ፈልግ

የቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የሱልጣን ማሊክ አል-ካሚል የመጀመሪያ ግንኙነት የቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የሱልጣን ማሊክ አል-ካሚል የመጀመሪያ ግንኙነት 

የቅዱስ ፍራንችስኮስ እና የሱልጣን ማሊክ አል-ካሚል ግኑኝነት ለስነ-ጥበብ ሥራ ግብዓት መሆኑ ተገለጸ

ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከ800 ዓመት በፊት ማለትም እ. አ. አ በ1219 ዓ. ም. ወደ ግብጽ በመጓዝ ከሱልጣን ማሊክ አል ካሚል ጋር ያደረገውን ግንኙነት የሚያብራራ መጽሐፍ መታተሙ ታውቋል። መጽሐፉ ባሁኑ ጊዜ በልዩ ልዩ ሐይማኖቶች መካከል እየተካሄደ ያለውን የጋራ ውይይት ለሚያጠኑ የታሪክ እና የስነ ጥበብ ሰዎች ከፍተኛ ግብዓት ሆኖ መገኘቱ ታውቋል። በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም በምትገኝ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስተባባሪነት በጣሊያንኛ ቋንቋ የታተመው ይህ መጽሐፍ፣ ከጣሊያንኛ ቋንቋ በተጨማሪ በአረብኛ ቋንቋም ተተርጉሞ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ለዚህ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉት የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የጣሊያን ዓለም አቀፍ ትብብር መሥሪያ ቤት መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና ሱልጣን ማሊክ አል ካሚል” በሚል ርዕሥ የታተመውን መጽሐፍ በአራት ክፍሎች በመለየት ለዜማ እንዲሆን ያዘጋጁት፣ በትሪፖሊ የቅዱስ ፍራንችስኮ ገዳም አለቃ ክቡር አባ ኪሪኮ ካሌላ መሆናቸው ታውቋል። በመጽሐፉ ዝግጅት ላይ የተሳተፉት በጣሊያን ውስጥ ኔፕል ከተማ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ በሜዲትራኒያን አካባቢ የአረብ እና እስልምና ጥናት ፋኩልቲ ውስጥ የቀድሞ የአረብኛ ቋንቋ እና ስነፅሁፍ ሙሉ ፕሮፌሰር እና በሮም በሚገኝ ጳጳሳዊ ተቋም የአረብ እና እስልምና ጥናቶች ተጋባዥ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር በርቶሎሜዎስ ፒሮን ሲሆኑ፣ በሙዚቃው ቅንብር የተባበሩት ክቡር አባ ካሊል ራህሜ መሆናቸው ታውቋል። 

በምዕራባዊ እና ምሥራቃዊ አካላት የተቃኘ የሙዚቃ ቅንብር

በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም በምትገኝ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስተባባሪነት በጣሊያንኛ ቋንቋ የታተመው ይህን መጽሐፍ ወደ አረብኛ የተረጎሙት ወ/ሮ ተሬዝ ፍራንቺስ ሲሆኑ፣ የሽፋን ገጽ ምስል ያዘጋጁት ሰዓሊ ክቡር አባ ማውሪሲዮ ፒያሳ መሆናቸው ታውቋል። የዜማ ቅንብር ዘይቤው የምዕራባውያን ክላሲካል ሙዚቃን ፣ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዜማ ጭብጦችን የሚያስታውስ ፣ የጎርጎሮሳዊ ዜማን፣ የሶርያ ዝማሬን፣ የቤተ ክርስቲያን መዝሙሮችን እና የምሥራቅ ቤተክርስቲያን ዜማዎችን የሚያስታውስ ሲሆን፣ ይዘቱ የባክ እና የፔሮሲ አፈ ታሪኮችን የሚያስታውስ መሆኑ ታውቋል።

“ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና ሱልጣን ማሊክ አል ካሚል” የሚል መጽሐፍ ዝግጅት የተጀመረው፣ ሁለቱ ሰዎች ማለትም ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና ሱልጣን ማሊክ አል ካሚል በግብጽ ውስጥ ዳሚዬታ ላይ የተገናኙበት 800ኛ ዓመት፣ እ. አ. አ በ2019 ዓ. ም. ከመከበሩ በፊት መሆኑ ተነግሯል። መጽሐፉ በኮንሴርት መልክ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው እ. አ. አ ኅዳር 6/2020 ዓ. ም. በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት በሚገኝ ቅዱስ ኤሊያስ ቤተክርስትያን ውስጥ ሲሆን፣ በኅዳር 7/2020 ዓ. ም. ላይ በትሪፖሊ ከተማ በሚገኝ ቅዱስ ማሩን ቤተክርስትያን ውስጥ እንደነበር ይታወሳል። በቤይሩት ከሚገኝ የጣሊያን ባሕል ተቋም ጋር በመተባበር በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም በድጋሚ መቅረቡ ይታወሳል። በሁለቱ አገሮች የቀረቡትን የዜማ ዝግጅቶች ኑርሳት እና ቴሌሉሚዬር የተባሉ የቴሌቪዥን ጣሚያዎች ያቀነባበሩ ሲሆን፣ የቪዲዮ ምስሉን ባሁኑ ጊዜ በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የሚገኝ ኦርጋን ፌስቲቫል የተባለ ድርጅት በዘረጋቸው፣ ዩቲዩብ እና ፌስቡክ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት መመልከት የሚቻል መሆኑ ታውቋል።

ታሪኩ በዝርዝር ሲታይ

በመጽሐፉ የመጀመሪያ ክፍል ላይ የተገልጸው ታሪክ አሲሲ ውስጥ የተፈጸመ ሲሆን፣ ይህም ኪያራ እና ወንድም ኤልያስ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ወደ ግብፅ የመሄድ ፍላጎቱን ለማዘናጋት ያደረጉትን ከንቱ ሙከራ የሚገልጽ መሆኑ ተገልጿል። ሁለተኛው እና ሦስተኛው ትዕይንት ቅዱስ ፍራንችስኮስ ወደ መካከለኛው አክሪ እና ከዚያም ወደ ግብፅ ያደረገውን የባሕር ላይ ጉዞን የሚገልጽ ሲሆን፣ አራተኛው ትዕይንት ቅዱስ ፍራንችስኮስ በግብጽ ዳሚዬታ ወደ ተባለች መንደር ሲደርስ፣ ሱልጣን አል-ማሊክ አል ካሚን ከልጁ ፋጢማ እና ከሌሎች ታዋቂ ሰዎች ጋር አቀባበል ያደርገለትን የሚገልጽ ክፍል እንደነበር ተመልክቷል። ቅዱስ ፍራንችስኮስ ወደ ዳሜዬታ በገባበት ዕለት ሌሊት የሱልጣን አል-ማሊክ አል ካሚን ልጅ ፋጢማ በሕልሟ የሚከፍት የሮማን ፍሬ ማየቷን እና በቅዱስ ፍራንችስኮስ የተመሩ “በርካታ የዓለም ድሆች ከሱፍዮች ያልተለዩ፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር የተዋቡትን” እና በሌላ ወገን ሱልጣኑ ሊከተል ስለሚገባው ባህሪ ሲያሰላስል የሚገልጽ ክፍል መሆኑ ተመልክቷል። ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከሱልጣን አል-ማሊክ አል ካሚን ጋር ሁለት ጊዜ የተገናኘ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ግንኙነታቸው ትንሽ የሻከረ ቢሆንም ወዲያው ተስተካክሎ ሁለቱ በወንድማማችነት አንድ የሚያደርጋቸውን ጸጋ የተገነዘቡበት እንደነበር ታውቋል። ቅዱስ ፍራንችስኮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ላይ ያለውን እምነት ለሱልጣኑ ባስረዳው ጊዜ፣ ሱልጣኑ ከአንድ የማታ ጸሎት በኋላ ቅዱስ ፍራንችስኮስ በእምነቱ ሥር የሰደደ፣ ለሕዝቡም የሚጨነቅ እንደሆነ መንገሩ ተገልጿል። የጓደኝነት ምልክት እንዲሆነው፣ ከአሲሲ የመጣው ወጣቱ ቅዱስ ፍራንችስኮስ እና እሱን የሚከተሉት ወንድሞቹ፣ በእርሱ ቁጥጥር ስር ወዳሉት ቅዱሳን ቦታዎች በነፃነት መድረስ እንደሚችሉ በመግለጽ፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ወደ አገሩ አሲሲ ሲመለስ በማሳየት ትዕይንቱ የሚያበቃ መሆኑ ተመልክቷል።

18 November 2021, 08:45