ፈልግ

የቤተሰብ አንድነት፤ የቤተሰብ አንድነት፤ 

“ቤተሰባችን”፥ የቤተሰብ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት።

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን በዚህ ዝግጅት የቤተሰብን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት የሚመለከት አጭር ጽሑፍ እናቀርብላችኋለን

በአንድ አገር ውስጥ የማኅበራዊ ተቋማት መኖር ያስፈለገበት ምክንያት ከሁሉ አስቀድሞ የሰውን ልጅ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች የሚመለክቱ ማኅበራትን በማደራጀት ተግባራዊነታቸውን ለመከታተል እና ለማስፈጸም ነው። ማኅበራዊ ተቋማት የምንላቸው የፖለቲካ ተቋም፣ የትምህርት ተቋም፣ የኤኮኖሚ ተቋም፣ የቤተሰብ ተቋም እና የሐይማኖት ተቋም ናቸው። እነዚህ ተቋማት በመካከላቸው ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ከግለ ሰብ ሕይወት አንስቶ ማኅበራዊ ሕይወትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖን ያበረክታሉ። የተመሠረቱበት ዓላማም በሰዎች መካከል ልዩነት ሳያደረጉ የእያንዳንዱ ሰው መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ፍላጎት በመልካም ደረጃ ላይ መኖሩን ለማረጋገጥ ነው።  

የቤተሰብን ሕይወት በድህነት፣ በበሽታ፣ በጦርነት፣ የትዳር ሕይወት በመቃወስ፣ በመገለል፣ በተፈጥሮ አደጋ እና በሌሎች ችግሮች አደጋ ሊደርስበት ይችላል። ቤተሰብ ለማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ከፍተኛ በመሆኑ ነው። መንግሥታዊ እና ሐይማኖታዊ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊ ተቋማት የቤተሰብን ሕይወት የመንከባከብ እና የማጠናከር እንዲሁም ደህንነቱ የመጠበቅ ሃላፊነት አለባቸው። ቤተሰብ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሊያጋጥሙት የሚችሉ የተለያዩ ችግሮችን በጋራ እየተወጣ፣ በሚገኝበትም ማኅበረሰብ ውስጥ ጠቃሚ ተግባራትን እንዲያበረክት የተዋቀረ፣ በማኅበራዊ ዘርፎች በንቃት በመሳተፍ ለእድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖን ማበርከት የሚችል የኅብረተሰብ መሠረት ነው።

አንድ ቤተሰብ ለሕይወቱ ዘላቂነት ብቻውን የሚያደርገው ጥረት በቂ አይደለም። በቤተሰብ ቡድኖች መካከል እርስ በእርስ መነጋገር፣ መመካከር እና መተጋገዝ ሊኖር ይገባል። ለአንዳንድ የቤተሰብ ክፍሎች ትልቅ ስጋት እየሆነ የመጣው የብቸኝነት ሕይወት ነው። የቤተሰብ ብቸኝነት በገንዘብ አቅም ማነስ ወይም በመገለል ብቻ የሚከሰት ሳይሆን በሰዎች መካከል ሊኖር የሚገባ ግንኙነት ሲቀንስ የሚመጣ ብቸኝነት ነው። የሰው ልጅ ለማኅበራዊ ሕይወት የተፈጠረ በመሆኑ የብቸኝነትን ሕይወትን ከባድ ይሆንበታል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ዓይነት የብቸኝነት ሕይወት መንፈሳዊ ድርቀት ወይም መንፈሳዊ መራቆት ይሉታል።  

የቤተሰብ ሕይወት የሚገኝበትን ደረጃ በማጤን ድጋፍን ከሚሰጡ፣ እንክብካቤንና ጥበቃን ከሚያደርጉ ማኅበራዊ ተቋማት በተጨማሪ ቤተሰብ ለቤተሰብ የሚያደርገው እገዛ ትልቅ ውጤት አለው። የቤተሰብን ሕይወት ለማሳደግ ከተሰማሩት ማኅበራዊ ተቋማት በተጨማሪ አንድ ቤተሰብ ከሌላ ቤተሰብ ጋር፣ ከሌላ ጎረቤት ጋር ያለው ግንኙነት ቤተሰብን ከስጋት እና ከጭንቀት ሕይወት ለማውጣት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” በማለት ባስተላለፉት የድሕረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው “የምንወዳቸውን ሰዎች በእግዚአብሔር ዓይን ማሰላሰል እና በእነርሱ ውስጥ ክርስቶስን ማየት ጥልቅ መንፈሳዊነት ተሞክሮ ነው። ይህም የእነርሱን ክብር እንድናደንቅ የሚያደርገን ነጻነትና ግልጽነት እንዲኖር ይፈልጋል። ለሌሎች ሙሉ ለሙሉ አለኝታ መሆን የምንችለው ራሳችንን ሙሉ ለሙሉ ስነሰጥና ሌላውን ስንረዳ ነው። የምንወዳቸው ሰዎች የእኛን ሙሉ ትኩረት ይሻሉ። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ምሳሌያችን ነው። ምክንያቱም ሰዎች ከእርሱ ጋር ለመነጋገር በቀረቡ ጊዜ ሁሉ በፍቅር እና በቀጥታ አተኩሮ ያያቸው ነበር። የእርሱ ቃላት እና እንቅስቃሴዎች “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” የሚል ጥያቄ የሚያስተላልፉ ስለ ሆኑ፣ ከእርሱ መገኘት ተገለልኩ ብሎ የሚያስብ ሰው አልነበረም። እኛም በቤተሰብ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ በየቀኑ የምናገኘው ይህን ነው። ከእኛ ጋር የሚኖሩ ሁሉ ሙሉ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ሁል ጊዜ ማሰብ ይኖርብናል። ምክንያቱም እያንዳንዳቸው የአብ ጥልቅ ፍቅር የሚንጸባርቅባቸው እና ገደብ የሌለው ክብር የተጎናጸፉ ናቸው። ርኅራሄ በተለየ መንገድ የሚገለጸው የሌላውን ሰው ውስንነቶች፣ በተለይም ግልጽ የሆኑ ውስንነቶች በፍቅር እና በእንክብካቤ በመያዝ ነው።

በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ቤተሰብ ሕይወትን ለመቀበል ዝግጁ የሚሆነው በራሱ ውስጥ ሕይወትን በመዝራት ብቻ ሳይሆን ከዚያ ወጣ ብሎ ሌሎችን በመንከባከብና የእነርሱንም ደስታ በመሻት ነው። ይህ ግልጽነት በተለይ የሚገለጸው ከዚህ በፊት የማናውቃቸውን ሰዎች በእንግድነት ስንቀበላቸው ነው። ይህም የሆነው “እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ ሳያውቁ መላእክትን አስተናግደዋልና (ዕብ. 13፡2) በማለት የእግዚአብሔር ቃል ስለሚያበረታታ ነው። አንድ ቤተሰብ ሌሎችን፣ በተለይም ድሆችን እና የተናቁትን የሚቀበል እና የሚያስተናግድ ከሆነ የቤተክርስቲያን ተምሳሌት፣ ምስክርና ተሳታፊ ይሆናል። የቤተሰብን መንፈሳዊ ትርጉምና ለሌሎች ያለውን ተልዕኮ በእውነት የሚያስተሳስረው የቅድስት ስላሴ ነጸብራቅ የሆነው ማኅበራዊ ፍቅር ነው። ምክንያቱም ማኅበራዊ ፍቅር በማኅበራዊ ግዴታዎቹ ሁሉ ውስጥ ስብከተ ወንጌል እንዲኖር ያደርጋል። ቤተሰብ መንፈሳዊነቱን ተግባራዊ ማድረግ የሚችለው በአንድ ጊዜ የቤት ውስጥ ቤተክርስቲያንም ዓለምን ለመለወጥ የሚያስችል ዋና ሕዋስም ሲሆን ነው። (“ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” 323-324)    

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን፣ የቤተሰብን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት  የሚመለከት ሳምንታዊ ጽሑፍ በዚህ እናጠቃልላለን። ሳምንት በምናቀርብላችሁ ጽሑፍ ተመልሰን  እስከምንገናኝ ሰላምን እና ፍቅርን ፍቅር ይብዛላችሁ።

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን።    

29 June 2020, 18:39