ፈልግ

የኢራቅ ምዕመናን በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት የገለጹት ደስታ የኢራቅ ምዕመናን በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት የገለጹት ደስታ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ለውጥ ከግል ሕይወት የሚጀምር መሆን እንዳለበት አስተማሩ።

በባግዳድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እና በምንኩስና ሕይወት የሚኖሩ እህት አናን አልካስ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፣ ቅዱስነታቸው የሰውን ልብ እና አእምሮ የሚለውጡ፣ በአገሪቱ በቁጥር ዝቅተኛ የሆኑ ክርስቲያን ማኅበረሰብንም የሚንከባከቡ ደፋር ሐዋርያዊ አባት ናቸው በማለት ገልጸዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በጦርነት፣ በስደት እና ከአሸባሪዎች በሚሰነዘር ጥቃት ከፍተኛ ውድመት ወደ ደረሰባት ኢራቅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው “ንጹሕ የፍቅር ተግባር” መሆኑን እህት አናን ገልጸዋል። እህት አናን አልካስ የሱፍ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ አብርሃም ምድር ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ድፍረት እንደሚያስፈልግ ገለጸው፣ የእርሳቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ኢራቅን በፍቅር የሚሞላ እና የዜጎችን ልብ በማደስ ድፍረትን የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።    

ቅዱስነታቸው ዘወትር ከእኛ ጋር ናቸው!

ፕሮፌሰር አናን በመቀጠልም “እኛ የኢራቅ ቀደምት ሕዝቦች ነን” ማለት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከእኛ ጋር መሆናቸውን በማስታወስ፣ ምን ያህል በእውነት በዚህች አገር ውስጥ ስር የሰደድን መሆናችንን ማወቅ ይኖርብናል ብለዋል። ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር እንደሚወዱን እናውቃለን ያሉት ፕሮፌሰሯ፣ በጸሎት እና በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር መሆኑን እናውቃለን ብለዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በኢራቅ ውስጥ አለመረጋጋት መኖሩን የገልጹት ፕሮፌሰር አናን፣ ቅዱስነታቸው ለኢራቅ ምዕመናንም እንክብካቤን የሚያደርጉ ታላቅ ሐዋርያዊ አባት ናቸው ብለዋል። አክለውም በኢራቅ የሚገኙ ክርስቲያን ምዕመናን ጥቂት ቢሆኑም እርሳቸው ያስተላልፉት የሰላም፣ የፍትህ እና የእኩልነት መልዕክት በመላው የኢራቅ ሕዝብ ልብ ውስጥ መግባቱን አስረድተዋል።

ለመላው ኢራቃውያን የቀረበ መልእክት

ፕሮፌሰር አናን በሰጡት የግል አስተያየታቸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት “በኢራቅ ምድር የመኖርን ክብር እንድገነዘብ አግዞኛል” ብለው፣ እንደ ፕሮፌሰር ለተማሪዎቻቸው የሚያስተላልፉት መልዕክት ቢኖር “በኅብረት መልካም ማኅበረሰብን መገንባት እንዲችሉ እና ልዩነትን አስወግደው እንደ አንድ ሕዝብ እንዲያድጉ ማገዝ ነው” ብለዋል።

“ለመላው የኢራቅ ሕዝብ ያለኝ መልዕክት ይህ ነው” ያሉት ፕሮፌሰር አናን፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ኢራቅ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በችግሮች መካከል ቢሆንም ፍሬ ያለው ነው ብለዋል። ጉብኝታቸው የኢራቅ ሕዝብ ልብ እንዲለወጥ፣ አዕምሮውም እንደገና ማሰብ እንዲጀምር የሚያደርግ በመሆኑ ከፍተኛ ለውጥን የሚያመጣ መሆኑን አስረድተዋል። “ጥረቱ ከእኛ መጀመር ይኖርበታል” ያሉት ፕሮፌሰሯ፣ ሰላም በሌለበት ፍትህ ሊኖር አይችልም ብለው፣ ለውጡ ከራሳችን መጀመር አለበት በማለት አስተያየታቸውን ገልጸዋል። 

08 March 2021, 13:23