ፈልግ

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር፣ አቶ ቢሲሌይ የ2020 ዓ. ም. የኖቤል የሰላም ሽልማት በተቀበሉበት ወቅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር፣ አቶ ቢሲሌይ የ2020 ዓ. ም. የኖቤል የሰላም ሽልማት በተቀበሉበት ወቅት  

ለዓለም ሕዝብ በቂ ምግብን ማቅረብ ከሰላም ማረጋገጫ መንገዶች አንዱ መሆኑ ተነገረ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም “WFP-PAM” ታኅሳስ 23/2013 ዓ. ም. የተከበረውን ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት፣ ለዓለም ሕዝብ በቂ ምግብን ማቅረብ ከሰላም ማረጋገጫ መንገዶች አንዱ መሆኑን አስታወቀ። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማኖያ ጁኔያ፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀጥሎ ዓለማችንን ያስጨነቀው ሁለተኛው ወረርሽኝ ረሃብ መሆኑን አስረድተው፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት መሠረት በማድረግ፣ የገንዘብ አቅምን አውዳሚ የጦር መሣሪያ መግዣ ከማዋል ይልቅ የተራቡትን መመገብ እና አቅመ ደካሞች የሚታገዙበት እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ 17 ሚሊዮን ሕጻናትን፣ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ገበሬዎች የቦይ መስመር እና ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ የሚያደርሱበትን መንገድ በመሥራት ለዓለም ሕዝብ በቂ ምግብን ማምረት ሰላም ከሚረጋገጥበኣቸው መንገዶች አንዱ መሆኑ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማኖያ ጁኔያ ተናግረዋል። በተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ዕርዳታን በማቅረብ የሚታወቀው ዓለም አቀፉ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የጎርጎሮሳዊያኑን 2020 ዓ. ም. የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆኑን አስታውሰው፣ ይህ ድርጅት ባሁኑ ጊዜ በዓመት ከመቶ ሚሊዮን ሰዎች በላይ ከረሃብ አደጋ የሚታደጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከአመጽ የወጡት የሰላምን አየር እንዲተነፍሱ ማገዝ     

ከጎርጎሮሳውያኑ 2013 ዓ. ም. ጀምሮ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር እና የፋይናንስ ክፍልን ሲመሩ የቆዩት ክቡር አቶ ማኖያ ጁኔያ፣ ድርጅታቸው በሮም ከተማ የተዘጋጀለትን የኖቤል የሰላም ሽልማት፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ታኅሳስ 10/2020 ዓ. ም. በተቀበለ ጊዜ ባሰሙት ንግግር፣ የድርጅታቸው ቀዳሚ ዓላማ በአመጽ ውስጥ የሚገኙት የዓለማችን አካባቢዎች ከአመጽ ወጥተው ወደ ሰላም ጎዳና እንዲገቡ በማድረግ፣ ለጦርነት የሚጋብዙ የውስጥ ግጭቶችን በማስወገድ ወደ ብልጽግና ማድረስ መሆኑን አስረድተዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማኖያ ጁኔያ፣
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማኖያ ጁኔያ፣

አስከፊውን የረሃብ እና የጦርነት መረብ መበጠስ

ዓለም አቀፉ የሰላም የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ በበኩሉ ሽልማቱ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንዲቀበል ያደረገበት ዋናው ምክንያት፣ የሰላም ማጣት ረሃብን ሊያስከትል ስለሚችል፣ በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩት ሰዎች በቂ ምርት እንዲያመርቱ፣ ኤኮኖሚውም እንዳይደናቀፍ ለማድረግ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በርትቶ በመሥራቱ የተነሳ መሆኑን አስረድቷል። ክቡር አቶ ማኖያ ጁኔያም በበኩላቸው ከ690 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 60 ከመቶ የሚሆኑት በቂ ምግብን ባለማግኘታቸው በረሃብ እንደሚሰቃዩ እና እነዚህም ግጭቶች በሚበዙባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጦር መሣሪያ ምርትን ማቆም እና ገንዘብን ለዕርዳታ ፕሮግራም ማዋል

መረጋጋትን እና ሰላምን የሚያረጋግጡ ሰብዓዊ ዕርዳታ ፕሮግራሞችን በገንዘብ መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን የገለጸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ በአዲሱ የጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ. ም. በ80 አገሮች ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በአስቸኳይ የምግብ አቅርቦት ለማገዝ 12 ቢሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ የሚያስፈልግ መሆኑን አስታውቋል። ለዓለም የምግብ ፕሮግራም የተሰጠው የ2020 ዓ. ም. የኖቤል የሰላም ሽልማት፣ ሰብዓዊ ቀውሶችን ለመቋቋም ፈጥኖ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ መልዕክት የሚያስተላልፍ ሲሆን፣ ነገር ግን ይህ ካልተደረገ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀጥሎ ረሃብ ከፍተኛ አደጋን ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል። 270 ሚሊዮን ሰዎችን ያጠቃው የረሃብ አደጋ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አደጋው በእጥፍ ማደጉ ሲነገር፣ እንደ የመን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሶርያ እና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ፣ አደጋውን ለመከላከል የሚያስችል የምዕራባዊያን በቂ የገንዘብ ዕርዳታ የማይደርሳቸው መሆኑ ታውቋል።

ለጦር መሣሪያ መግዣ የሚውል ገንዘብ ረሃብን ለመዋጋት ይዋል

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በአንድ ወቅት መልዕክታቸው “ማንም ከማኅበረሰብ ተነጥሎ ወደ ኋላ መቅረት የለበትም” በማለት፣ አላስፈላጊ ወጭዎችን እና ኢፍትሃዊነትን በመዋጋት፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ዕርዳታ አቅምን በማሳደግ፣ ለጦር መሣሪያ መግዣ የሚውለውን ገንዘብ ረሃብን ለማስወገድ በሚደረግ ጥረት ውስጥ ማዋል የሚያስፈልግ መሆኑ ተገልጿል። ለጦር መሣሪያ መግዣ ከሚውል የገንዘብ ወጪ ከመቶ እጅ ጥቂቱን ብቻ እንኳን ለረሃብ ማስወገጃ ብንጠቀምበት፣ እስከ ጎርጎሮሳዊያኑ 2030 ዓ. ም. ድረስ የተወጠነውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ክቡር አቶ ማኖያ ጁኔያ አስረድተዋል። 

02 January 2021, 15:37