስ እንደሚችል ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ግምቱን አስፍሯል። 

በአፍጋኒስታን ያለው ቀውስ ቀድሞውንም ለሴት ሠራተኞች ፈታኝ ሁኔታ መሆኑን የገለጹት እና  በአፍጋኒስታን ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ከፍተኛ አስተባባሪ አቶ ራሚን ቤህዛድ፣ በአንዳንድ ቁልፍ ኤኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚታየው የሥራ ቁጥር መመናመን በሴቶች ተሳትፎ ላይ የተጣለው አዲስ እገዳ አሉታዊ ገጽታ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል። የድርጅቱ አስተባባሪው በአፍጋኒስታን ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት እና እንዲያገግም ለማድረግ ፈጣን ድጋፍ ያስፈልጋል ብለው፣ በተጨማሪም ቅድሚያ የሚሰጠው ሰብአዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ቢሆንም ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ለውጥ የማኅበረሰቦችን ኑሮ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ያማከለ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ክፉኛ የተጎዱ ዘርፎች

አፍጋኒስታንን የታሊባን ኃይሎች ከተቆጣጠሩት ወዲህ በብዙ ቁልፍ የሥራ ዘርፎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የሥራ ኪሳራ መድረሱን ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት አስታውቋል። ኪሳራ ካጋጠማቸው የሥራ ዘርፎች መካከል ግብርና፣ የመንግሥት አስተዳደር፣ ማኅበራዊ አገልግሎት እና የግንባታ ሥራዎች እንደሆኑ ድርጅቱ ገልጾ፣ በግብርና እና ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ላይ በደረሰው ከሥራ የተባረሩ ወይም ሳይከፈላቸው የቀሩ መኖራቸውን አስታውቋል። ከግንባታ ዘርፉ የተባብረሩት ሠራተኞች ቁጥር 538,000 ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 99 በመቶው የሚሆኑ ወንዶች መሆናቸውን አስታውቆ ሌሎችም ዋና ዋና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መቆማቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

በአፍጋኒስታን ያለው የታሊባን አስተዳደር እንደዚሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአፍጋኒስታን የጸጥታ ሃይል አባላት ሥራቸውን እንዲያቋርጡ ማድረጉ ታውቋል። የዓለም ለጋሾች ድጋፋቸውን እየቀነሱ ባሉበት በዚህ ወቅት መምህራን እና የጤና ሠራተኞች ኤኮኖሚውን ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት በጥልቅ የተጎዱ መሆናቸውን ድርጅቱ አስታውቋል። በአፍጋኒስታን ውስጥ የሀገር ውስጥ ገበያዎች በሰፊው መስተጓጎላቸውን የገለጸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቱ፣ ምርታማ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ እየቀነሰ በመምጣቱ የምርት ወጪን ከፍ ማድረጉን አስታውቋል። የአፍጋኒስታን 9.5 ቢሊዮን ዶላር ሀብት በመታገዱ ምክንያት የውጭ ዕርዳታ፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት  ክፉኛ መጎዳቱን ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅቱ ገልጾ፣ አክሎም የገንዘብ እጥረት እና በባንክ ሂሳብ ላይ እገዳዎች መጣላቸው በንግድ ድርጅቶች በሠራተኛ ማኅበረሰብ እና በቤተሰብ ሕይወት ከፍተኛ ችግር ማስከተሉን ገልጿል።

የሕጻናት ጉልበት

በአፍጋኒስታን ውስጥ የታየው የሥራ እጦት የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን ሊያባብስ እንደሚችል ያሰጋል ያለው ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅቱ፣ ከ5 እስከ 17 ዓመት እድሜ ካላቸው ሕጻናት መካከል 40 በመቶ ብቻ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ መሆኑን አስታውቋል። ብዙ ቁጥር ያላቸው ሕጻናት ትምህርት ማቋረጣቸውን፣ ከእነዚህም ዘጠኝ በመቶው የሚሆኑ ዕድሜያቸው  ከ5 እስከ 17 ዓመት የሆናቸው ሕጻናት ለጉልበት ብዝበዛ መዳረጋቸውን፣ ከእነዚህ መካከል ከ770,000 በላይ የሚሆኑ ወንዶች ሲሆኑ ወደ 300,000 የሚጠጉ ሴት ሕፃናት መሆናቸውን ድርጅቱ ገልጿል። ችግሩ በገጠራማው አካባቢዎች በጣም የከፋ ነው ያለው ድርጅቱ፥ 9.9 በመቶ ወይም 839,000 ህጻናት በከተማ ከሚገኙት 2.9 በመቶ ወይም 80,000 ጋር ሲነፃፀሩ በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ ሕፃናት ለጉልበት ብዝበዛ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አስታውቋል።

በዚህ ዓመት የአፍጋኒስታንን ሕዝብ ለመደገፍ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቅድሚያ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች፣ የሕይወት አድን ዕርዳታ መስጠት፣ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ማስቀጠል እና ማኅበራዊ ኢንቨስትመንቶችን እና መሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶችን ለማሟላት አስፈላጊ የሆኑ ማኅበራዊ ሥርዓቶች ማስጠበቅ መሆኑ ታውቋል። ይህንን እቅድ ለማስፈጸም ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ከአሠሪዎች እና ከሠራተኛ ማኅበራት ጋር በመተባበር ውጤታማ የሥራ ስምሪት ያለበት ተግባር ለማከናወን ቃል መግባቱ ታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአራት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን እነሱም የድንገተኛ ጊዜ ሥራ ስምሪት አገልግሎት፣ ሥራ ተኮር ኢንቨስትመንቶችን ማበረታታት፣ የሥራ ድርጅቶችን ማስተዋወቅ እና ክህሎትን ማጎልበት ፣ የሠራተኛ መብቶችን ፣ የጾታ እኩልነትን እና ማኅበራዊ ውይይት እና ጥበቃ ማጠናከር፣ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ማስወገድ እና የአካል ጉዳተኞችን ማካተት የሚሉ መሆናቸው ታውቋል።

21 January 2022, 13:29