ፈልግ

ስደተኞች የሜዲቴራኒያን ባሕር ለማቁረጥ የሚገለገሉበት የላስቲክ ጀልባ     ስደተኞች የሜዲቴራኒያን ባሕር ለማቁረጥ የሚገለገሉበት የላስቲክ ጀልባ  

በሜዲቴራኒያን ባሕር በስደተኞች ላይ የደረሰው የሞት አደጋ ድንገተኛ አለመሆኑ ተገለጸ

በቅርቡ በሜዲቴራኒያን ባሕር በስደተኞች ላይ የደረሰው የሞት አደጋ በጣሊያን እና በተቀሩት የአውሮፓ አገሮች ዘንድ የሕሊና ወቀሳን የሚያስከትል መሆኑ ታውቋል። አደጋው ድንገተኛ አይደለም ያለው “ኦፔን አርምስ” የተሰኝ የባሕር ላይ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅት ዘገባ በሊቢያ የባሕር ጠረፍ ላይ ወድቀው የተገኙን የሕጻናት አስከሬን ምስል ያሳየ ሲሆን፣ በሕጻናቱ ላይ የደረሰው የሞት አደጋ የአውሮፓ አገሮች ለዘብተኝነት ውጤት መሆኑን አስታውቋል። ከአደጋው በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ “ለስደተኞች በሚደረግ የዕርዳታ አቅርቦት ላይ ማሻሻያዎች ሊደረግበት ያስፈልጋል” ብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ክቡር አቶ ሚኬለ ባክለት ለሊቢያ መንግሥት፣ ለአውሮፓ ኅብረት እና አባል አገራት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሜዲቴራኒያን ባሕር በሰደተኞች ላይ የሚደርሰውን የሞት አደጋ ለመከላከል አገራቱ ሰብዓዊ ሕሊና ሊኖራቸው የገባል ብለው፣ ስደተኞቹ መሠረታዊ የሆነውን ሰብዓዊ ክብርን የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑን ገልጸው፣ ከሁሉም በላይ መብታቸው በሕይወት መኖር ነው ብለዋል። ኮሚሽነሩ አክለውም የሚያሳዝነው ስደተኞችን በባሕር ላይ ከሚያጋጥማቸው የሞት እና የስቃይ አደጋዎች መካከል አብዛኛዎቹን መከላከል ይቻል ነበር ብለው፣ በባሕር ላይ ስደተኞችን በየዓመቱ አደጋ የሚያጋጥማቸው የነፍስ አድን ዕርዳታ ዘግይቶ ስለሚደርስ ወይም ፈጽሞ ሳይደርሳቸው ሲቀር ነው ብለዋል።

በሊቢያ ዛዋራ ወደብ ላይ የተገኙት ሕጻናት

በቤልጄም ብራክሰል ከተማ በተካሄደው የአውሮፓ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተቀመጡት በጣሊያን ሪፓብሊክ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ማርዮ ድራጊ፣ በሊቢያ የባሕር ጠረፍ ላይ ወድቀው የተገኙ የሦስት ሕጻናት አስከሬን ምስል ተመልክተው ሐዘናቸውን ከገለጹ በኋላ እንደተናገሩት፣ የአውሮፓ ኅብረት የስደተኞችን መከራ በመመልከት ውጤታማ የሆነ ፍትሃዊ እና ሰብዓዊ ዕርዳታን ማቅረብ ይኖርበታል ብለው፣ የኅብረቱ አባል አገሮች የጣሊያን መንግሥትን መርዳት እንዳለባቸው ጠይቀዋል።

ስደተኞች ተገቢ ጥበቃ አልተደረገላቸውም

የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በሜዲቴራኒያን ባሕር ለስደተኞች የሚደረጉ የነፍስ አድን ዕርዳታን እና የሕይወት ጥበቃ አገልግሎቶችን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርቱ፣ በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ ለስደተኞች በቂ ዕርዳታ የማይደረግላቸው የሊቢያ መንግሥት፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የተለያዩ ተቋማት እና ተዋናይ ድርጅቶች በሚወስዷቸው ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ምክንያት መሆኑን አስረድቷል። የአውሮፓዊያኑ 2019/2020 ዓ. ም ሪፖርቱ አክሎም በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ በስደተኞች ላይ የሚደርስ አደጋ የጨመረው፣ የአውሮፓ ኅብረት አገራት የባሕር ላይ ዕርዳታን በመቀነሳቸው እና በነፍስ አድን አገልግሎት ላይ የተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አገልግሎታቸውን እንዳያቀርቡ በመታገዳቸው ምክንያት መሆኑን አስታውቋል።

“አሳፋሪ ተግባር ነው”

ባለፈው 2020 የአውሮፓዊያን ዓመት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በባሕር ላይ የሚሞቱ ነፍሳትን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በባሕር ላይ የዕርዳታ አግልግሎትን ሳያገኙ ቀርተው በርካታ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸ የሚያሳፍር ነው ብለው፣ በዚሁ መልዕክታቸው በባሕር ጉዞ ላይ ለሚገኙት ስደተኞች መጸለይ እንደሚገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል።         

የሜዲቴራኒያን ባሕር የሞት አደጋ ድንገተኛ አይደለም

በሜዲቴራኒያን ባሕር በስደተኞች ላይ የደረሰው የሞት አደጋ ድንገተኛ አለመሆኑ የገለጹት፣ በጣሊያን “የኦፔን አርምስ” ቃል አቀባይ ቬሮኒካ አልፎንሲ በዘንድሮ የአውሮፓዊያኑ ዓመት ብቻ በባሕር ላይ አደጋ የሞቱት ስደተኞች ቁጥር ከስድስት መቶ በላይ መሆኑን ገልጸው፣ አውሮፓ ድንበሮቹን የሰብዓዊ መብቶች ደንብን ከሚጥሱ አገሮች ውጭ ማድረጉ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዘንድ የታወቀ መሆኑን አስረድተዋል። ስደተኞችን በባሕር ላይ የሚደርስ አሰቃቂ አደጋ እና ሰብዓዊ መብታቸው መጣስ ከአገሮች አለመተባበር፣ የአውሮፓ ኅብረት ትክክለኛ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ካለመውሰድ እና የጣሊያን መንግሥት ለሊቢያ ሚሊሻዎች በሚያደርገው የገንዘብ ዕርዳታ ምክንያት መሆኑን አስረድተው፣ በሜዲቴራኒያን ባሕር በስደተኞች ላይ የደረሰው የሞት አደጋ ድንገተኛ ሳይሆን የአውሮፓ ሕብረት ምርጫ እና ፍላጎት መሆኑን ገልጸዋል።       

27 May 2021, 16:28