ፈልግ

በአፍጋኒስታን የሚገኝ የታሊባን ሠራዊት በአፍጋኒስታን የሚገኝ የታሊባን ሠራዊት 

በአፍጋኒስታን የሚቋቋመው አዲስ መንግሥት ከኢራን እስላማዊ መንግሥት ጋር ይመሳሰላል ተባለ

አፍጋኒስታን ከውጭ አገራት በተለይም ከአሜሪካ በኩል ከሚደርስባት ተጽዕኖ ነጻ ከወጣች በኋላ አገሪቱን ለማስተዳደር የሚቋቋም አዲስ መንግሥት ከኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑ ሲ ኤን ኤን የአሜሪካ ዜና ማዕከል ከታማኝ ምንጭ ያገኘውን መረጃ በመጥቀስ ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አሜሪካ በአፍጋኒስታን የሚገኙ ሰራዊቶቿን በሙሉ ካስወጣች በኋላ ታሊባኖች አገሪቱ የምትተዳደርበትን አዲስ ሥርዓት በማርቀቅ ሂደት ላይ መሆናቸው ታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ዴቪድ ሳሶሊ፣ አውሮፓ ለአፍጋኒስታን ስደተኞች በሰጠችው ምላሽ ቅሬታ የተሰማቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በኳታር መዲና ዶሃ ውስጥ በእንግሊዝ መንግሥት እና በታሊባኖች መካከል ውይይት መጀመሩ ታውቋል። የቦሪስ ጆንሰን መንግሥት ፍላጎት በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚገኙ የእንግሊዝ ዜጎች እና ተባባሪ አፍጋኒስታዊያን ከአገሩ በሰላም የሚወጡበትን መስመር ታሊባኖች እንዲያመቻቹ የሚል መሆኑ ታውቋል። አሜሪካ በአፍጋኒታን የሚገኙ ሰራዊቶቿን ሙሉ በሙሉ ያስወጣች ሲሆን እንግሊዝ ግን የሚቀሯት ዜጎች ያላት መሆኑ ተገልጿል። ሆኖም የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ዴቪድ ሳሶሊ፣ በስሎቬኒያ ብሌድ ከተማ በተካሄደው የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ስትራቴጂካዊ መድረክ ላይ ባሰሙት ንግግር፣  የአውሮፓ ኅብረት የመረጋጋት ፣ የሰላምና የልማት እርምጃዎችን መውሰድ እንዲችል ድምፁን ማሰማት አለበት ብለዋል።

የኢራን ሞዴል

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታሊባኖች አፍጋኒስታንን ለመምራት በማዘጋጀት ላይ የሚገኙት መንግሥት ከኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑ ተነግሯል። ሲኤንኤን የዜና ማዕከል ከታማኝ ምንጭ አገኘሁ ባለው መረጃው፣ ሂባቱላህ አኽውንድዛዳ የአፍጋኒስታን ከፍተኛ መሪ በመሆን እውቅና የሚሰጣቸው መሆኑን ገልጿል። በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የሚኖረው ሃይማኖታዊ ሥልጣን፣ አኩንድዛዳ የፖለቲካ መስመሩን የመወሰን ፣ ሕጎቹን የመሰረዝ አልፎ ተርፎም ፕሬዚዳንቱን የማስወገድ ኃይል እንዲኖራቸው ያደርጋል ተብሏል። የአገሪቱ ከፍተኛው መሪ የሚሆነው በሁሉም የመንግሥት ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ያለው ሲሆን፣ ከ 2016 ዓ. ም. ጀምሮ የታሊባን እንቅስቃሴን የመሩት አኩንድዛዳ በዋናነት ከካንዳሃር ክፍለ ሀገር ሆነው አፍጋኒስታንን ይመራሉ ተብሏል።

02 September 2021, 16:25