ጆርጅ ፍሎይድን የገደለው ፖሊስ የ22 ዓመት ከግማሽ በእስር እንዲቀጣ ተበየነበት
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በሚኒያፖሊስ ግዛት እና በተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ተቃውሞን ማስነሳቱ እና ለከፍተኛ የንብረት መውደም ምክንያት መሆኑ ይታወሳል። በወቅቱ በተቀሰቀሰው አመጽ የሰው ሕይወት መጥፋቱ እና ሰዎች በጽኑ መቁሰላቸው ይታወሳል።
ከፍተኛው ቅጣት እንዲጣልበት ተጠይቋል
በሰሜን አሜሪካ፣ ሚኒያፖሊስ ፍርድ ቤቱ የሚካሄደውን የፍርድ ሂደት ይከታተሉ የነበሩ፣ በአስራዎቹ የሚቆጠሩ ሰዎች “የጥቁር ነፍስ ዋጋ አለው” እያሉ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ታይተዋል። የጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰቦች እና ጠበቆች ጥፋተኛው ቢያንስ የሰላሳ ዓመት ቅጣት እንዲበየንበት መጠየቃቸው ታውቋል። ጥፋተኛው ፍርዱን ያገኘው ጥፋተኛነቱ ከታወቀ ከሁለት ወራት በኋላ መሆኑ ታውቋል። የዴሪክ ሾቬን ጠበቆች አስቀድመው አጥፊው በነጻ የሚለቀቅበትን መንገድ ከፈለጉ በኋላ ቀጥለው ቅጣቱን ዝቅተኛ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል ተብሏል። ዳኛው ፍርዱን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት ፍርዱ የተሰጠው በስሜት ሳይሆን በጥፋቱ ልክ መሆኑን በሥፍራው ለነበሩት በሙሉ አስታውቀው፣ በ22 ገጾች ላይ የክስ ማህደር ለፍርዱ በቂ ምክንያቶችን የያዘ መሆኑንም አስረድተዋል።
ጥፋተኛው ፖሊስ ለፍሎይድ ቤተሰብ ሀዘኑን ገልጿል
ጆርጅ ፍሎይድን ትንፋሽ በማሳጣት ለሞት ያበቃው የግዛቲቱ ፖሊስ ዴሪክ ሾቬን ለጆርጅ ቤተሰብ ሐዘኑን የገለጸ ሲሆን ወደ ፍርድ ቤቱ ከመምጣቱ በፊት ለሁለት ዓመታት ቅም እስረኛ በመሆን ከሰው ተለይቶ እንዲቆይ መደረጉ ታውቋል። በፍርድ ቤቱ አዳራሽ በተገጠመው የቪዲዮ መገናኛ መስመር የጆርጅ ፍሎይድ የሰባት ዓመት ልጅ የምትወደውአባቷን ያጣች መሆኑን ገልጻለች።
ጆ ባይደን የተሰጠው ፍርዱ ተገቢ ነው
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ከግምት ውስጥ የተካተቱትን ሁሉንም ሁኔታዎች ባላውቅም ግን ፍርዱ ተገቢ ይመስላል ብለዋል።