ፈልግ

በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ የተሰማራው የጸጥታ አስከባሪ ኃይል በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ የተሰማራው የጸጥታ አስከባሪ ኃይል  

በዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ ሁከትን የሚያነሳሱ የቅኝ ግዛት ውርሶች መኖራቸው ተገለጸ

ሰኞ የካቲት 15/2013 ዓ. ም. በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ምሥራቃዊው ክፍለ ሀገር የሥራ ጉብኝት ለማካሄድ በጉዞ ላይ በነበሩት፣ በኮንጎ የጣሊያን አምባሰደር በሆኑት በክቡር አቶ ሉካ አታናሲ ላይ ታጣቂዎች በተከፈተባቸው ተኩስ፣ ከአንድ ጠባቂ ፖሊስ እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሽከርካሪ ጋር መገደላቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ድርጊቱን በማውገዝ ድምጻቸውን ካሰሙት በርካታ መሪዎች ጋር በመሆን ሐዘናቸውን መግለጻቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው የቴሌግራም መልዕክታቸውን የላኩት ማክሰኞ የካቲት 16/2013 ዓ. ም. ሁለት የአደጋው ሰለባዎች አስከሬን ወደ ሮም በደረሰበት ወቅት መሆኑ ታውቋል። በታጣቂዎች በኩል ጥቃት የተሰነዘረባቸው በኮንጎ የጣሊያን አምባሳደር የነበሩት ሉካ አታናሲ እና የደህንነት ጠባቂያቸው አቶ ቪቶሪዮ አንቶናቺ ከአሽከርካሪያቸው ሙስጠፋ ሚላምቦ ጋር በምሥራቅ ኮንጎ፣ ጎማ በተባለ መንደር በምትገኝ በሰሜን ኪቩ ውስጥ የሚካሄደውን የዓለም ምግብ ፕሮግም ድርጅት የዕርዳታ አቅርቦት መርሃ ግብርን ለመጎብኘት ሲጓዙ መሆኑ ታውቋል።

ለአደጋው ሃላፊነትን የወሰደ ክፍል እስካሁን አለመኖሩ ሲነገር፣ በአካባቢው በተሰማሩት የጸጥታ አስከባሪ ኃይል መረጃ መሠረት ከዚህ በፊት በሰሜን እና ደቡብ ኪቩ 122 የተለያዩ ጠንካራ የሚባሉ ታጣቂ ቡድኖች መኖራቸውን እና እስካሁንም ከ2000 በላይ ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂዎቹ እጅ መገደላቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን አስታውቋል። የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ፕሬዚደንት ፌሊክስ ሺሰከዲ የአደጋውን መርማሪ ባለስልጣን ለማገዝ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ አማካሪያቸውን እና የጣሊያን ፖሊሶችን ወደ አካባቢው ልከዋል። አካባቢው እስካሁን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ኃይል ሲታገዝ የቆየ እና ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያህል የተመደበለት 15,000 ያህል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ አስከባሪ ኃይል የተሰማራበት አካባቢ መሆኑ ታውቋል።

ዴሞክራቲክ ሪ. ኮንጎ እጅግ ሀብታም ከሚባሉ አገሮች አንዱ ናት

ሰሜን ምሥራቅ ኮንጎ እጅግ ለም፣ በመዳብ ፣ በወርቅ ፣ በአልማዝ ፣ በኮባልት ፣ በዩራኒዬም ፣ እና በነዳጅ ዘይት የበለፀገ አካባቢ መሆኑ ሲታወቅ፣ ኮንጎን በዓለማችን ውስጥ ሃብታም ከሚባሉ አገሮች መካካለ አንዷ አድርጓታል። ከ60 ዓመታቱ የቤልጄም ቅኝ ግዛት በኋላም ቢሆን በኮንጎ የፖለቲካ መረጋጋት ጠፍቶ ሙስና፣ ድህነት እና የሥራ አጥ ቁጥር በመጨመር አመጾች ሲቀሰቀሱ ቆይቷል። የተፈጥሮ ሃብትን ለመጋራት በሚደረግ ውጊያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል። የአገሪቱ ፕሬዚደንት ፌሊክስ ሺሰከዲ፣ እ. አ. አ. በጥር ወር 2019 ዓ. ም. ስልጣን በተረከቡበት ጊዜ በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍላተ አገራት ውስጥ ጸጥታን ለማስከበር ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው።

ነገር ግን ተንታኞች እንደሚሉት የጦራቸውን ዋና መቀመጫን ወደ ሥፍራው ለማዛወር ፣ በክልሉ የሚታየውን የጸጥታ እና ስትራቴጂ ሁኔታ ለማሻሻል የተገባው የተስፋ ቃላቸው ፍሬ አልባ ሆኖ መቅረቱ ታውቋል። አጎራባች አገር ከሆኑት ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ቡሩንዲ ጋር ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት ለማሻሻል ያደረጉት ጥረትም እንደዚሁ ፍሬን ሳያፈራ መቅረቱ ታውቋል። በዚህ ምክንያት የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ሕዝብ ከፍተኛ የሕይወት ዋጋን እየከፈለ የሚገኝ እና ሁከትን የሚያነሳሱ የቅኝ ግዛት ውርሶችን በማስተናገድ አመጽ እና ብጥብጥ የተስፋፋበት አገር መሆኑ ታውቋል። 

25 February 2021, 13:37