ፈልግ

በኢራቅ ውስጥ ከደረሱት ውድመቶች መካከል በኢራቅ ውስጥ ከደረሱት ውድመቶች መካከል  

የኢራቅን ሕዝብ ሰላም የሰፈነበት የወንድማማችነት ባሕል የናፈቀው መሆኑ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ. ም. ድረስ በኢራቅ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለመጀመር ዓርብ የካቲት 26/2013 ዓ. ም. የሚጓዙ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊት በኢራቅ ሕዝብ መካከል ሰላም እና አንድነት እንዲወርድ በማለት በተለያዩ ጊዜያት ሐዋርያዊ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ መቆየታቸው ይታወሳል። በኢራቅ ውስጥ እ. አ. አ ከ2014 – 2017 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት፣ በአገሪቱ እስላማዊ መንግሥትን ለመመስረት ያለመ እና ለበርካታ ሕይወት መጥፋት እና ንብረት መውደም ምክንያት ሆኖ ማለፉን የሽብር ጥቃት ተንታኝ እና የፖለቲካ መምህር የሆኑት ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢራቅ የተፈጸሙት ጀሃዳዊ የሽብር ጥቃቶች የቅርብ ጊዜ ትዝታዎቻችን ናቸው የሚሉት ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ፣ እ.አ.አ በሰኔ 19/2014 ዓ. ም. በሞሱል ከተማ ራሳቸውን የእስላማዊ መንግሥት መሪ ነኝ ብለው ያሰየሙት አቡ በከር አል ባግዳዲ፣ የሶርያ ሰሜን ምዕራብ ግዛቶችን እና አካባቢ አገሮችን ጨምሮ ምዕራብ ኢራቅን በቁጥጥራቸው ስር ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህ ከሆነ ከሰባት ዓመት በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢራቅ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው እሑድ የካቲት 28/2013 ዓ. ም. ሞሱል ከተማን የሚጎበኙ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው የሞሱል ከተማን በሚጎበኙበት ዕለት፣ እ. አ.  አ. ከ2014 – 2017 ዓ. ም. በተካሄደው የሦስት ዓመት ጦርነት፣ በጀሃዳዊ አሸባሪዎች ሕይወታቸውን ያጡትን በጸሎት የሚያስታውሷቸው መሆኑ ታውቋል።

የሃያኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ

የሽብር ጥቃት ተንታኝ እና የፖለቲካ መምህር የሆኑት ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ በኢራቅ ውስጥ በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች የተፈጸሙት ጥቃቶች በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ የተፈጸሙ መሆናቸውን አስታውሰዋል። “የሞሱል ከተማ በእስላማዊ መንግሥት እጅ መውደቅ” በሚል አርዕስት መጽሐፍ ያሳተሙት ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ፣ መላው የኢራቅ ሕዝብ በአምባገነን አገዛዝ ምክንያት ውስጣዊ ችግሮች ቢኖሩም፣ የወጭ ወራሪ ኃይልን ለመመከት በጋራ መዋጋታቸውን አስታውሰዋል። ኤኮኖሚያዊ ይዘትን ከተላበሰው ከባሕረ ሰላጤው ጦርነት በኋላም ቢሆን በኢራቅ ውስጥ መረጋጋት መጥፋቱን የገልጹት ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ፣ በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣው ሽብርተኝነት የተጀመረው ከጦርነቱ በፊት መሆኑን ገልጸዋል።

እ. አ. አ. የ2003 ጦርነት

እ. አ. አ. በ2003 ዓ. ም. በኢራቅ የተካሄደው ጦርነት ሁኔታዎችን ሙሉ በሙሉ መቀየሩን የሚናገሩት ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ፣ አገሪቱ ስር ለሰደደ የመከፋፈል አደጋ መጋለጧን ተናግረው፣ ምክንያቱን ሲገልጹ፣ ጦርነቱን እንደ ውጭ ኃይል ወረራ ስለተመለከቱት ነው ብለዋል። የውጭ አገር ወራሪ ኃይልን በስፋት የተቃወመው የኢራቅ ሕዝብ፣ ወራሪ ኃይሉ ወደ ኢራቅ እንዲገባ የኢራቅ ሰሜናዊው ግዛት እገዛ መስጠቱ በስፋት ይነገር እንደነበር ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ አስታውሰዋል። ሙሰኝነት በወቅቱ ምን ያህል እንደተስፋፋ ባይታወቅም፣ አገሪቱን ለክፍፍል መዳረጓን አስታውሰዋል።

አክራሪነት መስፋፋት

በኢራቅ ውስጥ የተቀሰቀሰው ግጭት በሲቪል ማኅበረሰብ መካከል ያስከተለው ከባድ መዘዝ መኖሩን የማይክዱት ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ፣ የሽአ እና ሱኒ እምነት ተከታይ የሆነው የኢራቅ ሠራዊት ከኢራን ጋር ጦርነት መግጠሙን አስታውሰው፣ እ. አ. አ. በ2003 ዓ. ም. በሁለቱ አገራት መካከል የተካሄደው ጦርነት በኢራቅ መንግሥት ሠራዊት መካከል አክራሪነትን ማሳደጉን ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ ገልጸዋል። በሠራዊቱ መካከል የተፈጠረው አክራሪነት ከዓመታት በኋላ የሽብር ጥቃቶችን የሚፈጽም ጀሃዳዊ መንግሥት ታጣቂ ሠራዊት እንዲፈጠር መድረጉን አስረድተዋል።

የጦርነቱ መባባስ

በዓመታት መካከል ሁኔታዎች መለወጣቸውን የሚገልጹት ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ እ. አ. አ. በ2013 ዓ. ም. በኢራቅ ውስጥ በሚገኙት የአልቃኢዳ ተዋጊ ኃይላት መካከል ከፍተኛ ለውጦች መታየታቸውን አስታውሰው፣ በጊዜው የሰሜን ኢራቅ ክፍለ ሀገር መሪ የነበሩት አቡ በከር አል ባግዳዲ፣ ዋና መቀመጫውን ሶርያ ውስጥ ላደረገው የአል ቃኢዳ ታጣቂ ኃይል እውቅናን አሳጥተው “አይ ሲ ስ” የተባለ፣ ሶርያን እና ኢራቅን ጨምሮ የአካባቢውን አገሮች የሚገዛ እስላማዊ መንግሥት መመስረታቸውን ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ አስታውሰዋል።

የኢራቅ ሕዝብ

በኢራቅ ውስጥ ዛሬም ቢሆን የእስላማዊ መንግሥት ሺአ ሚሊሻ ታጣቂዎች መኖራቸውን የሚገልጹት ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ፣ ለሕዝቡ በርካታ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንደሚጎድሉ ገልጸው፣ የኢራቅ ሕዝብ ለአንድነት ያለው ምኞት ከፍተኛ በመሆኑ አዲስ ሕይወት ለመጀመር በኅብረት በመጣር ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኢራቅ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአገሪቱ ውስጥ የደስታ እና የሰላም ተስፋን በማምጣት፣ መጭው ጊዜ የተሻለ እንደሚሆን ክርስቲያን ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን የሙስሊም ማኅበረሰብም ጭምር ተስፋ ማድረጉን፣ የሽብር ጥቃት ተንታኝ እና የፖለቲካ መምህር የሆኑት ወ/ሮ ላውራ ሳንፌሊቺ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

04 March 2021, 15:35