ፈልግ

ዓለም አቀፍ የመንፈሳዊ ዜማ እና ሥነ-ጥበብ ኮንሴርት ዓለም አቀፍ የመንፈሳዊ ዜማ እና ሥነ-ጥበብ ኮንሴርት 

ሃያኛ ዙር የመንፈሳዊ ዜማ እና ሥነ-ጥበብ ኮንሴርት በሮም እንደሚካሄድ ተገለጸ

ዘንድሮ ለሃያኛ ጊዜ የሚቀርብ የመንፈሳዊ ሥነ-ጥበብ እና የሙዚቃ ኮንሴርት በተለያዩ የእምነት ተቋማት መካከል የወንድማማችነትን ስሜት እና ሰላምን ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ታውቋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከገባ ወዲህ ተቋርጦ የቆየው ይህ ዓመታዊ ፌስቲቫል፣ በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኙ ባዚሊካዎች ውስጥ ከኅዳር 4-7/2014 ዓ. ም. ድረስ ስድስት የመንፈሳዊ ዜማ ዝግጅቶችን ለማቅረብ መዘጋጀቱ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሃንስ አልቤርት ኩርሻል የተጀመረው የቤተክርስቲያን ዜማ እና የሥነ-ጥበብ ኮንሴርት እ. አ. አ ከ2002 ዓ. ም. ጀምሮ በየዓመቱ ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል። የመንፈስዊ ዜማ ስልቶችን ከትላልቅ ጳጳሳዊ ቤተክርስቲያናት ጋር ለማገናኘት በሚል ዓላማ የተጀመረው ታላቅ ዓመታዊ ፌስቲቫል፣ ዘንድሮ ኅዳር 4/2014 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በሚቀርበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የሚጀምር መሆኑ ታውቋል። ከፌስቲቫሉ መክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ቀጥሎ በሮም ከተማ በሚገኙ ትላልቅ ባዚሊካዎች፣ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ፣ በሎዮላው ቅዱስ ኢግናጢዮስ ቤተክርስቲያን፣ በቅድስት ማርያም ባዚሊካ እና በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ የመንፈሳዊ ዜማ ኮንሴርት የሚቀርብ መሆኑ ታውቋል። በሮም ከተማ በተጠቀሱ ባዚሊካዎች ውስጥ የሚቀርቡ ስድስት የመንፈሳዊ ዜማ ኮንሴርቶች ያለፈው መስከረም 8/2014 ዓ. ም. በስፔን ባርሴሎና ከተማ በተዘጋጀው ፌስቲቫል መቅረባቸው ታውቋል።

የዚህ ዓመታዊ የመንፈሳዊ ዜማ ኮንሴርት መሥራች የሆኑት አቶ ሃንስ አልቤርት ኩርሻል፣ በባርሴሎና እና በሮም ከተሞች በሚገኙ ባዚሊካዎች የሚቀርበው መንፈሳዊ የዜማ ኮንሴርት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጨናግፎ የነበረው ዓመታዊ የዜማ ኮንሴርት በአዲስ ስሜት እንደገና የሚጀምር መሆኑን ገልጸዋል።

የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ዝግጅት ነው

ዘንድሮ በሚካሄድ ሃያኛው ዙር ለሮም ነዋሪዎች የሚቀርብ የዜማ ኮንሴርት፣ በአሜሪካው የቴሌቪዥን አውታረመረብ በኩል የአካባቢ ጥበቃን እና በሐይማኖቶች መካከል የሚደረገውን የጋራ ውይይት የሚያጠናክር መሆኑ ታውቋል። በተለይም ቅዳሜ ኅዳር 4/2014 ዓ. ም. የሚቀርብ የዜማ ኮንሴርት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ቅዳሜ ኅዳር 4/2014 ዓ. ም. የሚቀርብ የዜማ ኮንሴርት፣ የዓለም መንግሥታት ተወካዮች በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት ከጥቅምት 21 - ኅዳር 3/2014 ዓ. ም. ሲያካሂዱት የቆየውን ጉባኤ ማጠቃለያን ምክንያት በማድረግ መሆኑ ታውቋል።   

ለዳንቴ ክብር የሚቀርብ የግጥም እና የሙዚቃ ዝግጅት

የዜማ ኮንሴርቱ እሑድ ጥቅምት 5/2014 ዓ. ም. በሚያቀርበው ዝግጅቱ ዕውቁ ጣሊያናዊ ገጣሚ ዳንቴ አልጌርን ለማስታወስ መሆኑ ታውቋል። ይህን ታላቅ የሥነ-ጥበብ ሰው በማስታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጻፉት መልዕክት “የሥነ-ጥበብ ሰው ዳንቴ፣ የአዲስ ሕልውና መልዕክተኛ፣ ሰላምን እና ደስታን የሚፈልግ የአዲስ ስብዕና ነቢይ” ነቢይ በማለት መግለጻቸው ይታወሳል።  

ዜማ የጋራ ውይይት መጠቀሚያ መሣሪያ ነው

ዘንድሮ የሚከበረው ሃያኛ ዙር የቤተክርስቲያን ዜማ ኮንሴርት የሚፈጸመው፣ ሰኞ ጥቅምት 6/2014 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኙ በሎዮላው ቅዱስ ኢግናጢዮስ ቤተክርስቲያን ውስጥ እና በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ውስጥ በሚቀርቡ የመንፈሳዊ ዜማ ዝግጅቶች እንደሚሆን ታውቋል። በመተጨማሪም በሮም ከተማ ውስጥ በሚገኙ ሁለቱ ባዚሊካዎች ውስጥ የሚቀርብ የዜማ ዝግጅቶች፣ በእምነቶች እና በባህሎች መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት ዓለም አቀፋዊ ገጽታ እንዳለው የሚያመላክቱ እንደሚሆኑ ታውቋል።

09 November 2021, 16:39