ፈልግ

የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ “COVAX” የተላከለትን የኮቪድ-19 መከላከያ መድኃኒት በዕርዳታ ሲቀበል     የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ “COVAX” የተላከለትን የኮቪድ-19 መከላከያ መድኃኒት በዕርዳታ ሲቀበል  

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላያከያ ክትባት ስርጭት የሰብዓዊ ወንድማማችነት መንፈስ የተከተለ መሆኑ ተገለጸ

በቅድስት መንበር የጀርመን አምባሳደር የሆኑት ክቡር አቶ ሚካኤል ኮክ፣ “COVAX” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ስርጭት አስተባባሪ ድርጅት፣ ክትባቱ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ለማድርግ የጀመረውን መርሃ ግብር የሚደግፉት መሆኑን አስታወቁ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በምህፃረ ቃል “COVAX” ተብሎ የሚጠራው ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላያከያ ክትባት ጥናት እንዲጎለብት፣ በጥንቃቄ እንዲመረት፣ ሰዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምርመራን ማድረግ እንዲችሉ መንገዶችን ማመቻቸት፣ በወረርሽኙ የተያዙት ሰዎች በቂ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እና ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የክትባት መርሃ ግብር እንዲካሄድ የሚያስተባብር ድርጅት መሆኑ ታውቋል። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች፣ ከፍተኛ የጤና ተቋማት እና የመርምር ማዕከላት የ “COVAX”ን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ የሚሰሩ መሆናቸው ታውቋል። በሌላ ወገን ሦስተኛ ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት በዓለም ዙሪያ እጅግ ከፍተኛ የሞት አደጋን በማስከተል ኤኮኖሚያዊ ቀውስን፣ ሥራ አጥ ቁጥር መጨመርን፣ ቤተሰብን ከቤተሰብ መለየትን እና የአዕምሮ ሕመምን ማስከተሉ ታውቋል። ወረርሽኙ ያደጉትን እና በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ሳይለይ በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች መሰራጨቱ ቢታመንም፣ ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ላይ  የሚገኝ ድሃ ማኅበረሰብ መሆኑ ታውቋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን በአገር ደረጃ በግል ይዞ ማስቀረት ማንንም እንደማይጠቅም ወይም እንደማያድን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና ቅድስት መንበር ከዚህ በፊት አስታውቀው፣ የሚበጀው በሰብዓዊ ወንድማማችነት እና በአንድነት መንፈስ የመከላከያ መድሃኒቱን በእኩል ተጠቃሚነት መልካም የወደ ፊት ሕይወትን ማመቻቸት እንደሚቻል ማሳሰባቸው ይታወሳል።   

በቅድስት መንበር የጀርመን አምባሳደር የሆኑት ክቡር አቶ ሚካኤል ኮክ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አገራቸው ጀርመን በ “COVAX” መርሃ ግብር በመታቀፍ ለዓለም ደህንነት ሲባል በጤናው ዘርፍ የምትችለውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቷን ገልጸዋል። “ሀብታም አገሮች ለሕዝባቸው እንጂ ስለ ሌላው ግድ የላቸውም” የሚለውን አስተያየት የማይቀበሉት ክቡር አቶ ሚካኤል ኮክ “መንግሥታት ለዜጎቻቸው ሕይወት ሃላፊነትን መውሰዳቸው እውን ቢሆንም፣ ጠቅላላ መግባባት ኖሮን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያን በተመለከተ ስኬታማ መሆን የሚቻለው እያንዳንዱን ሰው ከወረርሽኙ መጠበቅ ሲቻል ብቻ ነው” ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መድሐኒት እጥረት በመኖሩ ተፈላጊነቱ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ያሉት ክቡር አምባሳደር ሚካኤል ኮክ፣ አገራቸውን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች በኅብረት “COVAX” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ስርጭት አስተባባሪ ድርጅትን በመመስረት፣ በማደግ ላይ ያሉ አገሮችም እንዲሁ ክትባቱን አግኝተው ለህዝቦቻቸው እንዲያደርሱ በማገዝ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በዓለም ጤና ድርጅት ጥላ ስር ሆኖ እየሰራ የሚገኘው “COVAX” በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ቫይረሱን ለመዋጋት በሚደረጉት ጥረት በተቻለ መጠን እንዲሳተፉ ለመርዳት፣ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን እንዲያገኙ እገዛን በማድረግ፣ ሞያዊ ምክርን፣ በተለይም የክትባት መድኃኒቶችን በመላክ የሚያግዝ መሆኑን ክቡር አምባሳደር ሚካኤል ኮክ ተናግረዋል።

ማንም ብቻውን መዳን አይችልም

ያጋጠመንን ችግር በአንድነት እናሸንፈዋለን ወይም ካልሆነ በአንድነት እንረታለን የሚለው ግንዛቤ የ“COVAX” መርሃ ግብር የሚመራበት መንፈስ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ ሰብዓዊ ወንድማማችነት አስፈላጊነትን በማስመልከት ከሰጡት ምክር ጋር የሚስማማ መሆኑን ተናግረዋል። አምባሳደር ሚካኤል ኮክ አክለውም ከዓለም ሕዝብ መካከል አንድ ከመቶ የሕዝብ ቁጥር ያላት ጀርመን፣ በሰብዓዊ ወንድማማችነት ዓላማ በመነሳሳት የተቀረውን 99 ከመቶ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ ሃላፊነት ወስዳ ለመርዳት መወሰኗን አስረድተዋል።  

ዓላማዎች እና የጊዜ መስመር

የ “COVAX” የክትባት መርሃ ግብር በአንዳንድ አገራት መጀመሩን ያስታወቁት አምባሳደር ሚካኤል ኮክ፣ ወደ ሌሎች አገሮችም በመድረስ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ወደ ሌሎች 130 አገራት እንዲደርስ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው፣ ይህም እስከሚቀጥለው የአውሮፓዊያኑ ዓመት መጨረሻ 20 ከመቶ የዓለማችን ሕዝብ የክትባቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የክትባት መርሃ ግብሩን በገንዘብ የሚደግፍ እና የሚቆጣጠር የዓለም ጤና ድርጅት በድህነት ለሚቸገሩ የዓለማችን ሕዝቦች ክትባቱን ያለ ክፍያ ለማድረስ እቅድ ያለው መሆኑን በቅድስት መንበር የጀርመን አምባሳደር ክቡር አቶ ሚካኤል ኮክ አስረድተዋል።   

23 March 2021, 15:40