ፈልግ

ቤተሰብ በኅብረት የሚሆኑበትን ጊዜ አግኝተው፤ ቤተሰብ በኅብረት የሚሆኑበትን ጊዜ አግኝተው፤ 

“ቤተሰባችን”፥ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የቤተሰብ ሚና።

ክቡራት እና ክቡራን የ “ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን፣ በዚህ ዝግጅት የቤተሰብን ጠቅላላ ሕይወት በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ ትምህርቶችን እና አስተያየቶችን ስንካፍላችሁ መቆየታችን ይታወሳል። በዛሬው ዝግጅታችንም “በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የቤተሰብ ሚና” በሚል ርዕስ የተጋጀውን ጽሑፍ እናቀርብላችኋለን።

በዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ የሆኑ ሁለት ነገሮችን እንመለክታለን። እነርሱም ማኅበራዊ ሕይወት እና የቤተሰብ ሚና የሚሉ ናቸው። ሁለቱም በመካከላቸው ሰፊ ግንኙነት ያላቸው፣ እርስ በእርስ የሚደጋገፉ ናቸው። ያለ ቤተሰብ ተሳትፎ ማኅበራዊ ሕይወትን መመስረት እንደማይቻል ሁሉ ያለ ማኅበራዊ ድጋፍ የቤተሰብን ሕይወት ማሳደግ አይቻልም። ማኅበራዊ ሕይወትን የሚገልጹ በርካታ አስተያየቶችን ማቅረብ ይቻላል። የሚከተለውን አስተያየት እንመልከት። ማኅበራዊ ሕይወት በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ወይም ሕዝቦች ለኑሮ የሚጠቅሙ ባሕላዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሐይማኖታዊ እሴቶችን እየተጋሩ የሚኖሩበት የጋራ ሕይወት ነው። ለማኅበራዊ ሕይወት የሚጠቅሙ እሴቶች የሚገኙባቸውን ማኅበራዊ ተቋማት ከጠቀስን እሴቶቻቸውን በሦስት ዋና ዋና መሠረትዊ ነጥቦች ከፍለን እንመለከታቸዋለን። 1ኛ የሰውን ልጅ መሠረታዊ መብቶች ማክበር እና ማዳበር፣ 2ኛ የኅብረተሰብ ዓለማዊ እና መንፈሳዊ ጥቅሞችን ማሳደግ፣ 3ኛ የአባላቱን ሰላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ የሚሉ ናቸው(የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 1925)።

 

የሰው ልጅ መሠረታዊ መብቶች ማክበር እና ማዳበር፣  

ማኅበራዊ ሕይወትን ለማሳደግ ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር እና ማስከበር እጅግ አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ ሰው እኩል ሰብዓዊ መብት አለው ሲባል፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኝ ሰው የዘር፣ የጾታ፣ የሐይማኖት፣ ልዩነት ሳይደረግበት፣ ከማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚነት እስከ ተፈጥሮ ሃብት ክፍፍል ድረስ እኩል የመጠቀም መብት ማስ­­­­­ጠበቅ ማለት ነው። በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ከሕጻን እስከ አዋቂ በስብዕናው ማገኘት የሚገባውን መሠረታዊ ጥቅሞች፣ ከሁሉም በላይ የምግብ፣ የመጠለያ እና የልብስ አቅርቦት ዋስትናን ማረጋግጥ ያስፈልጋል። በብዙ አካባቢዎች ለማኅበራዊ ሕይወት መናጋት ዋና ምክንያቱ መሠረታዊው የሰው ልጅ መብት አለመከበር ነው። ሕዝቦች የጎሳ እና የዘር፣ የፖለቲካ እና የሐይማኖት ልዩነቶችን እንደ መልካም ማኅበራዊ እሴቶች ካለተመከቷቸው እና አንዱ በሌላው ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት የሚጠቀሟቸው ከሆነ የሰብዓዊ መብቶች ተግባራዊነት አደጋ ላይ ይወድቃል።

ከሰብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ የእምነት ነጻነት ነው። በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የእያንዳንዱ ሰው የእምነት ነጻነት የተከበረ መሆን ይኖርበታል። ይህ ነጻነት ከግለሰቦች እና ከማኅበራዊ ቡድኖች ተጽዕኖ እና ጭቆና ነጻ መሆን ይኖርበታል። ይህ ማለት ማንም ሰው ሆነ ቡድን ከሚፈልገው እና ከመረጠው የእምነት መንገድ በተለየ ሁኔታ እንዲያምን መገደድ የለበትም ወይም እና ጫና ሊደረግበት አይገባውም ማለት ነው። የእምነት ነጻነት ሕልውናን ያገኘው ከዋናው ሰብዓዊ መብት አጠባበቅ በመሆኑ በሕገ-መንግሥትም እውቅናን ሊያገኝ ይገባል። ሰብዓዊ መብትን መሠረት ያደረገ እምነትን የመግለጽ መብት በነጻነት እና በሙሉ ፍላጎት፣ ሃላፊነት በተመላ መንገድ፣ በስነ ምግባር በመታገዝ፣ እውነተኛውን መንገድን በመከተል፣ በተለይም ሐይማኖታዊ እውነትን ተከትሎ የሚገለጽ መሆን ይኖርበታል። እምነትን መግለጽ በሰብዓዊ ማኅበረሰብ የሚተገበር በመሆኑ በእርግጥ አንዳንድ ደንቦችን እና መመሪያዎችን ያገናዘበ ወይም ያከበረ መሆን ይኖርበታል። ማንኛውም ዓይነት ነጻነት የጋራ እና የግል ስነ ሞራላዊ ሃላፊነት ሊኖረው ይገባል። ነጻነት በተግባር በሚተረጎምበት ጊዜ እያንዳንዱ ግለሰብ ሆነ ማኅበራዊ ድርጅቶች ሞራላዊ ሕጎችን በመከተል የራስ ሆነ የሌላ ሰው ነጻነት ሲሉ ለጋራ ጥቅም የቆሙ  መሆን ይኖርባቸዋል። (Dignitatis Humanae - ሰብዓዊ ክብር 2, 7)        

የኅብረተሰብ ዓለማዊ እና መንፈሳዊ ጥቅም ማሳደግ፣

ለማኅበራዊ ሕይወት መጎልበት አስተዋጽዖን ከሚያበርክቱት መሠረታዊ ነገሮች መካከል አንዱ በጋራ በምንኖርባት ምድራችን ላይ የሚገኝ የተፈጥሮ ሃብት ነው። ዕለታዊ ሕይወታችንን በጥሩ መንገድ መምራት የሚቻለው፣ ማኅበራዊ ብልጽግናን ማምጣት የሚቻለው በአካባቢያችን የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብታችንን ስንከባከብ እና ጥበቃ ስናደርግላቸው ነው። ቤተሰብ ለማኅበራዊ ሕይወት ማደግ የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ፣ ለተፈጥሮ የሚያደርገው እንክብካቤ እና ጥበቃ ከፍ ሊያደርግ ይገባል። የተፈጥሮ መመናመን በማሕበራዊ ሕይወት ላይ የሚያስከትለው አደጋ ቀላል የሚባል አይሆንም። የአየር ንብረት ለውጥ፣ የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር፣ የምድራች በረሃማነት እና ሌሎች በርካታ አደጋዎች ሊከሰቱ የሚችሉት ለአካባቢ ተገቢውን እንክብካቤን እና ጥበቃን ካለማድረጋችን ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተቀናጀ የተፈጥሮ እንክብካቤን በማስመልከት ባስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው “ስለ አካባቢ ስንናገር፣ በተፈጥሮ እና በማኅብረተሰብ መካከል ስላለው ግንኙነት ማለታችን ነው ብለው፣ ተፈጥሮን ከእኛ እንደተለየ ነገር ወይም በውስጡ የምንኖርበት ቦታ ብቻ አድርገን ማሰብ አንችልም” ብለዋል። “እኛ የተፈጥሮ አካል፣ በውስጡ ያለንና ያለማቋረጥ ከተፈጥሮ ጋር የምንገናኝ ነን። አንድ የተወሰነ አካባቢ በምን ምክንያት እንደ ተበከለ ለማወቅ፣ የኅብረተሰብን አሠራር፣ የኤኮኖሚውን፣ የሥነ ባሕሪውን እና እውነታን ማጥናት ይጠይቃል። ስለዚህ በተፈጥሮ ሥርዓቶችና በማኅበራዊ ስርዓቶች መካከል ያሉ መስተጋብሮችን ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ አጠቃላይ መፍትሄዎችን መሻት ያስፈልጋል” (ውዳሴ ላንተ ይሁን ምዕ. 4, 139)

አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን፤    

20 June 2020, 19:17