ፈልግ

በየመን ለአመጽ ከሚውሉ የጦር መሣሪያዎች መካከል በየመን ለአመጽ ከሚውሉ የጦር መሣሪያዎች መካከል 

የጦር መሣሪያ ምርትን በመቃወም ውይይት መደረጉ ተገለጸ

የጦር መሣሪያ ምርት ተወግዶ ሰላም የሚገኝበትን የኤኮኖሚ እድገት ለማምጣት የተለያዩ ሕዝባዊ ማኅበራት እና የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ አባላት የካቲት 10/2013 ዓ. ም. በአውታረ-መረብ አማካይነት ተገናኝተው የጋራ ውይይት አድርገዋል። በፎኮላሬ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ስር የተቋቋመው እና “ጦር መሣሪያ አልባ ኤኮኖሚ” የሚል መጠሪያ ያለው ግሩፕ የሰውን ሕይወት ለሞት ሳይዳርግ ሰላም የሰፈነበት የኤኮኖሚ እድገትን በማምጣት የሥራ ዕድልን እና አካባቢን ከውድመት ማዳን እንደሚቻል ቺንሲያ ጓይታ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ገልጻለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“አካባቢ፣ ሥራ እና የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ” በሚል ርዕስ በጣሊያ ውስጥ ታራንቶ ከተማ እ.አ.አ ከመጭው ጥቅምት 11-14/2014 ዓ. ም. ድረስ እንደሚደረግ አዘጋጅ ቡድኑ አስታውቋል። ለአንድ ሳምንት የሚቆየውን ማኅበራዊ ዝግጅት በማስመልከት በአውታረ-መረብ አማካይነት የሚካሄድ ውይይት ትናንት የካቲት 10/2013 ዓ. ም. መጀመሩ ታውቋል። ይህን ውይይት የሚካፈሉት ባለሞያዎች ወይም አባላት፣ የጦር መሣሪያ ምርቶችን ለመግታት እና ቁጥጥር ለማድረግ የተቋቋሙት የልዩ ልዩ ድርጅቶች አባላት መሆናቸው ታውቋል።

ጣሊያን እና የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ

ጣሊያን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጦር መሣሪያን ወደ ውጭ ከሚልኩት አሥር አገራት መካከል አንዷ ስትሆን፣ ቀላል የጦር መሣሪያዎች የሚባሉትን በማምረት እና ወደ ውጭ በመላክ በዓለም የቀዳሚነት ስፍራ ያላት መሆኑ ታውቋል። ጣሊያን JSF35 የተባሉ ተዋጊ የጦር ጄቶችን የመጠገን መርሃግብር በመቀላቀል የኑክሌር መሣሪያዎችን ለማስታጠቅም ዕቅድ ያላት መሆኑ ታውቋል። ከሌሎች ታላላቅ የጦር መሣሪያ አምራች ኩባኒያዎች ጋር በመሆን ያመረተችውን የጦር መርከብ ለግብጽ እና ሳውድ አረቢያ መንግሥታት በቅርቡ ለሽያጭ ማቅረቧ ይታወሳል። በየመን ግጭት ውስጥ ለተሳተፉ ሀገሮች የሚላኩ ፈንጂዎች በጣሊያን ውስጥ መመረቱ ተቃውሞ ማስነሳቱን ከውይይቱ ተካፋዮች በኩል የቀረበው ሪፖርት ያመለከተ ሲሆን፣ ይህም ጣልያን በጦርነት ውስጥ ባሉት አገሮች የጦር መሣሪያ መላክ የሚከለክል ሕገ-ደንብ ቁጥር 185/90 የሚጥስ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህ ደንብ በተጨማሪም የተለያዩ ሲቪል ማኅበረሰብ ከካቶሊካዊ ማኅበር ጋር በመተባበር ጦርነትን የሚከለክል ሕገ መንግሥታዊ ደንብ እንዲረቅ መደረጉ ይታወሳል።           

የፋይናንስ እገዛን ማቆም

“የጦር መሣሪያ ትጥቅ ማስፈታት” ፎኮላሬ የተባለ ካቶሊካዊ እንቅስቃሴ ዋና ዓላማ ሲሆን እንቅስቃሴው ይህን ዓላማ ለማጠናከር ሲል እ.አ.አ በ2015 ዓ. ም. ለጦር መሣሪያ ትጥቅ የሚውለውን የገንዘብ ዕርዳታን የሚስያቆም ማኅበር መመስረቱ የሚታወስ ሲሆን በተጨማሪም እንቅስቃሴው የተለያዩ ስብሰባዎችን፣ ጉባኤዎችን፣ የመታሰቢያ ቀን በዓላትን በማዘጋጀት እና ማኅበራትን ሲያስተባብር መቆየቱ ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በማለት ይፋ ባደረጉት ቃለ ምዕዳን፣ ለጦር መሣሪያ ግዥ የሚውለውን ከፍተኛ ገንዘብ ረሃብን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከዓለማችን ገጽ ለማጥፋት እና በድህነት የሚሰቃዩ አገራትን ወደ እድገት ለማምጣት ቆራጥ ውሳኔን ማድረግ ያስፈልጋል በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

የኢኮኖሚ እና ምርታማነት ቋጠሮን መበጠስ

በየመን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማገዝ የሚላኩ የጦር መሣሪያዎች የሚመረቱት፣ በጣሊያን ሳርዴኛ ግዛት ሲሆን ማዕከሉን የሚቆጣጠረው የጀርመን ኩባኒያ መሆኑ ይታወቃል። እ.አ.አ ከ2019 ዓ. ም. ጀምሮ በኩባኒያው ላይ ከባድ ተቃውሞን በማሰማት የጦር መሣሪያ ትጥቅ ለማስፈታት ጥረት እያደረገ ያለው ሬንሜታል የተባለ እንቅስቃሴ መሆኑ ታውቋል። እንቅስቃሴው ባሰማው ተቃውሞ የተነሳ የጣሊያን መንግሥት ምክር ቤት እ.አ.አ በሰኔ ወር 2019 ዓ. ም. ባስተላለፈው ጠቅላላ ውሳኔ፣ በየመን ጦርነት ላይ ለተሳተፉት ሁለት አገሮች፣ እነርሱም ሳውድ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሊላክ የነበረውን ከባድ የጦር መሣሪያ ሽያጭን ያገደ መሆኑ ይታወሳል።

እ.አ.አ. በ2021 ዓ. ም. የሚካሄደውን ውይይት ከልዩ ልዩ የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ጋር በመተባበር፣ ጣሊያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመደቡት ቀዳሚ የጦር መሣሪያ ላኪ አገሮች መካከል መመደቧ፣ ባለፉት ዓመታት ውስጥ የጦር መሣሪያ አምራች አገሮች የወሰዱት የተሳሳተ ውሳኔ መሆኑ ታውቋል። በውይይቱ ላይ እንደሚሳተፉ የገለጹት ቺንሲያ ጓይታ፣ የተሳተፉበት ዋና ዓላማ በጣሊያ ውስጥ ሳርዴኛ ግዛት ውስጥ የሚገኘው የከባድ ጦር መሣሪያ ምርት የሚከለክል ሕገ-ደንብ ቁጥር 185/90 መጣሱን ለማሳወቅ መሆኑን አስታውቀው፣ ከዚህም በተጨማሪ የጋራ ውይይቱ ዋና ዓላማ በጣሊያን መንግሥት ምክር ቤት የተደረሰው ጦርነትን የመቃወም ሕገ መንግሥታዊ ውሳኔን በክርስቲያናዊ አስተሳሰብ በመታገዝ ለማጽናት መሆኑን አስታውቀዋል።

እ.አ.አ በ2015 ዓ. ም. ለጦር መሣሪያ ትጥቅ የሚውለውን የገንዘብ ዕርዳታን ለማስቆም የተመሠረተው ማኅበር ዋና አላማ፣ ከኤኮኖሚያዊ አቅጣጫ በመነሳት በጣሊያን ውስጥ ለጦር መሣሪያ ምርት የሚውለውን የፋይናንስ ድጋፍ በመቃወም በሰው ልጆች መካከል እጅግ ተፈላጊ የሆነውን ሰላምን ለመገንባት ቆራጥ ውሳኔ እና ምርጫ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ታውቋል። ሰላም ለሰው ልጅ እድገት እና ሕይወት ምንም አማራጭ የሌለው ቢሆንም ተገቢ እንክብካቤ ሳይደረግለት ቀርቶ በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነቶች እንዲቀጣጠሉ ዕድል በመሰጠት ላይ መሆኑን ቺንሲያ ጓይታ ገልጸው፣ “የጦር መሣሪያ ትጥቅ ማስፈታት” የተባለ ካቶሊካዊ እንቅስቃሴ በተለያዩ ጊዜያት ባካሄዳቸው አስተንትኖ ያሰባሰባቸውን ገንቢ ሃሳቦችን ይዞ በመቅረብ እና አባላቱን አሰልጥኖ በማዘጋጀት የሰላምን እና የጦርነትን ተለዋዋጭነት አስመልክቶ አቋሙን ለህዝብ በመግለጽ ላይ ይገኛል።

በየመን ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጾ፣ ይህም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የከፋው ጥፋት የተከሰተበት በማለት ገልጾታል። ጣሊያን በተዘዋዋሪ መንገድ በክልሏ ውስጥ በሚገኝ ፋብሪካ የተመረተውን የጦር መሣሪያ ወደ ውጭ በመላክ ለጥፋት ተግባር ያበረከተች ሀገር መሆኗ ታውቋል። ፋብሪካው በጀርመን ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን ይህን ጉዳይ ለጣሊያን ፖለቲከኞች ለማሳወቅ የተለያዩ ግንኙነቶችን ማድረጋቸውን ቺንሲያ ጓይታ አስታውቀዋል። በቅርቡ የታየው ልውጥ ቢኖር እ. ኤ. አ. ዘንድሮ ጥር ወር ውስጥ የጁሴፔ ኮንቴ መንግስት በወሰደው የመጨረሻው እርምጃው ለሳዑዲ አረቢያ የጦር መሣሪያ ሽያጭ እቀባ ማድረጉን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በነበሩት መንግስታት የታቀደው የጦር መሣሪያ ሽያጭም ውድቅ ማድረጉን ቺንሲያ ጓይታ አክለው አስታውቀዋል።

“የጦር መሣሪያ ትጥቅ ማስፈታት” የተባለ ካቶሊካዊ እንቅስቃሴ ለአዲሱ የጣሊያን መንግሥት ባቀረበው አቤቱታ፣ የጦር መሣሪያ አምራች ተቋማት ለአካባቢ ጥበቃ ቅድሚያን በመስጠት፣ ሰላምን የሚያመጣ ዘላቂነት ያለውን ኤኮኖሚ መፍጠር እንጂ በአካባቢ ላይ ውድመትን የሚያስከትል አደገኛ የጦር መሣሪያን ማምረት እንደሊለበት ጠይቋል። ካቶሊካዊ እንቅስቃሴው ለአገር ውስጥ የፖለቲካ ሃይሎች ባስተላለፈው ጥሪ አክሎም ለጣሊያን እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የአካባቢ ጥበቃን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ ሃሳቦችን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ቀርቦ በውይይት ማግኘት ያስፈልጋል በማለት እንቅስቃሴው ለጣሊያን መንግስት አቤቱታውን አቅርቧል።

18 February 2021, 18:09