ፈልግ

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ወደ ወንድማማችነት መድረክ ማምጣት የሚጠበቅ መሆኑ ተገለጸ

ጥር 27/2013 ዓ. ም. የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀንን ለማክበር መላው ዓለም ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ሲነገር፣ ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ካደረጉት ሰዎች መካከል አንዱ ዳኛ አብደል ሳላም መሆናቸው ታውቋል። ዳኛው የሕዝቦችን ወንድማማችነት ለማሳደግ መንገድ የሚሆነውን ይህን ታላቅ ቀን በማስመልከት ከቫቲካን ዜና ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በየዓመቱ የሚከበረው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን ሀሳቦችን እና ራእዮችን በማደስ የሰዎችን ምኞት እውን የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአንድ ወቅት በግብጽ መንግሥት ምክር ቤት የታላቁ አል-አዛር ኢማም የሆኑት የሼክ አህመድ አል-ታይብ አማካሪ በመሆን ያገለገሉት ዳኛ ሞሐመድ መሐመድ አብደል ሳላም፣ በሞያቸው ማገለግለ ከጀመሩበት ጊዜ ወዲህ በማኅበረሰቡ መካከል የጋራ ውይይቶችን በማስተባበር እና በሐይማኖት ስም የሚቀሰቀሱ አመጾችን ለማስወገድ የሚያግዙ ሕጎችን በመቅረጽ እንደሚታወቁ ተነግሯል። ዳኛ ሞሐመድ መሐመድ አብደል ሳላም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና በአል አዛር ዩኒቨርሲቲ መካከል የነበረውን ግንኙነት ለማሳደግ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ.አ.አ የካቲት 3/2019 ዓ. ም. ልዩ ሽልማት ለማበርከት እንደሚፈልጉ ካሳወቁ በኋላ ሽልማቱን በመጋቢት ወር 2019 ዓ. ም. አበርክተውላቸዋል። በዓለማችን ውስጥ ሰላምን እና የጋራ ሕይወትን ለማሳደግ በሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ውስጥ የተገልጹ ሃሳቦችን በተግባር ለመተርጎም በመቻላቸው ዳኛ ሞሐመድ መሐመድ አብደል ሳላም እ.አ.አ በነሐሴ ወር 2019 ዓ. ም. የሰብዓዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚቴ ዋና ጸሓፊ ሆነው መመረጣቸው ታውቋል።

የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀንን በማስመልከት ዳኛ ሞሐመድ መሐመድ አብደል ሳላም ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። በቃለ ምልልሳቸው ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሚከበረው ዓለም አቀፍ ቀን ጠቅላላ አመለካከት ምን እንደሚመስል፣ ሰብዓዊ ወንድማማችነት እና የጋራ ሕይወት በተለያዩ ሰዎች ልብ ውስጥ ለማስገባት የተደረገውን ጥረት እና የሰነዱን ጭብጥ በተግባር ለመተርጎም በግል ያደረጓቸውን ጥረቶች በማስመልከት አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

ዳኛ ሞሐመድ መሐመድ አብደል ሳላም ለቫቲካን ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ በሚገባ ተመልክቶ፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀን እንድከበር መወሰኑ በመጭው ትውልድ መካከል ወዳጅነትን እና ወንድማማችነትን ማሳደግ አስፈላጊነት የተረዳው መሆኑን ያመለክታል ብለዋል። ተላላፊው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት ወቅት፣ አምጽ እና ጥላቻ እየተስፋፋ በሚገኝበት ባሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህን የመሰለ ውሳኔን ማሳለፉ፣ ችግሮች የሚፈቱት በሰው ልጆች መካከል በሚፈጠረው መተጋገግዝ እና ወንድማማችነት ብቻ መሆኑን ያመለክታል ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ ታላቅነት የሚለካው ሰብዓዊ ወንድማማችነትን እና ዓለም አቀፍ ሃላፊነትን ቀዳሚ በማድረግ፣ መላው ዓለም እነዚህን ወድ መርሆዎችን ከልብ በመገንዘብ፣ አዳዲስ ሀሳቦችን እና ዕይታዎችን እውን በማድረግ፣ የመቻቻል እና አብሮ የመኖር ፍላጎትን የሚያነቃቃ በመሆኑ ነው ብለዋል።

በሐይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ አገሮች እና ተቋማት በኩል የተዘጋጁ በርካታ ሰብዓዊ አመለካከቶችን ወደ ተግባር መለወጣቸውን ያስታወሱት ዳኛ ሞሐመድ መሐመድ አብደል ሳላም፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የታላቁ አል-አዛር ኢማም የሆኑት አህመድ አል-ታይብ በጋራ ከፈረሙት የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ በኋላ የተለያዩ ሃይማኖቶች መሪዎች ሰነዱን ተስማምተው መቀበላቸውን ተመልክተናል ብለዋል። አክለውም ባለፉት የሥራ ዘመንም በሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል ትብብርን ለማሳደግ ያላቸው ፍላጎት ከፈተኛ መሆኑን ገልጸው ከእነዚህ ተቋማት ጋር አጋርነትን ለመመስረት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

በመንግሥታት እና በውሳኔ ሰጭዎች ደረጃ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያግዙ ድጋፎችን በማግኘት፣ የአረብ ኤምረቶች ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪዎች የተለያዩ አገሮች ዜጎች ላይ ያንዣበበው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በተጠቂዎች መካከል ልዩነት ሳይደርግ፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ላይም ተጽዕኖ ሳይደረግባቸው ለእያንዳንዱ ሰው ዕርዳታ እንዲደርሰው ለማድረግ መወሰኑን ዳኛ ሞሐመድ መሐመድ አብደል ሳላም አስረድተዋል። የሰብዓዊ ወንድማማችነት ከፍተኛ ኮሚቴ መላው ዓለም ለሰው ልጆች እንዲፀልይ በጋበዘበት ወቅት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ልባቸውን ለወንድማማችነት እና ለአንድነት በመመለስ ለጥሪው ምላሽ ለመስጠት መቆማቸውን አስታውሰዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እጅግ አስፈላጊ ወደ ሆነው ወደ ሰብዓዊ ወንድማማችነት መልዕክት በጋበዟቸው ጊዜ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው የገለጹት ዳኛ ሞሐመድ መሐመድ አብደል ሳላም፣ የቅዱስነታቸውን መልዕክት በሚገባ ለማንበብ ያላቸውን እርግጠኝነት መግለጻቸውን አስታውሰዋል። የቅዱስነታቸውን መልዕክት በሚያነቡበት ጊዜ በውስጡ የሚገኙት ርዕሠ ጉዳዮች እና ሃሳቦች በሰዎች መካከል ወንድማማችነትን እና ሰላምን ለማሳደግ የሰቡ መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማስታወስ ያስተላለፉትን መልዕክት እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ዳኛ ሞሐመድ መሐመድ አብደል ሳላም፣ ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው እንደገለጹት፣ በችግር ውስጥ የሚገኙትን በሙሉ እንደ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በመመልከት የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ እንድናደርግላቸው ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

በር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በታላቁ አል-አዛር ኢማም በሆኑት አህመድ አል-ታይብ የተገለጹት ሰብዓዊ ባሕሪዎች፣ በእስልምና እና በክርስትና ሐይማኖቶች ውስጥ የሚገኙትን የሰላም እና የፍቅር እሴቶች አጉልቶ ከማሳየቱ በተጨማሪ፣ በሁለቱ እምነቶች ውስጥ የሚገኙ ግንኙነቶችን የሚያሳዩ መሆኑን አስረድተዋል። በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን ተግባራዊ ማድረጉ ከባድ መሆኑን የሚናገሩ አንድንድ ሰዎች ቢኖሩም፣ በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እና በታላቁ አል-አዛር ኢማም በሆኑት በአህመድ አል-ታይብ ስምምነት የተጀመረው የሰብዓዊ ወንድማማችነት እና ዓለም አቀፍ ወዳጅነት በጎ ዕቅድ፣ ሁለቱ መሪዎች በቋንቋ፣ በዘር፣ በባሕል በሐይማኖት ቢለያዩም ለሰብዓዊነት ሲሉ በፍቅር ተስማምተው አብረው ለመኖር እና ለመሥራት መጀመራቸው የሰብዓዊ ወንድማማችነትን ሰነድ በተግባር መግልጽ የሚቻል መሆኑን ያረጋገጡበት መሆኑን ዳኛ ሞሐመድ መሐመድ አብደል ሳላም ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አረጋግጠዋል።            

02 February 2021, 12:50