ፈልግ

ውዳሴ ላንተ የተሰኘ ማኅበር አገልግሎቱን በአዲስ ስብዕና መጀመሩን አስታወቀ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሰው ልጅ እና እርሱ በሚኖርበት አካባቢ የተፈጠረውን ከፍተኛ ቀውስ የሚመለከቱ የተቀናጁ ሥነ-ምህዳራዊ ሃሳቦችን “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው በኩል ለመላው ዓለም ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። “ስሎው ፉድ” የተባለ ማኅበር መስራች፣ የ “ቴራ ማድሬ” ወይም “እናት ምድር” እና “ውዳሴ ላንተ” የተሰኙ ማኅበራት አውታረመረብ አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ካርሎ ፔትሪኒ፣ ለግል ጥቅም እና ትርፍ ብቻ ከማሰብ ይልቅ በጋራ እና ተዛማጅነት ባላቸው ስነ-ምሕዳራዊ ጉዳዮች ላይ ማሰብ የሚጀምርበት ጊዜ መድረሱን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ትጉህ ተመራማሪ” ብለው የሚጠሯቸው ክቡር አቶ ካርሎ ፔትሪኒ ለፍጥረት ርኅሩህ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ቅን እና መልካም አመለካከት ስላላቸው ነው ተብሏል። የቀድሞ ኮሚኒስት ርዕዮተ ዓለምን ሲያራምዱ የነበሩት ክቡር አቶ ካርሎ ፔትሪኒ፣ ከዚህ አስተሳሰብ ተመልሰው እንደሆን በተጠየቁ ጊዜ “በተሰጠን ስጦታዎች ላይ ገደብ ማበጀት በጭራሽ አያስፈልግም” ካሉ በኋላ በተጨማሪም “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ሙሉ በሙሉ መሸነፋቸውንም ገልጸዋል።

አቶ ካርሎ ፔትሪኒ፣ መንግሥታዊ ያልሆነ “ስሎው ፉድ” የተባለ ዓለም አቀፍ ማኅበር መሥራች ናቸው። እ.አ.አ ከ1986 ዓ. ም. ጀምሮ ማኅበራቸው ለምግብ እና ለአምራች ማኅበረሰብ ክብርን በመስጠት፣ ሰዎች ለሚኖሩበት አካባቢ ያላቸውን ባሕላዊ አመለካከት እና የእንክብካቤ ዕውቀት ከፍተኛ ክብርን በመስጠት ይታወቃል። ይህን በማድረጉ ማኅበሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገትን በማሳየት ዛሬ በ150 አገሮች ውስጥ አገልግሎቱን በማቅረብ ላይ ይገኛል።

አቶ ካርሎ ፔትሪኒ፣ “ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚሰጠውን እንክብካቤ በማስመልከት ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ከተባለው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሲገልጹ፥ “የቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳን ሥነ ምህዳራዊ አመለካከትን በጥልቀት የሚለውጥ” ነው ብለዋል። አንዳንድ ሰዎች እንደሚናገሩት ሰነዱ ስለ ዕጽዋዕት ወይም ስለ አካባቢያዊ ሥነ-ምህዳር ብቻ የሚናገር ሳይሆን፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ መጨረሻ ስለ ማኅበራዊ ሕይወት የሚናገር ቃለ ምዕዳን መሆኑን አስረድተዋል። የተቀናጁ ሥነ-ምህዳራዊ ሃሳቦች፣ በሰው ልጅ እና በአካባቢው መካከል ያለውን ግንኙነት ከመመልከት በተጨማሪ በሁለቱ መካከል የተፈጠረውን ከፍተኛ ቀውስ ለማስረዳት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለመላው ዓለም ያበረከቱት ልዩ አስተንትኖ መሆኑን አቶ ካርሎ ፔትሪኒ ገልጸዋል።

የአቶ ካርሎ ፔትሪኒ ቁርጠኝነት

“ቴራ ማድሬ” ወይም “እናት ምድር” የተባለ ዓለም አቀፍ ማኅበር መስራች የሆኑት አቶ ካርሎ ፔትሪኒ፣ በማኅበራቸው አማካይነት ለገበሬዎች፣ ለዓሣ አጥማጆች፣ ለእንስሳት አርቢዎች እና ለዝቅተኛ ደረጃ አምራች ማኅበረሰብ ግንዛቤን በማስጨበጥ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከሁለት ዓመታት በፊት፣ በጣሊያን ውስጥ የሪኤቲ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ከሆኑት ከብጹዕ አቡነ ዶሜኒኮ ፖምፒሊ ጋር በመተባበር “ውዳሴ ላንተ” በሚል ስም የሚታወቅ ማኅበር በመመስረት፣ በአገር ውስጥ በ60 ማዕከላትን በማዋቀር፣ የተቀናጀ ሥነ-ምህዳራዊ ሃሳብን የሚገልጹ ቅስቀሳዎችን እና ስብሰባዎች በማካሄድ እንዲሁም ህትመቶች በማሰራጨት ዘላቂ የሆኑ ተጨባጭ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

ሁሉን አቀፍ እሴት

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን የታገዙ በርካታ መመሪያዎችን ያሳተሙት አቶ ካርሎ ፔትሪኒ፣ የተቀናጀ ሥነ-ምህዳራዊ ሃሳቦችን ያካፈሉትን ቅዱስነታቸውን አመስግነው፣ ሐዋርያዊ ምክራቸውን የሚጋሩ በርካታ ቤተሰቦች በሰሜን ጣሊያን ግዛቶች ውስጥ መኖራቸውን ተናግረዋል። እ.አ.አ መስከረም 12/2020 ዓ. ም. ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ” የተባለውን ማኅበርን በቫቲካን ውስጥ በክብር ተቀብለው ማስተናገዳቸውን አቶ ካርሎ ፔትሪኒ አስታውሰዋል። እ.አ.አ ከ2013 ዓ. ም. ወዲህ ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኝቶ ለመወያየት ሦስት አጋጣሚዎችን ያገኙት አቶ ካርሎ ፔትሪኒ፣ እ.አ.አ በ2019 በተካሄደው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መካፈላቸው ልዩ ደስታን ያስገኘላቸው መሆኑን “የወደ ፊት ምድራችን” የሚል አርዕስት በተሰጠው መጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የተሰኘውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን በማንበብ፣ ሰነዱ ለካቶሊካዊ ምዕመናን ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ ባካተታቸው ርዕሠ ጉዳዮች፣ አመለካከቶች እና የውይይት ዘዴዎች አማካይነት ሁሉን አቀፍ እሴቶችን ለመላው ዓለም የሚያቀርብ ሰነድ መሆኑን አቶ ካርሎ ፔትሪኒ አስረድተዋል።

እንደ አቶ ካርሎ ፔትሪኒ ገለጻ መሠረት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የምናደርገው እንክብካቤን፣ ውዳሴን ለእግዚአብሔር ከማቅረብ ጀምሮ አዲስ ስብዕናን በሕዝቦች መካከል በማስረጽ፣ በጥልቀት መፈተሽ ያለብን፣ አሁን እየኖርንበት ላለው የአከባቢ አደጋ መንስኤዎች መፈለግ ብቻ ሳይሆን ዘላቂነት የሌላቸው ማህበራዊ ሁኔታዎችንም መመልከት ያስፈልጋል ብለዋል። “ስሎው ፉድ” የተባለ ማኅበር መስራች የሆኑት ክቡር አቶ ካርሎ ፔትሪኒ፣ ለግል ጥቅም እና ትርፍ ብቻ ከማሰብ ይልቅ በጋራ እና ተዛማጅነት ባላቸው ስነ-ምሕዳራዊ ጉዳዮች ላይ ማሰብ የሚጀምርበት ጊዜ መድረሱንም አስታውሰዋል። 

ትናንሽ ነገሮች ለውጥን ለማምጣት አስፈላጊ ናቸው

አቶ ካርሎ ፔትሪኒ በገለጻቸው የዛሬዎችን ተግዳሮቶች ከመጋፈጥ አንስቶ አካባቢያዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች እና እየተከሰቱ ያሉት ቀውሶች የሚያሳስባቸው መሆኑን አስረድተዋል። በማከልም “የወደ ፊት ምድራችን” የተሰኘው መጽሐፋቸው ችግሮችን ለመቋቋም ማኅበራዊ ጥረቶች እንዲደረጉ ከማሳሰቡም በተጨማሪ እየደረሱ ያሉትን ቀውሶች በገሃድ ማሳወቅ የሚገባው ለባሕላዊ እና ፖለቲካ ዓለም ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ ግለ ሰብ መሆን እንዳለበት አሳስበው፣ እያንዳንዱ ትናንሽ ነገር ለለውጥ ወሳኝ ዕድሎችን ሊያመቻቹ ይችላሉ ብለዋል። አቶ ካርሎ ፔትሪኒ አክለውም እያንዳንዱ ግለ ሰብ ከዕለታዊ ሕይወቱ ጀምሮ የለውጥ አራማጅ  እንዲሆን ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውበት የሚገለጸው ግለ ሰቦች ለለውጥ ያላቸውን ፍላጎት ወደ ጎን በማለት ሳይሆን በማበረታታት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያድግ በማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

መሰናክሎችን ማሸነፍ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ ከፈጣሪያችን፣ ከሰዎች እና ከፍጥረት ጋር ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነታችን መልሰን እንድንጠግን የሚጋብዝ መሆኑን አስታውሰው፣ አንድነትን በማጠናክር፣ ካቶሊካዊው ማኅበረሰብ ከተቀረው ዓለም ጋር ተገናኝቶ ሰላማዊ የጋራ ውይይቶችን የሚያደርግበት ጊዜ መድረሱን አስረድተዋል። “ውዳሴ ላንተ” የተሰኘ ማኅበራቸው፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋች ግሬታ ቱንበርግን ጨምሮ የሌሎች በርካታ ወጣቶች ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን እና ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ምሕዳርን በማስፋት መሰናክሎችን ማሸነፍ የሚቻልበት ዕድል መኖሩን አስረድተዋል።

የልዩ ልዩ ቫይረሶች መገኘት እና ጥልቅ ለውጥ ማስፈለጉ         

የሰው ልጅ በኮቪድ-19 እና በሌሎች ወረርሽኞች መጨፍለቁን አስመልክተው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መናገራቸውን በመጽሐፋቸው የጠቀሱት አቶ ካርሎ ፔትሪኒ፣ በተሳሳተ የኤኮኖሚ ሥርዓት፣ አመጽ በበዛበት እና ፍትህ በጎደለበት ሥርዓት፣ ክቡር የሆነው የሰው ነፍስ እንደ እንስሳ ለሞት በሚዳረግበት እና እንደ እንሳሳ በሚኖሩበት ዘመን፣ ካለንበት ወጥተን በበርካታ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መመልከት የወደፊት የሥራ ድርሻችን መሆኑን አስረድተዋል። “የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአስቸጋሪ ምርጫዎች ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል ያሉትን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ መልዕክት ያስታወሱት አቶ ካርሎ ፔትሪኒ፣  “ከወረርሽኙ በፊት የነበሩትን ንድፎች እና እሴቶች እንደገና በመገንባት ከዚህ ሁኔታ እንወጣለን ብሎ የሚያስብ ሁሉ በእኔ እምነት የተሳሳተ ነው” ብለው ጥልቅ ለውጥን ለማምጣት የሚያስችሉ እድሎችን በመጠቀም፣ በአካባቢ እና በኤኮኖሚ ለውጥ ላይ የግል እና የጋራ ኃላፊነትን በመውሰድ በአዲስ የውይይት እና የማዳመጥ አቅም ትክክለኛ ዘዴን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

30 January 2021, 16:02