ፈልግ

ከወላጆች የሚደረግ የሕጻናት የትምህርት ዓመት ማገባደጃ ዝግጅት፤  ከወላጆች የሚደረግ የሕጻናት የትምህርት ዓመት ማገባደጃ ዝግጅት፤  

“ቤተሰባችን” - የቤተሰብ ተስፋ እና ተግዳሮት በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን። ክፍል 2

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ቤተሰብ ማለት ባል እና ሚስት እንዲሁም ልጆቻቸው እርስ በእርስ በሚጋሩት ፍቅራዊ ሕይወት የሚመሰረት ሕይወት ነው” በማለት ያስረዳሉ። (Familiaris Consortio“በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ” ቁ. 18) በእውነተኛ ፍቅር ላይ በመመስረት ሕይወትን የሚያገኝ ቤተሰብ በቀዳሚነት እምነት ተስፋን እና ፍቅርን በመመስከር፣ በጋራ ሕይወት ውስጥ ታማኝነትን በማሳየት እውነተኛ ሰብዓዊ አንድነት እንዲፈጠር ያደርጋል።   

በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ ቤተሰብ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን በጋራ ማቅረብ የሚቻልበት፣ ለማሕበራዊ እድገትም አስፈላጊውን የሰው ሃይል እና እውቀት ማቅረብ የሚችል ተቋም ነው። የቤተሰብ ሕይወት ቀስ በቀስ እያደገ የሚመጣ እና ከሌሎች ተመሳሳይ ሕይወት ካሏቸው ቤተሰባዊ ማኅበራት ጋር አንድ በመሆን ሰፊው የሆነው ኅብረተሰብ እንዲመሠረት ያግዛል። በዚህ ኅብረተሰብ ውስጥ በስነ ምግባር እና በዕውቀት የታነጸ፣ ከድህነት ሕይወት ተላቅቆ ራሱን መምራት የሚችል ቤተሰብ መኖር ለማኅበራዊ እድገት አስፈላጊ ነው። ይህም ቤተሰብ ለማሕበራዊ እድገት ሊያበረክት የሚችለውን እገዛ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው።  

ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ዓለማችን በከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባሕላዊ ለውጦች ላይ የሚገኝበት ዘመን ነው። ድህነት በተስፋፋበት፣ የማሕበራዊ ኑሮ አለመመጣጠን በሚታይበት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮች በተበራከቱበት፣ ከማሕበራዊ ሕይወት መገለል እየጨመረ በመጣበት ባሁኑ ጊዜ የቤተሰብ ሚና ምን መሆነ አለበት? የሚል ጥያቄ ይነሳል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በመበልጸግ ላይ ለሚገኝ ዓለማችን ቤተሰብ ሊያበረክት የሚችለው አስተዋጽዖ በቀጥታ በመሳተፍ ሳይሆን ለውጡ ትክክለኛ መንገድን የተከተል እንዲሆን ማድረግ ነው ብለው፣ ይህን እገዛ ማድረግ የሚችሉት በፍቅር እየኖሩ የፍቅር ስልጣኔን በማበረታታት ነው ብለዋል። (Catholicculture.org, 2020) 

በዚህ ሂደት የቤተሰብ ተግባር ማኅበረሰብን ፍቅር በማስተማር እንደሆነ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሕዝቦች መካከል በተግባር የሚገለጽ ፍቅር ለማኅበራዊ እድገት እና ብልጽግና የሚያበረክተው እገዛ ከፍተኛ መሆኑን በመልዕክታቸው ገልጸዋል። ትምህርት በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ እንደሚሰጠው ማወቅ የሚቻለው የትምህርት ዓላማ ከቤተሰብ ሕይወት ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ማወቅ ሲቻል ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የትምህርት ዋና ዓላማ የማኅበረሰብ አባል ሙሉ ስብዕና እንዲኖረው እና ሰው የመሆን ስጦታን እንዲረዳ ስለሚያደርግ ነው ብለዋል።

ትምህርት ሲባል በቀለም ትምህርት አማካይነት የተለያዩ ጽንሰ-ሐሳቦችን ለትውልድ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የማሕበረሰብ ክፍሎች ፣ ከወላጅ ቤተሰብ፣ ከትምህርት ቤት እንዲሁም ከባሕላዊ እና ሐይማኖታዊ ተቋማት ጋር በመተባበር መልካም የሆኑ እሴቶችን መካፈልን ይጠይቃል። (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 1783) ያስገነዝባል።

ራስን በፍቅር እና በመልካም ስነ ምግባር ማነጽ ለትክክለኛ እና እውነተኛ ብልጽግና መሠረት እንደሆነ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አስገንዝበዋል። መልካም የሆኑ እሴቶችን በማሳደግ እና በማስተማር ቤተሰብ የሚጫወተው ሚና ሰፊ ነው። በማሕበራዊ ተቋማት ውስጥም ዋና ተዋናይ በመሆን የሰው ሃይል እና እውቀት የሚገኝበት፣ መልካም የስነ ምግባር እሴቶች የሚቀሰምበት ተቋም ነው። የቤተሰብ ሕይወት በእውነተኛ ፍቅር ላይ በሚመሠረትበት ጊዜ ለጠቅላላ ማሕበራዊ ሕይወት የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ነው።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

13 June 2020, 18:40