ፈልግ

በሱዳን-ዳርፉር የሰላም አስከባሪ ሠራዊት ተልዕኮ በሱዳን-ዳርፉር የሰላም አስከባሪ ሠራዊት ተልዕኮ  

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል የዳርፉርን ተልዕኮ ፈጸመ

በምዕራባዊ ሱዳን ዳርፉር ክፍለ ግዛት ለ13 ዓመታት ሰላም በማስከበር ተልዕኮ ተሰማርቶ የነበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ተልዕኮውን ማጠናቀቁ ታውቋል። ሰላም አስከባሪ ኃይሉ ተልዕኮውን የጀመረው እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2007 ዓ. ም እንደነበር ይታወሳል። የሱዳን መንግሥት በዳርፉር ክፍለ ሀገር የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለመወጣት መዘጋጀቱን አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2007 ዓ. ም በዳርፉር ክፍለ ሀገር ሰላም በማስከበር ተልዕኮ የተሰማራው ሠራዊት ቁጥር 26 ሺህ እንደነበር ይታወሳል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በአውሮፓዊያኑ 2020 ዓ. ም. መጨረሻ ተልዕኮን ለመቀጠል የሚያስችል ስምምነት ሳያድስ ቀርቷል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትም በዳርፉር የሚካሄደውን የሰላም ማስከበር ሃላፊነትን ለሱዳን መንግሥት አሳልፎ መስጠቱ ታውቋል።

ዳርፉር

በዳርፉር ክፍለ ሀገር እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2003 ዓ. ም. የተጀመረው አመጽ ተስፋፍቶ በምዕራብ ሱዳን አማፅያን እና በካርቱም ጦር መካከል እ. አ. አ የካቲት 26/2013 ዓ.ም. ከፍተኛ ግጭት መካሄዱ ይታወሳል። ዳርፉርን ጨምሮ በምዕራባዊው የሱዳን ክፍለ ሀገር የሚገኙ የፉር ጎሳ አባላት እ.አ.አ ከ1985 – 1988 ከአባይ ሸለቆ ነዋሪ ከሆኑት ከአረብ ታጣቂ ወንበዴዎች ጋር መጋጨታቸው ይታወሳል። ጃንጃዊድ የተባለ የምዕራብ ሱዳን አማጺ ቡድን ከቻድ እና ከሊቢያ ጦር ሠራዊት ጋር በመተባበር እ.አ.አ በ1989 ዓ. ም. የተካሄደውን እስላማዊ-ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መምራቱ ይታወሳል። እ.አ.አ በ2003 ዓ. ም. ከምዕራብ ሱዳን ዘላን ማኅበረሰብ የተመለመሉ የተለያዩ አረብ እስላማዊ ሚሊሻ ታጣቂ ወገኖች በዳርፉር ግዛት በተካሄደ አመጽ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የሕይወት መጥፋት አደጋን ማድረሳቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ለሱዳን ነጻነት እና እኩልነት የሚታገሉ ሁለት ግንባር ቀደም የጃንጃዊት አማጺ ቡድኖች መመስረታቸው ታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው በአካባቢው በተካሄደው ጦርነት፣ ከጎርጎሮሳዊያኑ 2003 ዓ. ም. ወዲህ ከ300 ሺህ ሰዎች በላይ መሞታቸው እና ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው ታውቋል።

ችግሩ የጦር መሣሪያ ክምችት ነው

የቅዱስ ኮምቦኒ ገዳማዊያን ማኅበር አባል፣ ጋዜጠኛ እና በአፍሪቃ ውስጥ ለረጅም ዓመታት የኖሩት አባ ጁሊዮ አልባነዚ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ካለፈው ወር ጀምሮ በሥፍራው የሚያበረክተውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለመፈጸም መወሰኑ ተቃውሞን ማስነሳቱን ገልጸው፣ የሱዳን የሽግግር መንግሥት በአካባቢው የተሻለ ሰላምን እና መረጋጋትን ለማምጣት ጥረት እንዲያደርግ ሕዝቡ አሳስቧል። አባ ጁሊዮ አልባነዚ በማከልም በዳርፉር ውስጥ በርካታ የጦር መሣሪያ እና የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች መኖራቸውን ገልጸው ክልሉ በነዳጅ ዘይት የበለፀገ በመሆኑ እነዚህ የተለያዩ ወገኖች በጋራ ለመሥራት ከተስማሙ ለአካባቢው ነዋሪዎች ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚቻል መሆኑን አስረድተው ነገር ግን ከፍተኛ ጥንቃቄን እና ተስፋን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የሱዳን መንግሥት

የቀድሞ የሱዳን መንግሥት ፕሬዚደንት ኦማር አል በሺር እ.አ.አ ሚያዚያ 11/2019 ዓ. ም.  ከስልጣን ከወረዱበት በኋላ የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት በአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት የማስከበር ሃላፊነት ይጠበቅበታል ተብሏል። አሜሪካ በቅርቡ ሱዳንን ለ27 ዓመታት ያህል ከያዘቻት የአሸባሪ አገሮች መዝገብ መሰረዟ ይታወሳል። ይህ ከሆነ ከሁለት ወር በኋላ ሱዳን ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በመመስረት ከአረብ ኤምሬቶች እና ባሕሬን ቀጥላ ሦስተኛ አገር መሆኗን ዋሽንግተን አስታውቋል። እስራኤል እና ሱዳን በቅርቡ ይፋ ባደረጉት የስምምነት ውል በመካከላቸው የሚኖረው ግንኙነት በቀዳሚነት በኤኮኖሚ፣ በንግድ እና በእርሻው ዘርፍ እንደሚሆን መግለጻቸው ታውቋል።

04 January 2021, 13:45