ፈልግ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ዓለማችን ለውጥ የሚያስፈልገው መሆኑን አስታወቀ።

የተበበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ የጸደቀበት 75ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ዓለማችን ለውጥ የሚያስፈልገው መሆኑን አስታውቀዋል። የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ከ75 ዓመት በፊት በሰሜን አሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ሰኔ 26/1945 ዓ. ም. መጽደቁ ይታወሳል።

የቫቲካን ዜና፤

ወቅቱ ዓለማችን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለመውጣት በአዲስ መንፈስ የተነሳሳበት፣ በጦርነት የወደሙ ተቋማትን መልሶ መገንባት የጀመረበት ወቅት እንደ ነበር ይታወሳል። ይህን የሰላም እና የዕድገት ዓላማን የሚደግፉ አገራት ተባብረው የለውጥ ተስፋን በመያዝ የጦርነት አስከፊ ገጽታን ለመለወጥ፣ ከጨለማ ሕይወት ለመውጣት የተነሱበት ወቅት መሆኑ ይታወሳል። ከዚህም በተጨማሪ ለሰው ልጅ ክብርን በመስጠት መሠረታዊ ሰብዓዊ መቶችንም ለማረጋገጥ፣ ባደጉት እና በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ውስጥ የወንዶችን እና የሴቶችን እኩልነት በማረጋገጥ ማኅበራዊ ዕድገት እና ነጻነት ለማምጣት ጥረቶች የተጀመረበት ወቅት መሆኑ ይታወሳል። በሃያዎቹ ዓመታት ውስጥ በአገር ደረጃ ከተዋቀሩ አንዳንድ ማኅበራዊ ድርጅቶች ሌላ፣ መልካም ውጤቶችን ሊያመጣ እንደሚችል ታምኖበት፣ ጸጥታን የሚያስከብሩ፣ ድምጽን በድምጽ ለመሻር መብት የተሰጣቸው አምስት ቋሚ አባል አገሮች የሚገኙበት የጸጥታው ምክር ቤት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመስረቱ ይታወሳል።

ከ75 ዓመታት ጉዞ በኋላም ዓለማችንን ከተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ማውጣት አለተቻለም ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን እያስከተለው ያለውን ከፍተኛ ቀውስ በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፣ በወረርሽኝ ምክንያት ዓለማችን ከ75 ዓመት በፊት ወደ ነበረበት ደረጃ መመለስ የሌለበት መሆኑን አስረድተው፣ አሁን ለደረሰው ቀውስ በቀዳሚነት ምክንያቶችን ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ትኩረት ተሰጥቶበት መሠራት ያለበት በጤናው ዘርፍ መሆኑን የገለጹት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ በአገሮች እና በሕዝቦች መካከል ዘላቂ ግንኙነትን ማሳደግ እና የኤኮኖሚ አለመመጣጠንን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለማችንን እያስጨነቀ በሚገኝበት ባሁኑ ጊዜ፣ በጦርነት ተጠምደው በሚገኙ አገሮች ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ያሳሰቡት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳሳሰቡት ሁሉ  የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ በማለት 180 አገሮች ስምምነት ላይ ቢደርሱም፣ ጦር መሣሪያን ያነገቡ፣ በቁጥር 20 የሚሆኑ ታጣቂ ቡድኖች በዓለማችን ውስጥ መኖራቸውን አስታውቀዋል። በየመን እና በሊቢያ ውስጥ የሚካሄዱትን ጦርነቶች ያስታወሱት ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ በእነዚህ ሁለት አገሮች የሚካሄዱ ጦርነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መምጣታቸውን ገልጸዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው እንደገለጹት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለማችን በ83 አገሮች ውስጥ በረሃብ ለሚሰቃዩ 87 ሚሊዮን ሰዎች በየዓመቱ የምግብ እና የጤና አገልግሎት ዕርዳታን በማቅረብ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ድርጅታቸው ለ80 ሚሊዮን ስደተኞች እና ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ዕርዳታን በማቅረብ ላይ መሆኑን ገልጸው ከእነዚህም መካከል ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ እርጉዝ እናቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ አክለውም በዓለማች ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ጸጥታን በማስከበር አገልግሎት ተሰማርተው የሚገኙ 40 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጸጥታ አስከባሪ ተልዕኮ ፈጻሚ ቡድኖች መኖራቸውን ተናግረዋል።              

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመተዳደሪያ ደንብ የጸደቀበትን 75ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ትናንት ሰኔ 19/2012 ዓ. ም. በቪዲዮ ኮንፈንስ አማካይነት ለመወያየት የተቀመጠው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ፣ በመተዳደሪያ ደንብ ላይ ተሻሽሎ በማድረግ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር መስከረም 20/2020 ዓ. ም. እንዲያቀርብ ከተመደበው ከፍተኛ “UN75” ተብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር በተመሳሳይ ዕለት ጉባኤያቸውን ማካሄዳቸው ታውቋል።  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤን የመሩት የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴረዝ፣ የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም. በሰብዓዊ ቤተሰቦች መካከል የጋራ ውይይት የሚደረግበት፣ ለወደ ፊት መልካም ዕድል ተስፋ የተጣለበት መሆኑን አስረድተዋል።

ከ75 ዓመት በፊት የጸደቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ፣ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች 70 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወታቸውን ካጡ በኋላ የጸደቀ መሆኑን የገለጹት፣ በጣሊያን ብሔራዊ የሰላም ድርድር አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ፍላቪዮ ሎቲ፣ የጦርነትን አስከፊነት በመገንዘብ ለሰላም የቆሙ በጣሊያ የሚገኙ በቁጥር 100 የሚሆኑ ማዘጋጃ ቤቶች እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ጥቅምት 11/2020 ዓ. ም. ወደ አሲሲ ከተማ የሰላም ጉዞን ለማድረግ ያቀዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

27 June 2020, 19:26