ፈልግ

ታላቁ የኢትዮጲያ የሕዳሴ ግድብ ታላቁ የኢትዮጲያ የሕዳሴ ግድብ  

ታላቁ የኢትዮጲያ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ህልም፣ ምኞት እና ተስፋዎች ዙሪያ ላይ ያለው ሚና!

በእንግሊዘኛው አህጽሮተ ቃል “Gerd” "Grand Ethiopian Renaissance Dam" (ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ”) በመባል የሚጠራው ኢትዮጲያ በልጆቿ ላብ እና ጥሪት እየገነባች የምትገኘው የአፍሪካን አህጉር ዳግም የመወለድ ፍላጎትን የሚያመለክት ግድብ ሁለተኛ ሙሌቱን በቅርቡ ማጠናቀቁ ይታወቃል። ይህ በብዙ ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ መያዝ የሚችለው እና የኢትዮጲያን እና የጎሬቤት አገሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት እንደ ሚያሟላ ከፍተኛ ተስፋ የሰነቀው ግድብ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባሻገር በአፍሪካ አህጉር በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የኢትዮጲያን ተሰሚነት እና የኃይል ሚዛን የሚያስጠብቅ ግድብ እንደ ሚሆን “Osservatore Romano” በመባል የሚታወቀው በቅድስት መንበር እየታተመ የሚወጣው እለታዊ ጋዜጣ በፊት ገጹ ላይ በሐምሌ 13/2013 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ አስነብቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በኢትዮጵያ ከፍታማ ስፍራ ላይ ከሚገኘው የውሃ ምንጮች የሚመነጨው የአባይ ወንዝ ከዚያ ስፍራ የሚነሳ በአገሪቷ በኢትዮጲያ ካሉት ታላላቅ የውሃ ሀብቶች አንዱ ሲሆን በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ አንድ እየበቀለ የሚገኝ  ዘር ሲሆን ይህ ግዙፍ ግድብ ለመላው የአገሪቷ ሕዝብ ከፍተኛ የሆነ ተስፋ ይዞ የመጣ ግድብ ነው። ይህ ታላቁ የኢትዮጲያ የሕዳሴ ግድብ ከ110 ሚሊዮን በላይ የሚቆጠረውን ኢትዮጵያውያንን የመብራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን በተጨማሪም ኢትዮጲያ ለዘመናት በድቅር በመመታቷ የተነሳ ከውጪ አገር በግዢ እና በርዳታ መልክ የምታስገባውን እሕል በማቆ የአገሪቷን ሕዝብ መመገብ የሚያስችሉ ዘዴዎችን በመጠቀም የአገሪቷን ሕዝብ ለመመገብ ያላትን ቁርጠኝነት እና ሕልም እውን የሚያደርግ ግድብ እንደ ሚሆን ጋዜጣው ዘግቧል።

በቅርቡ የአሜሪካ የግብርና መምሪያ ድርጅት ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያ ጥራት ያለው እህል ለራሷ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ለሚገኙ ሀገሮች ጭምር የምግብ እሕሎችን በጥሩ ዋጋ የማምረት እና የማቅረብ አቅም እንዳላት የገለጸው “Osservatore Romano” በመባል የሚታወቀው ጋዜጣ ሕዝቦቿን በመመገብ፣ በመንከባከብ፣ በእድገት ማማ ላይ እንዲወጡ በማደረግ አገሪቷ ዳግም ውልደቷን እንደ ምታረጋግጥ ያለውን ተስፋ ጋዜጣው አክሎ ገልጿል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኙ ፋብሪካዎች እና የእንዱስትሪ መንድሮች ሳይቀር ሁሉም  በመዲናዋ አዲስ አበባ ዙሪያ ነው ያሉት ማለት ይቻላል ከአቅማቸው በ 50% ብቻ ተግባራቸውን እያከናወኑ እንደ ሚገኙ ጋዜጣው የዘገበ ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት በመብራት ኃይል እጥረት እንደ ሆነ አክሎ ዘግቧል። በተጨማሪም ኢትዮጲያ ለባለፉት በርካታ አመታት ያህል ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ከሚሰጡት እርዳታዎች እና መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገዝቶ ወደ አገር የሚያስገባቸውን ምግቦች በአገር ውስጥ በሚመረት እሕል ለመተካት የሚደርገውን ጥረት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የበኩሉን አስተዋጾ እንደ ሚያደርግ ይጠበቃል። 

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጲያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለሁለት ተከታታይ ዓመት የውሃ ሙሌት እንዳከናወነ የገለጸው “Osservatore Romano” የተሰኘው ጋዜጣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጲያ ያለውን የዝናብ ወቅት በመጠቀም ሁለተኛው ሙሌት እንደ ተከናወነ ገልጾ ይህ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ጥማት ለማርካት በማሰብ እየተገነባ የሚገኘው ግድብ የግብጽና የሱዳን ሕልውና ይፈታተናል ተብሎ በመታሰቡ ጉዳዩን ሁለቱ አገራት በቅርቡ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም / ቤት ማቅረባቸው ይታወሳል፣ ጉዳዩም በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል መወሰኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ እንደ ሆነ “Osservatore Romano” የተሰኘው ጋዜጣ አክሎ ገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት ከሳተላይቶች የሚታየው የተፋሰሱ ሁለተኛ ሙሌት “መጠናቀቁን” የኢትዮጵያ የውሃ ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ስለሺ በቀለ ማስታወቃቸውን የገለጸው ጋዜጣው አስራ ሶስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ  500 ሜትር ያህል ቁመት ባለው ግድብ ውስጥ መጠራቀሙን እንደ ገለጹ ያመለከተው ጋዜጣው ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የውሃ ማጠራቀም አቅሙ 73 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ሊደርስ እንደ ሚችል ጋዜጣው አክሎ ገልጿል። ከሁለት ዓመት በፊት ውሃ መያዝ የጀመረው ታላቁ የኢትዮጲያ የሕዳሴ ግድብ በተፋሰሱ እግርጌ ላይ የሚገኙ ሱዳን እና ግብጽ አሳሪ ስምምነት እንዲደረግ እያደረጉ የሚገኙትን ውትወታ እና ጫና ተቋቁሞ እውን እየሆነ ያለ ታላቅ ፕሮጀክት እንደ ሆነም ጋዜጣው አክሎ ገልጿል።

ለወደፊቱ አህጉሪቱ በዚህ ትልቁ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ላይ በመመርኮዝ የኢንዱስትሪ ልማት ፕሮጀክት ከማሳለጥ ባሻገር ስሙ የሚጠራው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተብሎ እንደ ሆነ የዘገበው “Osservatore Romano” የተሰኘ ጋዜጣ አክሎ የገለጸ ሲሆን አሁን በአፍሪካ ቀንድ ላይ እውን እየሆነ ያለ ፕሮጄክት እንደ ሆነም ተገልጿል። ትልቁ የውሃ ሀብት የሆነው የአባይ ወንዝ ከነጩ ናይል ጋር በመቀላቀል ታላቁን ናይል በሱዳን ይመሰርታል። በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጲያ እየገነባች የሚትገኘው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተመለከተ ከታች የሚገኙ የተፋሳሽ አገሮች ለባለፉት አስርት አመታት ያህል ድርድሮችን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን እ.አ.አ በ2015 ዓ.ም በሶስቱ የተፋሳሽ አገራት መካከል ስምምነት የተፈረመ ሲሆን በመጨረሻም ኢትዮጲያ ሁለተኛ የውሃ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት አሳሪ ስምምነቶችን በቅድሚያ መፈረም አለባት በሚል ክስ ጉዳዩ እስከ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም / ቤት ድረስ ድርሶ እንደ ነበረ የገለጸው ጋዜጣው ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ሕብረት እንደ ተመለሰ አክሎ ገልጿል። በአሁኑ ወቅት ታላቁ የኢትዮጲያ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ሙሌት በመጠናቀቁ የተነሳ ከጥቂት ወራት በኋላ ግድቡ ሁለት ተርባይኖችን ተጠቅሞ የመብራት ኃይል ማምረት እንደ ሚጀምር የአገሪቷ መንግሥት መግለጹን ጋዜጣው አስነብቧል።

21 July 2021, 10:56