ፈልግ

በፈረንሳይ ውስጥ የተፈጸመ የአባ ኦሊቨር ግድያ በፈረንሳይ ውስጥ የተፈጸመ የአባ ኦሊቨር ግድያ 

ፕሬዚደንት አማኑኤል ማክሮን፣ በፈረንሳይ በተገደሉ ካኅን የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አማኑኤል ማክሮን በፈረንሳይ ውስጥ በተገደሉት ካቶሊካዊ ካህን የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው ለአገሪቱ ካቶሊካዊ ምዕመናን በሙሉ መጽናናትን ተመኝተውላቸዋል። ከአንድ ግለሰብ በተሰነዘረባቸው ጥቃት ነሐሴ 3/2013 ዓ. ም የተገደሉት አባ ኦሊቨር ማየር በፈረንሳይ የሞንትፎርት ዓለም አቀፍ ሚስዮናውያን ማኅበር አባል መሆናቸው ታውቋል። አባ ኦሊቨር ማየር በቫንዴያ በሚገኝ የቅዱስ-ሎረንስ-ሱር ሴቭሬ ገዳም ውስጥ የአውራጃው የበላይ አለቃ ሆነው በማገልገል ላይ እንደነበሩ ታውቋል። አባ ኦሊቨር ማየርን የገደለው ግለሰብ በፈረንሳይ ውስጥ በሚገኝ የናንትስ ካቴድራል ላይ ባለፈው ዓመት የእሳት ቃጠሎን በማድረስ ክስ የቀረበበት ግለሰብ መሆኑ ሲታወስ፣ በአባ ኦሊቨር ላይም ግድያ መፈጸሙን አምኗል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሞንትፎርት ዓለም አቀፍ ሚስዮናውያን ማኅበር አባል እና በፈረንሳይ ውስጥ በቫንዴያ አውራጃ ሥር ለሚገኝ ማኅበራቸው ጠቅላይ አለቃ ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ታውቋል። ግድያውን እንደፈጸመ በቀዳሚነት የተጠረጠረው ግለ ሰብ አማኑኤል አባዪሰንጋ የተባለ የ40 ዓመት ጎልማሳ የሯንዳ ተወላጅ መሆኑ ታውቋል። ግለ ሰቡ ወንጀል መፈጸሙን በማመን ወደ ፖሊስ ቀርቦ እጅ መስጠቱ ታውቋል። ይህ ግለ ሰብ እ. አ. አ ሐምሌ ወር 2020 ዓ. ም. በፈረንሳይ ውስጥ በናንትስ ካቴድራል ላይ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ማድረሱ ታውቆ ችሎቱ በሰጠው ቀጠሮ መሠረት እ. አ. አ. በ 2022 ዓ. ም. ፍርድ ቤት ሊቀርብ በመጠባበቅ ላይ መሆኑ ታውቋል።

የፈረንሳይ ቤተክርስቲያን የተሰማት ሐዘን

የፈረንሳይ ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ አቡነ ኤሪክ ዴ ሙላ ቦፎ በቲዊተር ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው በኩል ባስተላለፉት የሐዘን መግለጫ መልዕክት፣ ለአባ ኦሊቨር ቤተሰብ እና ለማኅበራቸው አባላት በሙሉ መጽናናትን ተመኝተው በጸሎት የሚተባበሩ ማሆናቸውን ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ኤሪክ፣ አባ ኦሊቨርን ሲያስታውሱ ሕይወታቸውን በሙሉ ኢየሱስን ሲከተሉ እንደኖሩ፣ በሰዎች መካከል ልዩነት ሳያደርጉ ሁሉንም ተቀብለው ሲያስተናግዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል። በግድያው ድንጋጤ ለተሰማቸው በሙሉ፣ ግድያውን ለፈጸመውም ሳይቀር ጸሎት የሚያደርጉ መሆኑን ገልጸዋል። በአባ ኦሊቨር ግድያ ሐዘን የተሰማቸው የሞንትፎርት ዓለም አቀፍ ሚስዮናውያን ማኅበር ጠቅላይ አለቃ ክቡር አባ ሳንቲኖ ብሬምቢላ በበኩላቸው ፣ አባ ኦሊቨር፣ ትጉህ ካህን፣ ገዳማዊ እና ሚሲዮናዊ እንደነበሩ ገልጸው፣ በማኅበር ሕይወት ከፍተኛ መንፈሳዊነትን በመላበስ እና የማኅበራቸው መሥራች የሆነውን የሉዊ ማሪ ግሪኞ ዴ ሞንፎ ጥልቅ መልዕክት በመከተል ሲመሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። 

የፕሬዚደንት ማክሮን እና የመንግሥታቸው መልዕክት

የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ አማኑኤል ማክሮን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ዣን ካስቴክስ ለመላው የፈረንሳይ ካቶሊካዊ ምዕመናን እና ለሞንትፎርት ገዳማዊያን ማኅበር በላኩት የሐዘን መግለጫ መልዕክታቸው መጽናናትን ተመኝተው ከጎናቸው መሆናቸውን ገልጸዋል። ክቡር አቶ አማኑኤል ማክሮን በቲዊተር ማኅበርዊ መገናኛ መስመራቸው እንደገለጹት፣ አባ ኦሊቨር ትህትና እና ቸርነት በተሞላ አቀራረብ ለሁሉም ሰው ልግስናን እና ፍቅርን በተግባር ሲገልጹ መኖራቸውን አስታውሰው፣ በእምነታቸው የጸኑትን መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ብለዋል። የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ዣን ካስቴክስ ከሞንትፎርት ማኅበር ገዳማዊያን ጋር ያደረጉትን ስብሰባ ባጠቃለሉበት ጊዜ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በአባ ኦሊቨር ላይ የተፈጸመውን የጥላቻ ተግባር ግልፅ ማድረግ እንፈልጋለን ብለው፣ በካህኑ ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል በፈረንሣይ ላይ እንደተፈጸመ እንቆጠረዋለን ብለዋል።

በፈረንሣይ ጉዳት የደረሰባቸው ካህናት እና ገዳማዊያን

ከዚህ በፊት በፈረንሣይ ውስጥ በካኅናት እና በገዳማዊያን ላይ ያነጣጠሩ በርካታ አሳዛኝ ጉዳቶች ሲፈጸሙ ታይተዋል። እ. አ. አ ሐምሌ 26/2016 ዓ. ም የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎታቸውን ሲያሳርጉ በነበሩ በአባ ዣች ሐመል ላይ ግድያ መፈጸሙ ይታወሳል። ግድያው ከፈረንሳይ አብዮት በኋላ የተፈጸመ የመጀመሪያ ወንጀል መሆኑን ተነግሯል። ከአባ ዣክ ሐመል ግድያ አስቀድሞ በፈረንሳይ የሉርድ ሀገረ ስብከት ካህን የነበሩት አባ ዣን ሉክ ካብ እ. አ. አ ግንቦት 11/1991 ዓ. ም. መገደላቸው ይታወሳል። በቱል ሀገረ ስብከትም እ. አ. አ ጥቅምት 26/2009 ዓ. ም አባ ሉዊስ ዡሶም የተባሉ የኤግልቶን ቁምስና መሪ ካህን መገደላቸው ይታወሳል። እ. አ. አ ነሐሴ 16/2005 ዓ. ም. መንፈሳዊ ተጓዦች ለጸሎት በተሰበሰቡበት ቤተክርስቲያን ውስጥ የታይዜ ማኅበረሰብ መሥራች የሆኑት ወንድም ሮጀር ሹትዝ መገደላቸው ይታወሳል።

10 August 2021, 15:46