በማሊ የሰላም ድርድር እንዲደረግ የይሐማኖት መሪዎች ጠየቁ።
በምዕራብ አፍሪቃ አገር ማሊ የተፈጠረውን ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ለማረጋጋት በአገሪቱ የሚገኙ የሐይማኖት መሪዎች የጋራ ውይይት እንዲደረግ በማለት ጥሪ አቅርበዋል። ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች እስካሁን የአሥራ አንድ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ታውቋል። በሚቀጥሉት ቀናት ሌሎች ሰልፍችን ለማካሄድ እቅድ የተያዘለት ሲሆን፣ በአገሪቱ የሚገኙ የሐይማኖት መሪዎች በአመጽ ተጨማሪ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ እና ንብረት እንዳይወድም ማሳሰባቸውን የአፍሪቃ ፖለቲካን እና ኤኮኖሚ ጉዳዮችን የሚከታተል አቶ ሉቺያኖ አርዴሲ አስታውቋል።
የቫቲካን ዜና፤
ባለፉት ቀናት ውስጥ ታላቅ ቁጣ የታየበት ሕዝባዊ አመጽ በማሊ ዋና ከተማ ባማኮ ከተካሄደ በኋላ የአገሪቱ እስላማዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ ሼሪፍ ኡስማን ማዳኒሃይዳራ፣ የባማኮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ዜርቦ እና የማሊ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚደንት አቶ ኑሁ አግ ኢንፋያታራ በጋራ ሆነው በአገሪቱ ብዙሃን መገናኛ በኩል መልዕክት ማስተላለፋቸው ታውቋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ዜርቦ በመልዕክታቸው፣ በዋና ከተማዋ ባማኮ በተቀሰቀሰው አምጽ ምክንያት የሰው ሕይወት መጥፋቱ ያሳዘናቸው መሆኑን ገልጸዋል። “በማሊ ይህ አደጋ ሊከሰት ፈጽሞ አይገባም ነበር” ካሉ በኋላ የጋራ ውይይቶችን በማካሄድ ሰላምን መፍጠር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የአገሪቱ እስላማዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሼሪፍ ኡስማን በበኩላቸው፣ አመጽ አገርን ወደ ባሰ ጥፋት ከመምራት ባሻገር ምንም ውጤት አይኖረውም በማለት አስርድተዋል። ዜጎች እንዲረጋጉ እና በሕዝብ መካከል ለሚነሱ ችግሮች በጋራ ውይይት መፍትሄን ማግኘት የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል። ሼሪፍ ኡስማን አክለውም መንግሥት ሃላፊነቱን እንዲወጣ፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በአግባቡ መከናወናቸውን እንዲያረጋግጥ እና ያሰሯቸውን የተቃዋሚ እንቅስቃሴ አባላት እንዲፈቱ በማለት ጠይቀዋል። የማሊ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚደንት አቶ ኑሁ አግ ኢንፋያታራ በበኩላቸው በአገሪቱ የሚገኙ ክርስቲያኖች ተባብረው ለሰላም እንዲጸልዩ፣ ሐዘን ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን እና የቆሰሉትንም በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ለተፈጠሩት ማኅበራዊ ቀውሶች መፍትሄን ለማግኘት ወደ አደባባይ ወጥተው ለመታሰር የበቁት ሰዎች እንዲለቀቁ፣ የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ እንዲሻሻል፣ ሙስና እንዲወገድ፣ አገልግሎት ያቋረጡ ትምህርት ቤቶች እና የሕክምና ማዕከላት እንዲከፈቱ በማለት ለአገሪቱ ፕሬዚደንት ኢብራሒም ቡባካር ጥያቄዎች መቅረባቸው ታውቋል። ኤኮኖሚያዊ ቀውስ በገጠማት ማሊ ተቃዋሚዎቻቸውን ለማዳከም በሚል ዓላማ ፕሬዚደንት ኢብራሂም ቡባካር የመንግሥታቸውን ፓርላማ በመበተን ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት መመስረታቸው፣ በአገሪቱ የአሸባሪዎች ጥቃት እንዲስፋፋ እና አመጽ እንዲቀሰቀስ ማድረጉ ታውቋል። በዚህም በርካታ ሰዎች መቁሰላቸው እና መታሰራቸው ታውቋል። ከሐምሌ 8/2012 ዓ. ም. ጀምሮ ሌሎች ሰልፎችን ለማካሄድ ዕቅድ መያዙ ታውቋል። በሌላ ወገን የአገሪቱ ፕሬዚደንት ኢብራሒም ቡባካር፣ ባለፈው መጋቢት ወር በተካሄደው ምርጫ ውጤት ላይ ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሄ ለማግኘት የሚጥር ህገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት እንዲቋቋም ማድረጋቸው ታውቋል።
የሐይማኖት መሪዎች መልዕክት አስፈላጊነት፤
በማሊ ከሚገኙ ከፍተኛ የሐይማኖት መሪዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች የቀረበው ጥያቄ በጎ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚችል፣ በሕዝብ ዘንድ የተቀሰቀሰው አመጽ ሊበርድ እንደሚች የአፍሪቃ አህጉር የቅርብ ታዛቢ የሆኑት አቶ ሉቺያኖ አርዴሲ አስታውቀዋል። ፕሬዚደንት ኢብራሒም ቡባካር አዲስ ፍርድ ቤትን ቢያቋቋሙም ሕዝባዊ ሰልፍ አያቋርጥም ያሉት አቶ ሉቺያኖ፣ እስካሁን ሰልፈኞቹ ያቀረቡት ጥያቄዎች ጥቂት ቢሆኑም ፕሬዚደንቱ ከስልጣን እንዲወርዱ የቀረበው ጥያቄ እና ሌሎች ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ የሚያገኙ አለመሆኑን አቶ ሉቺያኖ አስረድተዋል።
አስቸጋሪ ውይይት ይሆናል፤
በኢማም ማሕሙድ ዲኮ የሚመራው እና የአገሪቱ ፕሬዚደንት ከስልጣን እንዲወርዱ፣ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍሎች አመጾችን በመቀስቀስ የሕዝቡን ጸጥታ የሚነሱ ታጣቂ የጎሳ ቡድኖችን እና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸውን እስላማዊ አሸባሪዎችን መንግሥት ትጥቅ እንያስፈታ፣ በአገሪቱ የተስፋፋው ሙስና እንዲወገድ እና ከፍተኛ ቀውስ ላጋጠመው የአገሪቱ ኤኮኖሚ መልስ እንዲሰጠው የሚሉ ጥያቄዎች ለፕሬዚደንት ኢብራሒም ቡባካር መቅረባቸው ታውቋል። በሌላ ወገን ዓለምን በከባድ አደጋ ውስጥ በጣለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በማሊ ወደ ሦስት ሽህ የሚጠጉ ሰዎችን ማጥቃቱ እና መቶ ሃያ ሁለት ለሞት መዳረጉ ታውቋል። በአገሪቱ የሚገኙ የፈረንሳይ ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ባለፈው ሰኔ ወር ውስጥ፣ ማሊን ጨምሮ በአካባቢ አገሮች የሚንቀሳቀስ የአልቃይዳ አሸባሪ ቡድን መሪ፣ አብደልማሌክ ድሩክዴልን መግደላቸው ይታወሳል።