ፈልግ

የባርነት ሥርዓት የሚገልጽ የፍራንሷ አውግስት ቢያርድ የቅብ ስዕል እ. አ. አ 1840   የባርነት ሥርዓት የሚገልጽ የፍራንሷ አውግስት ቢያርድ የቅብ ስዕል እ. አ. አ 1840  

የጭቆና አገዛዝ ተወግዷል ቢባልም አዲስ የጭቆና ሥርዓት መዘርጋቱ ተገለጸ

ዛሬ ነሐሴ 17/2013 ዓ. ም የጭቆና አገዛዝ የተገረሰሰበት ዓለም አቀፍ ቀን በመላው ዓለም ታስቦ መዋሉ ታውቋል። ሥርዓቱን በመቃወም የካሬቢያን አገር በሆነችው ሳንዶሚንጎ ከ230 ዓመት በፊት ከፍተኛ አብዮት መካሄዱ ይታወሳል። ያም ሆኖ ግን ዛሬ መልኩን የለወጠ የጭቆና ሥርዓት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መስፋፋቱ በርካታ ሰዎችን ለብዝበዛ እና ለስቃይ ሕይወት መዳረጉ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት ታስቦ የዋለው ዓለም አቀፍ ቀን ዋና ዓላማ፣ ሥርዓቱ በሰዎች ሕይወት ላይ ያስከተላቸውን ማኅበራዊ ችግሮችን ከኣማስተወስ በተጨማሪ እ. አ. አ ነሐሴ 22 እና 23/1791 ዓ. ም የተፈጸመውን የባሪያ ንግድ ለማስታወስ መሆኑ ታውቋል። በእነዚያ ታሪካዊ ቀናት ውስጥ የላቲን አሜሪካ ደሴቶች በሆኑት በሳን ዶሚንጎ፣ በሄይቲ እና በዶሚኒካን ሪፓብሊክ የተቀሰቀሰውን ዓመጽ ተከትሎ ሥርዓቱን ለማስወገድ የተካሄደውን ትግል ለማስታወስ መሆኑ ታውቋል።

የባርነት ሥርዓት ትልቅ ወንጀል ነው

በሦስቱ የደቡብ አሜሪካ ደሴቶች የተቀሰቀሰው የጭቆና ቀንበር ተቃውሞ በታሪክ ጥቁር ምልክት ትቶ ያለፈ ሲሆን በሥርዓቱ ወቅት በርካታ ሰዎች፣ ሴቶች እና ሕጻናት ለግብይት የቀረቡበት አስከፊ ሥርዓት እንደነበር ይታወሳል። ከ15ኛ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣት አፍሪካዊያን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተነስተው ወደ ላቲን አሜሪካ እና ሰሜን አሜሪካ የተወሰዱበት፣ በባሕር ላይ ጉዞም ከፈተኛ ስቃይ ያዩበት አጋጣሚ መሆኑ ይታወሳል። ከእነዚህ መካከል ብዙዎች ለሞት የተዳረጉበት እና ከባድ የጉልበት ሥራን እንዲሰሩ ተገድደው ጉልበታቸው የተበዘበዘበት መሆኑ ይታወሳል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ ሁለተኛ እ. አ. አ በ1462 ዓ. ም. በዛሬዋ ጊኒ ቢሳው ለሚገኙ ጳጳስ በጻፉት መልዕክታቸው፣ የባርነት ሥርዓት ትልቅ ወንጀል ነው ማለታቸው ይታወሳል።

አሳፋሪ ንግድ ሰለባዎች

ከአፍሪካ አህጉር ጀምሮ እስከ ላቲን አሜሪካ አገሮች ከፍተኛ ቁስልን ያስከተለው የጭቆና አገዛዝ ሥርዓት ብዙዎችን ለስቃይ መዳረጉ ይታወሳል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በሴነጋል ባደረጉበት ወቅት ለታሪክ የተቀመጡ የባርነት ሥርዓት ቤቶችን መጎብኘታቸው ይታወሳል። በወቅቱ በነበረው የጭቆና ቀንበር ሥርዓት ወቅት አፍሪካዊያን ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት በእነዚያ ጠባብ ቤቶች ውስጥ ታፍነው እንዲቀመጡ መገደዳቸው ተስተውሏል። ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት በግዞት ይመጡ የነበሩ ሰዎች የሚቀመጡባት የጎሪ ደሴት ታሪክ ባሁኑ ጊዜ በውጭ አገር በሚገኙ አፍሪቃዊያን አዕምሮ ዘወትር የሚታወስ መሆኑ ታውቋል።

አዲስ የጭቆና ሥርዓት

በአፍሪካ አገሮች ውስጥ አስከፊው የጭቆና ሥርዓት የተገረሰሰ ቢሆንም ዛሬም ቢሆን በተለያዩ የዓለማች ክፍሎች አዳዲስ የጭቆና ሥርዓቶች መኖራቸው መኖራቸውን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መናገራቸው ይታወሳል። እ. አ. አ በ2014 ዓ. ም የጭቆና ሥርዓትን በቃወም የተፈረመውን ሰነድ በማስታወስ ባደረረጉት ንግግር ላይ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የጨቆና ሥርዓትን ለማስቀረት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ከፍተኛ ጥረቶች እየተደረጉ ያለ ቢሆንም አዳዲስ የጭቆና ሥርዓቶች በሰዎች ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ስቃይን በማስከተል ላይ መሆኑን አስታውሰዋል። በሥርዓቱ የመከራ ሕይወት የደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ብዙ ቢሆኑም በተለይ በድህነት ሕይወት ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ የሚያስከትለው ስቃይ ከፍተኛ መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ አስታውሰዋል። በአሁኑ ጊዜ የጭቆና ቀንበር ተሸክመው አስጨናቂ ሕይወት እየመሩ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከአርባ ሚሊዮን በላይ መሆኑን የተለያዩ ምንጮች ጠቁመዋል።      

23 August 2021, 16:41