ፈልግ

የድህነት እና የመገለል ሕይወት የድህነት እና የመገለል ሕይወት  

ሁሉ አቀፍ ማኅበራዊ ሕይወትን ለመመሥረት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. አሲሲ ከተማን ከጎበኙ በኋላ እና 5ኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በሚከበርበት ዋዜማ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት፣ በጣሊያን የሚገኝ የ “ሳክሮ ኩዎሬ” ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ አንቶኔላ ሻሮኔ፣ በጣሊያን ያለውን አሳሳቢ የድህነት ገጽታን በማስታወስ የድህነት መከላከያ መንገዶች ፍለጋን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ትናንሽ የንግድ ተቋማትን እና ሴቶች የሚሳተፉባቸውን የሥራ መስኮችን መደገፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፣ ለዜጎች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ ግራ እንዳያጋባ የአሰራር ዘዴ ካልተቀየረ በቀር ሃብት የሚባክን መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጣሊያን ውስጥ እ. አ. አ 2021 ዓ. ም. ይፋ የሆነው ዓመታዊ ስትቲስቲክስ እንደገለጸው፣ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል የሚታየው ድህነት ከ 2 ሚሊዮን በላይ ቤተሰቦችን እንደጎዳ እና በፍጆታ መጠን ላይም ጉዳት ማስከተሉን አስታውቋል። በጣሊያን የሚገኝ ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅት የ2021 ዓ. ም. ሪፖርት እንደገለጸው፣ ሥር በሰደደ የድህነት ሕይወት ውስጥ ወድቀው ላለፉት አምስት ዓመታት እና ከዚያም በላይ የዕርዳታ ጥገኛ የሆኑት ሰዎች ብዛት ከ25.6 ከመቶ ወደ 27.5 ከመቶ ማደጉን አመልክቷል። እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም. በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በድህነት ሕይወት ውስጥ የወደቁ አዳዲስ ቤተሰቦች መመዝገባቸው ታውቋል።

የ“ሳክሮ ኩዎሬ” ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ዳይሬክተር፣ በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚ ፕሮፌሰር እና በቫቲካን የገንዘብ ቁጥጥር እና መረጃ ባለስልጣን የሆኑት ወ/ሮ አንቶኔላ ሻሮኔ፣ በቅርቡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ባቋቋሙት ጽ/ቤታቸው በኩል ይፋ ባደረጉት መረጃ፣ ማኅበራዊ ሕይወትን የሚደግፉ መፍትሄዎችን በመለየት ከመጠን በላይ የሆኑ የዕዳ ጫና እና አዳዲስ የድህነት ዓይነቶች በማደግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ወ/ሮ አንቶኔላ ሻሮኔ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ “ድሆች” የሚለው አስተሳሰብ በጣም ዘርፈ ብዙ እንደሆነ እና “የሚያሳዝነው በርካታ የተለያዩ የድህነት ዓይነቶች በማደግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

ረዘም ላለ ጊዜ ሥራ ባለመኖሩ ምክንያት ከሚያጋጥም ሥር የሰደደ ድህነት በተጨማሪ ከድንገተኛ እና ባልተጠበቀ ከሥራ መጥፋት ጋር የተቆራኘ ድህነት መኖሩን ገልጸው፣ አነስተኛ የግል ሥራ ዘሮፍች ፣ የእጅ ባለሞያዎች ፣ በተለይም ትላልቅ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከደረሰባቸው ቀውስ በማገገም መሻሻልን ለማሳየት ተስፋ ሊያደርጉ ቢችሉም፣ በአሁኑ ጊዜ ​​ከመካከለኛው እና ከዚያ በላይ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ መገለል ያጋጠማቸው እና ካለፈው ጊዜ ይልቅ አሁን እኩልነት በጎደለው ሕይወት ውስጥ መገኘታቸውን አስታውሰዋል። ኤኮኖሚያዊ ቀውሱ እና የዕዳ ጫና መጠን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ከፍተኛ እንደነበር፣ ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ በአስፈሪ ሁኔታ ማደጉን አስረድተዋል። ድህነትን ለመቅረፍ በተቋማት እና በመንግሥት ተወካዮች በኩል አዳዲስ መፍትሄዎችን መፈለግ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ወ/ሮ አንቶኔላ ሻሮኔ፣ በግል ደረጃ እና ከበጎ አድራጎት የልማት ዕቅዶች ወደ ገንቢ የኤኮኖሚ ዕቅዶች መሸጋገር እንደሚያስፈልግ ሃሳብ አቅርበዋል። ድህነት ባለበት ዕዳ እንዳለ፣ ዕዳ ባለበት ደግሞ አበዳሪዎች መኖራቸውን የገለጹት ወ/ሮ አንቶኔላ፣ አበዳሪዎች እና ተበዳሪዎች በአንድ ላይ ሆነው ለሁሉም ሰው የሚሆን በቂ መፍትሄ ለማግኘት አብረው ከሠሩ ከድህነት የሚወጣበትን ትክክለኛው መንገድ ማግኘት ይቻላል ብለው፣ ውጤታማ መፍትሄዎችን ማግኘት የሚቻለው አብሮ መሥራት ሲቻል ነው ብለዋል።

ኤኮኖሚያዊ ቀውሶችን እና ድህነትን የምናሸንፍባቸው ቀላል መመሪያዎች ባይኖሩም ነገር ግን ትምህርት እና ስልጠና በጣም አስፈላጊ መሆኑን ወ/ሮ አንቶኔላ ገልጸው፣ ከሥነ-ምህዳር፣ ከዲጂታል ሽግግር እይታ አንጻር ብዙ ለውጦች ሲኖሩ፣ በዚህ ዕድል ውስጥ ሰዎች እንዲገቡ መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በወጣቱ ዓለም ምንም የማይሰሩ ብዙ ወጣቶች አሉን ያሉት ወ/ሮ አንቲኔላ፣ የሚያስጨንቀው ከወጣትነት የዕድሜ ክልል ያልሆኑ፣ ከሥራ ዘርፍ የተባረሩት እንደገና ሥራን ለመፍጠር ትልቅ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ አለባቸው ብለዋል።

ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጠንካራ እና ተቀባይነት ካላቸው ባህሪያት መካከል አንዱ ድህነትን ለመዋጋት የተለያዩ አቀራረቦችን እና ማኅበራዊ ሞዴል ለውጦች ጋር አብሮ የሚሄዱ ዘዴዎችን ማሰባቸው ነው ያሉት ወ/ሮ አንቶኔላ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቤተክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮን ከኢኮኖሚያዊ እና ገንዘብ ነክ ዕይታ አንጻር የሰጡን አንዳንድ ልዩ ትምህርቶች እንዳሉ ገልጸዋል። ድህነት በከፊል የብዙ ኅብረተሰብ  ፍላጎት ማሟላት ያልቻለ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ሥርዓት ውጤት ነው ያሉት ወ/ሮ አንቶኔላ፣ ድህነት መሸነፍ ያለበት፣ የበለጠ የሚያስተባብር እና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ማለፍ እንዳለብን የሚጠይቅ ፈተና እንደሆነ አስረድተዋል።

15 November 2021, 15:14