ፈልግ

ሕጻናት ንጹሕ ውሃን በቀላሉ አያገኝም ሕጻናት ንጹሕ ውሃን በቀላሉ አያገኝም  

ከአምስት ሕጻናት መካከል አንዱ ለዕለት የሚበቃ ንጹሕ ውሃን አያገኝም ተባለ

በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” ፣ “በቂ ውሃን ለሁሉ ማድረስ” በሚለው ዓለም አቀፍ ዕርዳታ አቅርቦት መርሃ ግብሩ መሠረት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ሕጻናት ዕርዳታን ለማድረግ በመሥራት ላይ መሆኑን ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” አዲስ ባወጣው ሪፖርቱ በዓለማችን ውስጥ ከ1.42 ቢሊዮን በላይ ሰዎች፣ ከእነዚህም መካከል 450 ሚሊዮን ሕጻናት ከፍተኛ የውሃ እጥረት በሚገኙባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን አስታውቋል። ይህ ማለት ደግሞ በዓለማችን ውስጥ ከአምስት ሕጻናት መካከል አንዱ ለዕለታዊ ፍጆታ የሚሆን በቂ ውሃ አያገኝም ማለት ነው። “በቂ ውሃን ለሁሉ ማድረስ” የሚለው ዓለም አቀፍ ዕርዳታ አቅርቦት መርሃ ግብር፣ ለሕዝቦች የሚቀርብ የውሃ መጠን ማነሱ በቂ ውሃን ለማቅረብ ከሚደረግ አገልግሎት የሚበጥ ሆኖ ተገኝቷል። የውሃ እጥረት በሚታይባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ዝቅተኛ በሆነ የውሃ አቅርቦት ወይም ከግማሽ ሰዓት በላይ ተጉዘው ውሃን የሚያገኙ መሆኑ ታውቋል።

ሕጻናት ከፍተኛ የችግሩ ተጠቂዎች ናቸው

የውሃ እጥረት አጋጥሞናል ሉት፣ በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ሄንሪታ ፎር፣ ችግሩን የከፋ የሚያደርገው የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን አብራርተዋል። በዚህ መካከል በተለይ ሕጻናት የችግሩ ዋነኛ ተጠቂዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ የውሃ ጉድጓዶች ሲደርቁ ሕጻናት ከትምህርት ቤት ቀርተው ውሃ ፍለጋ የሚንከራተቱ መሆኑን አስረድተው፣ ድርቅ በጨመረ ቁጥር ሕጻናት በቂ እና ተመጣጣኝ ምግብ አያገኙም ብለዋል። ኃይለኛ ዝናብ ዘንቦ ጎርፍ የሚመጣ ከሆነም ሕጻናት በውሃ ወለድ በሽታዎች የሚታመሙ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በ80 አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሕጻናት ከፍተኛ የውሃ እጥረት በሚታይባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሲሆን፣ በተለይም በምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ አገሮች ውስጥ ከሚኖሩት ሕጻናት መካከል 58 ከመቶ የሚሆኑ ሕጻናት በየቀኑ በቂ ውሃን አያገኙም ተብሏል። በተቀሩት የዓለማችን ክፍሎች፣ በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ 31 ከመቶ፣ በደቡብ እስያ 25 ከመቶ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች 23 ከመቶ የሚሆኑ ሕጻናት በቂ ውሃን የማያገኙ መሆኑ ተነግሯል። ደቡብ እስያ በቂ ውሃን የማያገኙ በርካታ ሕጻናት የሚገኝበት የዓለማችን ክፍል ሲሆን በቁጥር ሲተመን ከ155 ሚሊዮን በላይ መሆናቸው ታውቋል።

በ 37 ሀገሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ

የውሃ እጥረት የሚታይባቸው የ37 አገሮች ሕጻናት “በቂ ውሃ ለሁሉ ይድረስ” የሚል አስቸኳይ ዓለም አቀፍ መርሃ ግብር በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ መሆኑ ታውቋል። የውሃ እጥረት ከሚታይባቸው 37 አገሮች መካከል አፍጋኒስታን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኢትዮጵያ፣ ሃይቲ፣ ኬንያ፣ ኒጀር፣ ናይጄሪያ፣ ፓክስታን፣ ፓፗ ኒው ጊኒ፣ ሱዳን፣ ታንዛንያ እና የመን የሚገኙ መሆኑ ታውቋል። የውሃ መጠን እየቀነሰ እያለ የውሃ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ለዚህም ዋና ምክንያቱ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የሚገኘው የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሞች ዕድገት፣ አላግባብ የሌለው የውሃ አጠቃቀም፣ የአየር ንብረት ለውጥ ያስስከተለው የንጹህ ውሃ መጠን መቀነስ መሆኑ ሲነገር፣ በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት በ2017 (እ.አ.አ) ሪፖርቱ እንዳስታወቀው በ2040 (እ.አ.አ) በዓለማችን ከአራት ሕጻናት መካከል አንዱ ከፍተኛ የውሃ እጥረት በሚታይበት አካባቢ እንደሚኖር ተንበያውን አቅርቧል። በማከልም የውሃ እጥረት ማጋጠሙ በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ በግልጽ የሚታይ መሆኑን ድርጅቱ ገልጾ፣ ለዝቅተኛ የውሃ መጠን ችግር ዋና ምክንያቱ የአየር ንብረት ለውጥ በመከሰቱ ነው ብሏል። በመሆኑም የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ ባሁኑ ወቅት እያንዳንዱ ሕጻን ዘላቂ እና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ የውሃ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል። ጥረቱ የሚያተኩረው ያለውን አቅም በማስተባበር ደህንነቱ የተጠበቀ ፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ዘላቂ የውሃ መጠን ማቅረብ፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና አጠባበቅ አገልግሎቶችን በአስቸኳይ ማቅረብ መሆኑን አስታውቋል።  

20 March 2021, 17:17