ፈልግ

በቻድ መዲና ንጃሜና የተቀመጡት፣ የG5 አገራት መሪዎች በቻድ መዲና ንጃሜና የተቀመጡት፣ የG5 አገራት መሪዎች 

አባ አርማኒኖ፣ ሰብዓዊ ክብርን ያገናዘበ መልሶ የማቋቋም ሥራ መሰራት እንደሚያስፈግ አሳሰቡ

G5 በመባል የሚታወቁ የሰሃል አገራት በቻድ ውስጥ የጋራ ስብሰባን ካካሄዱ በኋላ ከጂሃዳዊ ቡድኖች ጋር የሚደረገውን ውጊያ ለማጠናከር መስማማታቸው ታውቋል። በስምምነታቸው መሠረት ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ከአንድ ሺህ በላይ ተዋጊ ሠራዊት መሰማራቱን እና አሸባሪዎችም በክልሉ ተበራክተው መገኘታቸውን በኒጀር የወንጌል አገልጋይ የሆኑት ክቡር አባ ማውሮ አርማኒኖ ለቫቲካን ዜና ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶን በሚያዋስኑ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ እስላማዊ አሸባሪዎችን የሚዋጉ፣ በቁጥር አንድ ሺህ ሁለት መቶ የጦር ሠራዊት ወደ አካባቢው መላኩን የቻድ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ አስታውቀዋል። ውሳኔውን በቻድ መዲና ንጃሜና የተቀመጡት፣ የG5 አገራት የሚባሉ፥ ቻድ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ማውሪታኒያ እና ቡርኪና ፋሶ ሲሆኑ፣ በቪዲዮ አማካይነት የተካሄደውን ኮንፈረንስ የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ኤማኑኤል ማክሮን መካፈላቸው ታውቋል። ፕሬዚደንት ኤማኑኤል እንዳስገነዘቡት፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰውን እና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለውን ጂሃዳዊ ቡድኖችን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ አገራቱ ባዶ የቀሩ አካባቢዎችን በሠራዊቶቻቸው እንዲጠበቁ በማለት ከመከሩ በኋላ፣ ከዚህ በፊት በአካባቢው ሰላምን በማስጠበቅ ተግባር ላይ የቆዩ 5,100 የፈረንሳይ ወታደሮች አካባቢውን ለቀው የሚመለሱ መሆኑን ገልጸዋል። እ.አ.አ 2020 ዓ. ም. በአካባቢው የሚገኝ የፈረንሳይ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ቁጥር የጨመረበት ምክንያት፣ አሸባሪዎቹ በማሊ ውስጥ የሚገኙ ስድስት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይልን እና አምስት የፈረንሳይ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በመግደላቸው መሆኑ ታውቋል።

ከሁሉም በላይ የፖለቲካ ችግር ያለበት ነው

በሰሃል አገሮች ውስጥ በርካታ አሸባሪ ቡድኖች መኖራቸው ሲነገር ከእነዚህ ቡድኖች መካከል አንዳንዶቹ ከእስላማዊ መንግስት ጋር እራሳቸውን የሚያዛምዱ መሆኑን እና ለበርካቶቹ በአካባቢው ለሚደረግ ጦርነት ዋና ምክንያቱ ኤኮኖሚያዊ መሆኑ ታውቋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ በአካባቢው አሸባሪነት የተስፋፋበት ምክንያት ጠንካራ መንግስት ካለመኖሩ የተነሳ ነው ተብሏል። በኒጀር ኒያሜ ውስጥ በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የተሰማሩት፣ የአፍሪካ ሚሲዮናዊያን ማኅበር አባል የሆኑት ክቡር አባ ማውሮ አርማኒኖ፣ ኒጀር ከፍተኛ የአሸባሪዎችን ቁጥር ከሚያስመዘግቡ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸዋል። ክቡር አባ ማውሮ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀስ አሸባሪ ቡድንን የሚታገሉ ከአንድ ሺህ በላይ ወታደሮች ከቻድ መላኩ በቂ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ችግሩ ይህ ብቻ ሳይሆን በአገራቱ ውስጥ በማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሂደቶች ላይ ቆራጥ ለውጦች ሊደረጉ ያስፈልጋል ብለዋል። አባ ማውሮ በማከልም፣ ከሁሉም በላይ የፖለቲካ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸው፣ ይህም በትምህርት እና በሕግ አደረጃጀት ላይ ችግር ማስከተሉን አስረድተው፣ ሕግ ማስከበሩን በተመለከተ ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ መመለስ ትልቅ እርምጃ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ለጅሃዳውያን ምቹ ሥፍራ ሆኖላቸዋል

ክቡር አባ ማውሮ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት አገርን በጋራ ለመገንባት የሚያስችል የፖለቲካ መድረክን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አስረድተው፣ ማኅበራዊ ኑሮን መልሶ ለመገንባት ድሃውን ማኅበረሰብ፣ ወጣቱን ትውልድ፣ በማኅበራዊ ሕይወት እንቅስቃሴዎች እንዳይሳተፉ ስፍራን ለተነፈጉ ሴቶች ዕድል በመስጠት ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ እነዚህን ማኅበራዊ እውነታዎችን በውል ካልተገነዘቡ በቀር ሰላምን ማምጣት የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል። አማካይ የወጣት ትውልድ ዕድሜ 15 ዓመት በሆነባት ኒጀር በርካታ የዕድገት ለውጦች መመዝገባቸውን የሚገልጹት ክቡር አባ ማውሮ፣ ቢሆንም ማኅበራዊ ተቋማት ራሳቸውን ችለው የቆሙ ባለመሆናቸው ብዙ ቅዥቶች ውስጥ መግባት እንደማይገባ ገልጸው፣ ባለፉት ዓመታት የትምህርት እና የጤና ስርዓት የመፍረስ ሂደት ተመልክተናል ብለዋል። የለውጥ ሂደት ገና ይቀረዋል ያሉት ክቡር አባ ማውሮ፣ መንግስት የጤናን እና የፍትህ ዘርፍን ባላሳደገባቸው አካባቢዎች ጅሃዳዊ ታጣቂዎች ራሳቸውን ለማደራጀት ምቹ አጋጣሚን ያገኛሉ ብለዋል።        

ሰብዓዊ ክብርን ማሳደግ ያስፈልጋል

ለሰሃል አካባቢ አገሮች አለመረጋጋት ምክንያቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ለምግብ ፍለጋ ሲሉ ከቄያቸው እንዲፈናቀሉ ያደረገው ድህነት ነው ያሉት ክቡር አባ ማውሮ፣ ማኅበራዊ ሕይወት የሚቀጥልበት ተስፋ እንዲገኝ፣ ማኅበራዊ ሕይወትን መልሶ ለመገንባት ኃይል ያለው እና ለብዙ ዓመታት ተዘንግቶ የቆየው የውጣቱ ትውልድ ትኩረት ሊሰጠው ይግባል ብለዋል። አባ ማውሮ በመቀጠልም በአካባቢው በወንጌል አገልግሎት ለተሰማሩት ዋስትና እንዲኖራቸው ጠይቀው፣ በማሊ ከረጅም ዓመታት መታሰር በኋላ እ.አ.አ በ2020 ዓ. ም. ተፈተው ነጻ የወጡትን አባ ጂጂ ማካሊን እና ከአራት ዓመት በፊት ታግተው የተወሰዱትን እህት ግሎሪያ ናርቫሬስን አስታውሰዋል። የወንጌል መልዕክተኞቹ ከምዕራቡ ዓለም እና ከክርስቲያን ወገን መሆናቸው ለከፍተኛ ችግር የሚዳርጋቸው ቢሆንም ያደርጋቸውም ችግር ውስጥ ከሚገኝ የአካባቢው ሕዝብ ጋር አብሮ መጓዝ መሰረታዊ ሰላምን የሚሰጥ መሆኑን አባ ማውሮ አስረድተው፣ የሕዝቡ ቁስል የሚሲዮናዊያኑ ቁስል በመሆኑ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕሙማንን፣ የድሆችን እና የችግረኞችን ሕይወት እንደተካፈለ ሁሉ እኛም የአካባቢውን ሕዝብ ስቃይ እና ችግር መጋራት ይኖርብናል ካሉ በኋላ “ሰብዓዊ ክብር የሚባለው በዚህ አካባቢ ትርጉም እና ዋጋ የሚሰጠው ከሆነ፣ መከራ ቢበዛብንም በአካባቢው የተገኘንበት ዋና ምክንያት ለሰው ልጅ ክብር ስንል ብቻ ነው” በማለት ክቡር አባ ማውሮ አርማኒኖ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።             

17 February 2021, 17:09