ፈልግ

የታሊባን ተዋጊዎች ከተሞችንም መቆጣጠር ጀምረዋል የታሊባን ተዋጊዎች ከተሞችንም መቆጣጠር ጀምረዋል 

የታሊባን ተዋጊዎች በአፍጋኒስታን ውስጥ ከተሞችንም መቆጠጣር መጀመራቸው ተነገረ

በአፍጋኒስታን ውስጥ መንግሥትን ለመቀየር የትጥቅ ትግል በማድረግ ላይ የሚገኙ የታሊባን ተዋጊዎች ገጠራማው አካባቢዎችን ብቻ ሳይሆን ትላልቅ ከተሞችንም መቆጠጣር መጀመራቸው ታውቋል። በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ አራት የአንድ አውራጃ ከተሞችን ከተቆጣጠሩ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ከተሞችን ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። በፍጋኒስታን የሚገኙ የታሊባን አማጺ ተዋጊዎች በመጨረሻዎቹ ዓመታት ባካሄዱት ጥቃት የአገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ገጠራማ አካባቢዎችን እና የድንበር አካባቢዎችን በቁጥጥር ስር በማስገባት፣ ወደ ዋና ከተማዋ ካቡል የሚገቡትን እና ከዋና ከተማዋ የሚወጡ ምርቶች መስመር ለመዝጋት ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፍጋኒስታን ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የታሊባን አማጺ ተዋጊዎች ኩንዱዝ የተባለች ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል የምትገኘውን የሳር ኤ ፑል ከተማን ቅዳሜ በቁጥጥራቸው ማስገባታቸው ታውቋል። ይህም ተዋጊዎቹ በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ መቆጣጠር የቻሉትን ከተማዎች ቁጥር ወደ አራት ማድረሱ ታውቋል። የታሊባን አማጺያን፣ እ. አ. አ ከ2016 ዓ. ም ጀምሮ የኒምሩዝ አውራጃ ዋና ከተማ ዛራንጅን ዓርብ ሐምሌ 30/2013 ዓ. ም ምንም ዓነት የመከላል ውጊያ ሳይገጥማቸው መቆጣጠር መቻላቸው ታውቋል። የታሊባን ተዋጊዎች ሐምሌ 1/2013 ዓ. ም ማካሄዱት ውጊያ ሼበርጋን በተባለ አካባቢ በሚገኙ ወህኒ ቤት የሚገኙ እስረኞችን ነጻ ማውጣታቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መዘገባቸው ታውቋል። የኮንዱዝ ከተማን መቆጣጠር መቻላቸውን እንደ ትልቅ ድል የቆጠሩት የታሊባን ተዋጊዎች ከዚህ በፊት እ. አ. አ በ2015 እና ቀጥሎም በ2016 ዓ. ም ለአጭር ጊዜ መቆጣጠራቸው ይታወሳል።

የኩንዱዝ አውራጃ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ መሐመድ ሁሴን ሙጃሂድዛዳ፣ የታሊባን ተዋጊዎች የኩንዱዝ ከተማን ለመያዝ በዙሪያዋ አንድ ሻለቃ የጦር ሰራዊትን ማሰማራቱን ገልጸው አሁን ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በታሊባን ተዋጊዎች እጅ መውደቋን አስረድተዋል። የታሊባን ተዋጊዎች ከተማዋን ለመቆጣጠር ከአካባቢ ሚሊሻዎች ጋር ባደረጉት ውጊያ በከተማዋ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ፣ የንግድ ተቋማት እና ሕንጻዎች በእሳት መቀጣጠላቸውን “ቶሎ” የተሰኘ የመገናኛ አውታር አስታውቋል። የካቡል የመከላከያ ሚኒስትር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የመንግሥት መከላከያ ሠራዊት ከተማዋን ከታሊባን እጅ መልሶ ለመያዝ ውጊያ በማድረግላይ መሆኑን አስታውቋል።

በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ፍርሃት ነግሷል

በደቡባዊው የሄልማን ግዛት ውስጥ ከሚገኝ ከላሽካር ከተማ ማንቂያዎች መድረሳቸው ተሰምቷል። ከአንድ ዓመት በፊት ከተደረገ የመጨረሻው ወታደራዊ ጥቃት በፊት በአካባቢው ጠንካራ የታጣቂዎች ቡድን በመኖሩ ኃይለኛ ጦርነት መካሄዱ ይታወሳል። በላሽካር ጋ የሚገኝ አንድ የዓይን እማኝ፣ የከተማው ነዋሪዎች ቤታቸውን እና ንብረታቸውን በመተው እየወጡ ማሆናቸውን፣ በሆስፒታል የሚገኙ ዜጎች ጭንቅት ውስጥ መግባታቸውን እና የመንግሥት መከላከያ ሠራዊት በትጥቅ በኩል በሚገባ ያልተዘጋጀ መሆኑን ገልጿል።

ከ 20 ዓመታት ጦርነት በኋላ

እ. አ. አ መስከረም 11 ቀን 2001 በኒው ዮርክ እና በዋሽንግተን የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት ተከትሎ የአሜሪካ ወታደሮች አፍጋኒስታንን በተመሳሳይ ዓ. ም መውረራቸው ይታወሳል። ከዚያ በፊት እ. አ. አ ከ1996 – 2001 ዓ. ም ድረስ ጽንፈኛው ቡድን አገሪቱን ሲቆጣጠር መቆየቱ ይታወሳል። በአፍካኒስታን ውስጥ የአልቃይዳ መሪዎችን ከታሊባን በኩል ከለላ ሲደረግላቸው መቆየቱ ይታወሳል። በመሆኑም የታሊባን አገዛዝን ለመጣል የአሜሪካ መንግሥት እ. አ. አ ከጥቅምት ወር 2001 ዓ. ም ጀምሮ ላለፉት 20 ዓመታት ጦርነት ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል።

ከአሜሪካ ለቃ ከመውጣት በስተጀርባ

አሜሪካ አፍጋኒስታንን ለቃ እንድወጣ የታሊባኖች እየበረቱ መምጣት ዋናው ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። በታሊባን እና በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በነበሩ ትራምፕ አስተዳደር መካከል ሰፊ ድርድር ከተደረገ በኋላ አሜሪካ አፍጋኒስታንን ለቃ እንድትወጣ እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም የካቲት ወር ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል። የአፍጋኒስታን ማዕከላዊ መንግሥት በእነዚያ ድርድሮች ውስጥ ያልተሳተፈ ሲሆን፣ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በስምምነቱ መሠረት የአሜሪካ ወታደሮች እስከ መስከረም 11/2021 ድረስ ሙሉ በሙሉ ከአፍጋኒስታን የሚወጡ መሆኑን አስታውቀዋል።

09 August 2021, 14:22