ፈልግ

ነፍሳት ተክልን ለሕይወት ማቆያ ይጠቀሙታል፤ ነፍሳት ተክልን ለሕይወት ማቆያ ይጠቀሙታል፤ 

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የእግዚአብሔር ቁጣ ሳይሆን የተስፋ ጥሪ መሆኑ ተገለጸ

በክርስቲያኖች መካከል ውህደትን ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርተሎሜዎስ 1ኛ፣ የቱርክ ደሴት በሆነችው ሃልኪ በተካሄደው አራተኛ ዙር አከባቢያዊ ጥበቃ ጉባኤ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የእግዚአብሔር ቁጣ ሳይሆን ለአከባቢያችን የበለጠ ክብር እንድንሰጥ የሚያሳስበን የተስፋ ጥሪ” ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቁስጥንጥንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ 1ኛ፣ ማክሰኛ ጥር 18/2013 ዓ. ም. በሃልኪ ደሴት በተካሄደው የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት መልዕክታቸው፣ ሥነ ምህዳራዊ ቀውስን መቀየር የሚቻለው ለፍጥረታት የምንሰጠውን ጥበቃ እና እንክብካቤ በዘላቂነት ማሳደግ ስንችል ነው በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ለምድራችን መስዋዕትነት መክፈል ካለመፈለግ የመጣ ነው

ከተለያዩ አገሮች የመጡ ባለሞያዎች በተገኙበት ጉባኤ ላይ የተገኙት የቁስጥንጥንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ 1ኛ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በጋራ መኖሪያ ምድራችን ሕይወት ላይ ካለው እንድምታ ጋር በማዛመድ ሞያተኞቹ ሃሳባቸውን እንዲለዋወጡ ጋብዘዋል። አራተኛው ዙር የሃልኪ ጉባኤ በዋናነት የሚያተኩረው ጉዳዩ በሚመለከታቸው ባለድርሻ ወገኖች መካከል በሚደረጉ የውይይት እሴቶች እና ኅብረት ላይ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ባሁኑ ወቅት እነዚህ እሴቶችም ሳይቀሩ በዓለም አቀፉ ቫይረሱ መጠቃታቸው የጉባኤው ተካፋዮች አስተውለዋል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርተሎሜዎስ 1ኛ አክለውም የአየር ንብረት ለውጡን ወደ ነበረበት መመለስ የሚቻለው ለዓለማችን ባለን አስተሳሰብ እና በምናደርገው እንክብካቤ ጠቅላላ ለውጥን ማሳየት ስንችል ነው ብለው፣ ችግሩ የሚጀምረው ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እና ለሌሎች ደህንነት ሲባል መስዋዕትነትን መክፈል ካለመፈለግ መሆኑን አስረድተዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ካለ እድገት አለ

የቁስጥንጥንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ 1ኛ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የእርስ በእርስ መደማመጥ እና አንዱ ከሌላው መማማር አስፈላጊነትን አሳይቶናል ካሉ በኋላ በተጨማሪም የፍቅርን እና የመተጋገዝ ኃይልን በግልጽ አሳይቶናል ብለዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጋራ የምንኖርበት ዓለማችን ከጭንቀታችን እና ከግል ምኞታችን፣ ከቤተ ክርስቲያናችን እና ከእምነት ማኅበረሰብም፣ ከፖለቲካ ባለ ስልጣናት እና ብሔራዊ ጥቅም እጅግ እንደሚበልጥ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርተሎሜዎስ 1ኛ አስረድተዋል። አክለውም “በየቤቶቻችን ተዘግተ በቆየንባቸው ወራት የታየው የአየር ብክለት መቀነስ፣ ተፈጥሮአዊ አከባቢን ለጥፋት በማጋለጥ የሚመጣ እድገት እውነተኛ እድገትን ሊያመጣ እንደማይችል ማረጋገጫ አሳይቶናል” ብለዋል።

በቀል መውሰድ ሳይሆን እርዳታ መጠየቅ ያስፈልጋል

የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግንኙነት ያታወሱት ፓትሪያርክ በርተሎሜዎስ 1ኛ፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮ መካከል ከመጠን ያለፈ ጣልቃ በመግባት፣ ሕገ ወጥ የደን ጭፍጨፋን በማካሄድ፣ ምድርን በማራቆት፣ ከተሞችን በማስፋፋት፣ ሰፋፍፊ የእርሻ መሬቶችን በመሸንሸን፣ ፈጣን ተላላፊ በሽታዎችን ሰውን ጨምሮ ከእንስሳት ወደ እንስሳት በማስተላለፍ ላይ መሆኑን አስታውሰው፣ የስነ-ምሕዳር ለውጥ በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን፣ በዱር እንስሳት የሚተላለፉ በሽታዎች መጨመር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከሚመጣው የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ ከሚያደርገው ወረራ እና ከፈጣን የአየር ንብረት ለውጥ ጋር አብረው የተከሰቱ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ብጹዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊ ለጉባኤው ተካፋዮች ያቀረቡትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት፣ “የኮቪድ-19 ወረርሽኝም ከእግዚአብሔር በኩል የተላከ ቁጣ ሳይሆን ነገር ግን በሁላችን በኩል ለተፈጥሮ የበለጠ አክብሮት የተሞላበት አቀራረብን እንድናደርግ የተላከ የተስፋ ጥሪ ነው” ብለዋል።

28 January 2021, 14:33