ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን በቆጵሮስ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች (የስደተኞች መጠለያ ጉብኝታቸው) ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን በቆጵሮስ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች (የስደተኞች መጠለያ ጉብኝታቸው) 

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ጉብኝት በቆጵሮስ ብዙሃን መገናኛዎች አድናቆትን ማግኘቱ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኅዳር 23-25/2014 ዓ. ም. ድረስ በቆጵሮስ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አድናቆት ማግኘቱ ዜጎችን ያስደሰታቸው መሆኑ ተገለጸ። ቅዱስነታቸው በቆጵሮስ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት ለአውሮፓ ኅብረት አገራት ያስተላለፉትን መልዕክት በማስታወስ የአገሪቱ መገናኛዎች አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሜዲቴራኒያ ደሴት በሆነችው ቆጵሮስ ባደረጉት የሦስት ቀናት ጉብኝት ወቅት የተወያዩባቸው ርዕሠ ጉዳዮች የዜጎችን ልብ መንካቱ ተገልጿል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቆጵሮስ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀደም ሲል በቆጵሮስ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን በቆጵሮስ የማሮናይት ሥርዓት አምልኮን የመትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋዜጠኛ ክርስቲያን ሴውስ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ገልጿል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ቆጵሮስን ጎበኝተው ከተመለሱ በኋላ የታዩት ለውጦች ብዙ እንደሆኑ ክርስቲያን ገልጾ፣ የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሙሉ ቅዱስነታቸው በደሴቲቱ ያደረጓቸውን እንቅስቃሴዎች በቀጥታ ስርጭት ሲዘግቡ እንደነበር ገልጾ፣ ይህም ከዚህ በፊት ደሴቲቱን በጎበኙት ሰዎች ፈጽሞ ያልታየ ክስተት መሆኑን አስረድቷል።

ማኅበራዊ መገናኛዎች የሕዝቡን ስሜት እና ውሳኔ እንዲሁም የሚሆነውን ሁሉ በግልጽ የማሳየት አቅም እንዳላቸው ጋዜጠኛ ክርስቲያን ገልጾ፣ ጥቂት ርዕሠ ዜናዎች እና ጋዜጣዊ መግለጫዎች የሚወጡባት ቆጵሮስ በእነዚህ ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሯቸው የተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ሰፊ እና ከባድ ሆነው የቆዩ ጉዳዮችን በመልካም ቃላት ማብራሪያ የሰጡበት በመሆኑ ብዙዎችን ያስደነቃቸው መሆኑን ተናግሮ፣ ለዚህ የተሰጡ በጎ አስተያየቶችን ከማኅበራዊ መገናኛዎች መገንዘብ መብቃቱን አስታውቋል።

የካቶሊክ እምነት ተከታይ ካልሆኑ አንዳንድ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምዕመንና በኩል የቀረቡ አስተያየቶችንም መመልከቱን የገለጸው ጋዜጠኛ ክርስቲያን፣ እነዚህ መዕመናን ምናልባት ስለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ስለ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስን እውቀት ያላቸው ሰዎች መሆኑን አለባቸው ብሎ፣ ነገር ግን የቅዱስነታቸውን ንግግር ካዳመጡ በኋላ የነበራቸው ግንዛቤ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን አስረድቷል። የመንግሥት ባለ ሥልጣናትም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት እጅግ መደነቃቸውን ጋዜጠኛ ክርስቲያን ገልጾ፣ ቅዱስነታቸው ወደ ሮም ሲመለሱ ከጥገኝነት ጠያቂዎች መካከል የተወሰኑትን ወደ ሮም መውሰዳቸው ትልቅ ትርጉም እንዳለው በአስተያየታቸው መግለጻቸውን ተናግሯል።

ቆጵሮስ ስደተኞችን ተቀብላ ለማስተናገድ እና ለዜጎቿ መልካምን ለማድረግ የተቻላትን ሁሉ በማድረግ ላይ እንዳለች የገለጸው ጋዜጠኛ ክርስቲያን፣ የቅዱስነታቸው በቆጵሮስ የፈጸሙት መልካም ተግባር አውሮፓ አገራት እና ምዕራቡ ዓለምም የመረዳዳትን ትርጉም እንዲያውቁ ለማድረግ ትልቅ ምሳሌ መሆኑን አስረድቷል። ጋዜጠኛ ክርስቲያን በማከልም ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከቆጵሮስ ወደ ጣሊያን መወሰዳቸው ለወደፊት ሕይወታቸው ጥሩ እድል እንደሚፈጥርላቸው ያለውን እምነት ገልጿል።

06 December 2021, 18:00