ፈልግ

ስደተኞች በነፍስ አድን ዕርዳታ ሰጭ ጀልባ ላይ ሆነው ስደተኞች በነፍስ አድን ዕርዳታ ሰጭ ጀልባ ላይ ሆነው 

ሊቀ ጳጳስ ሎሬፊቼ፥ ስደተኞችን ወደ መጡበት መመለስ እንዲያበቃ አሳሰቡ።

በቅርቡ በሜዲቴራኒያን ባሕር የተከሰተውን የሰው ሕይወት መጥፋት አደጋ ዜናን በመስማት፣ በጣሊያን የፓሌርሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኮራዶ ሎሬፊቼ፣ ድህነትን እና ጦርነትን ሸሽተው የሚሰደዱትን ሰዎች ሕይወት ለማዳን ሕዝባዊ ተቋማት እና የክርስቲያን ማኅበረሰብ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሁለት የባሕር ላይ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ አደጋ ላይ የወደቁ 265 ስደተኞችን በኤምፔዶለ ወደብ ወደሚገኝ ሰብዓዊ ዕርዳታን ወደሚያገኙበት ለይቶ ማቆያ ስፍራ ማጓጓዛቸው ታውቋል። ከዚህ በፊት በቆዩበት ሊቢያ ያጋጠማቸውን የስቃይ ሕይወት ከሸሹት መካከል 160 ስደተኞች በሊቢያ የድንበር ጠባቂ ወታደዎች ተይዘው ወደ መጡበት ሲመለሱ 13 ስደተኞች የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል።

ክርስቲያኖች የወንጌልን መልዕክት መዘነጋት የለባቸውም

በስደተኞች ላይ ለሚደርስ አደጋ ከሕዝባዊ ተቋማት እና ክርስቲያን ማኅበረሰብ ተገቢ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል በማለት በጣሊያን የፓሌርሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኮራዶ ሎሬፊቼ ጥሪ አቅርበው፣ አዲሱ የጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ. ም. የስደተኞችን ችግር በተመለከተ በአውሮፓ ሕብረት አገሮች በኩል ገንቢ ለውጥ የሚታይበት እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኮራዶ አክለውም በታህሳስ ወር አጋማሽ ላይ በሊቢያ የባሕር ጠረፍ ጠባቂ ወታደሮች አስገዳጅነት ከሸሹበት ወደኋላ እንዲመለሱ የተደረጉት 4 አዳጊ ሕጻናት በባሕር ሰምጠው መሞታቸው እና አስከሬናቸው በሊቢያ ባሕር ዳርቻ መገኘታቸው ገልጸው፣ የጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ. ም. በአውሮፓ ሕብረት አገሮች ዘንድ ገንቢ የሆኑ አዲስ ደንቦችን አውጥተው መልካም ለውጦችን የሚያመጡበት ዓመት እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። የዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች መዝገብ በሊቢያ ውስጥ 12 ሺህ ስደተኞች መኖራቸውን፣ 323 መሞታቸውን፣ 417 ስደተኞች የደረሱበት የማይታወቅ መኖራቸውን የሚያመለክት ሲሆን፣ ስደተኞችን ወደመጡበት መመለሱ በጀኔቭ የጸደቀውን ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ስምምነትን የሚጥስ፣ የቅዱስ ወንጌል መልዕክትን የሚዘነጋ እና ሰብዓዊ ወንድማማችነትን የሚክድ ድርግት መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኮራዶ አስረድተው፣ በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ የሚሞቱ ስደተኞች ሕይወት ከአደጋ ለማትረፍ የክርስቲያን ማኅበረሰብ እና መላው የአውሮፓ አገሮች ሃላፊነትን በመውሰድ፣ ስደትን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ውጤታማ ማላሽ ማግኘት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ሰዎች ከመኖሪያቸው የሚፈናቀሉት እና ወደ ሌላ አገር የሚሰደዱት ኤኮኖሚያዊ አለመመጣጠን እና ብዝበዛ የሚያስከትለውን ጦርነት እና ድህነት በመሸሽ ስለሆነ፣ የአውሮፓ ኅብረት አገሮችን ጨምሮ በኤኮኖሚ ያደጉት አገሮች ድሃ አገሮችን የመርዳት ሃላፊነት እንዳለባቸው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኮራዶ አሳስበው፣ አዲሱ የጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ. ም. ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበት፣ በኤኮኖሚ ያደጉት ምዕራባዊያን አገሮች በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮችን የማገዝ ሃላፊነታቸውን በተግባር የሚያሳዩበት እና የሰው ሕይወት ለሞት አደጋ  መጋለጡ የሚያበቃበት እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

አንድነትን እና ወንድማማችነት በተግባር ካልታየ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መላቀቅ እንደማይቻል የገለጡት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኮራዶ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማንም ቢሆን ብቻውን በሚያድረገው ጥረት ከዚህ ወረርሽኝ መዳን እንደማይች፣ ነገር ግን እርስ በእርስ በመረዳዳት ከችግር ሁሉ መውጣት እንደሚቻል መናገራቸውን አስታውሰዋል። ስደትም ቢሆን በጋራ ክንድ፣ እርስ በእርስ በመረዳዳት ማስወገድ የሚቻል ማኅበራዊ ችግር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል። በስደት ወቅት የሚሰቃዩት እና የሚሞቱት በሙሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መሆናቸውን፣ የሰው ልጅ መሆናቸውንም መዘነጋት የለብንም ብለዋል።

በደቡብ ጣሊያን፣ ሲሲሊ ክፍለ ሀገር ያለው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን መዘንጋት የለብንም ያሉት ብጹዕ አቡነ ኮራዶ፣ በተለይም በላምፔዱስ ወደብ የሚታየውን የስደተኞች ችግር መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል። አክለውም በሜዲቴራኒያን ባሕር በስደተኞች ሕይወት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ዕርዳታን በማቅረብ ላይ ለሚገኙ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ምስጋናቸውን አቅርበው በሀገረ ስብከታቸው የሚገኙ ቁምስናዎች እና ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በችግር ለሚገኙት ስደተኞች ለሚያደርጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። የቅዱስ ወንጌልን መልዕክት በተግባር የማትገልጽ ቤተክርስቲያን ተልዕኮዋን የዘነጋች መሆኗን ገልጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት ቤተክርስቲያን ከሁሉም በላይ የፍቅር መንገድን መጓዝ እንዳለባት አሳስበው፣ የሰውን ሕይወት ለሞት አሳልፎ መስጠት ለእግዚአብሔር የምንሰጠውን ምስክርነት እና እርስ በእርስ ተዋደዱ የሚለውን የእግዚአብሔር ትዕዛዝ የሚቃረን መሆኑን አስረድተዋል።                  

08 January 2021, 16:06