ፈልግ

በደቡብ አፍሪቃ ሕጻናትን ከኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል ጥረት ሲደረግ፣ በደቡብ አፍሪቃ ሕጻናትን ከኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል ጥረት ሲደረግ፣ 

“ቤተሰባችን” ጊዜው የምሕረት፣ የርኅራሄ እና የተስፋ ነው!

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን እንደ ምን ሰንብታችኋል። ባለፈው ሳምንት ባቀረብነው የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሁላችን በስጋት ውስጥ ብንገኝም መልካም ጎኖች መኖራቸውን ተመልክተናል። የቤተሰብ መሰባሰብ፣ በሥራ ሆነ በሌሎች ምክንያቶች ተራርቀው የሚኖሩት የቤተሰብ አባላት ለመሰባሰብ እድል ማግኘታቸው አንዱ መልካም አጋጣሚ ነው። አንድ ላይ መሰባሰብ ብቻ ሳይሆን አንድ ላይ ለመጸለይ እና ለማስተንትን፣ ስለ ቤተሰብ ሕይወት ለማሰብ እና ለመመካከር ዕድል መገኘቱ ሌላው መልካም አጋጣሚ ነው ማለት እንችላለን። በዛሬው ሳምንታዊ የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት አሁን የምንገኝበትን የጽሞና ጊዜ ቤተሰብ እየተጠቀመ ይገኛል ከሚለው ጥያቄ በመነሳት አሁን ከምንገኝበት ጊዜ ጋር የሚሄዱ ሦስት ነገሮችን መመልከት እንወዳለን፤ አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ እንጋብዛችኋለን።

በምድራችን ላይ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወራት ተቆጥረዋል። ወረርሽኙን ከሌሎች ወረርሽኞች ልዩ የሚያደረገው ጊዜን የማይሰጥ በመሆኑ፣ በፍጥነት ሊዛመት በመቻሉ፣ መድሃኒት አለመገኘቱ እና ሌሎች ባህርያት ታክሎበት አደገኛነቱን የጎላ አድርጎታል። ያም ሆኖ ከሰው ወደ ሰው ሊተላልፍ የሚችልበትን መንገድ ቶሎ በማወቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንድናደርግ በጥናት የታገዙ ምክሮች ከጤና ባለሞያዎች በኩል ይደርሱናል። እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ የራሳችን እና የሌሎችን ሕይወት ከሞት አደጋ ማትረፍ የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው። የጤና ባለሞያዎችን፣ የመንግሥት እና የሐይማኖት አባቶች ምክር ችላ የምንል ከሆነ፣ መከራ ይምከረው ወደ ሚለው የአባቶቻችን አባባል እንሄዳለን። ከሁሉ አስቀድሞ መከራን ማስወገድ እየተቻለ ወደ መከራ ውስጥ መግባት ተገቢ አይሆንም። የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመከላከል እንዲረዱን ከተነገሩን ምክሮች መካከል አንዱ ቤት ውስጥ መሆን ነው። ይህም ያለ ተጨባጭ ምክንያት ከቤት በመውጣት በየመንገዱ እና በየሠፈሩ የሚደረጉ አላስፈላጊ ዝውውሮችን እንዲሁም ለማስወገድ እንጂ ለቤተሰብ ፍጆታ አስፈላጊ የሆኑ የዕለት ቀለብ እና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን ወደ ቤት ማምጣት የሚከለክል አይደለም።

ባሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የብዙ ስዎችን ሕይወት ማጥፋቱ፣ ብዙችንም ወደ ሞት አፋፍ ላይ ማድረሱ፣ ሌሎችን ደግሞ ከመቼ መቼ ይይዘኛል በሚል ስጋት ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ስቃይ እና ጭንቀት ከቅርብ ወራት የጀመረ እንጂ ዓለማችን ስቃይ እና ጭንቀት ውስጥ ከገባ ዘመናት ተቆጥረዋል። ዓለማችን የሚገኝበትን ስቃይ በማስታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት “ዓለማችን ሕመም ላይ መሆኗን ሳናውቅ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ፍጥነት ወደ ፊት ስንጓዝ ነበር። ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አስቀድሞ ሌላ ወረርሽኝ በመካከላችን ገብቶ ነበር ማለታቸው ይታወሳል። ዓለማችን የሚገኝበትን ሕመም “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው በስፋት ተናግረዋል። የሰው ልጅ ለተፈጥሮ ሊሰጥ የሚገባውን እንክብካቤ በማጓደሉ ምክንያት የሚከስት የአየር ንብረት ለውጥ፣ በምድራች በረሃማነት እየተስፋፋ መምጣት፣ የባሕር ላይ አውሎ ነፋስ፣ ከመጠን ያለፈ ዝናብ መዝነብ እና የምድራችን ከባቢ አየር ሙቀት መጨመር በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ አደጋን በማስከተል እያስጨነቀ ይገኛል። ድህነት፣ ረሃብ፣ ስደት፣ ጥላቻ፣ አመጽ፣ ጦርነት፣ ጭቆና፣ ብዝበዛ፣ ራስ ወዳድነት፣ ኢፍትሃዊነት፣ ልይነት፣ በደል ማድረስ፣ ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም፣ ሙስና እና ብልሹ አስተዳደር፣ እነዚህ እና እነዚህን ሌሎች እንዳይታይብን የምንደብቃቸው ክፉ ተግባሮቻችን በሕይወታችን ላይ ስቃይ እና መከራን አስከትሏል፣ በማስከትል ላይ ይገኛል። ማኅበረሰባችን በእነዚህ ያልተስተካከሉ አካሄዶች ምክንያት እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ሲደርስበት ኖሯል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያመጣው የጽሞና ጊዜ፣ በፍጥረታት እና በሰው ልጆች ላይ ባደረስንባቸው በደሎች እና ግፎች በፈጸምናቸው ስህተቶች ላይ በመጸጸት፣ ከፈጣሪ፣ ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር የምንታረቅበትን ምሕረት የምንለምንበት እና የምንጠይቅበት ጊዜ ነው። ስለዚህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው የጽሞና ጊዜ መፈጸም ያለብን የመጀመሪያው ተግባር በሠራናቸው ክፉ ተግባራት ተጸጽተን ምሕረትን መለመን ነው። 

የምንገኝባት የጋራ መኖሪያ ምድራችን አንዱ ወገን የሚኖርባት፣ ሌላው የሚገለልባት አይደለችም። ሁላችን በጋራ ሆነን በመረዳዳት እና በመዋደድ በሰላም በጤናና በደስታ እንድንኖርባት የተሰጠን ናት። መረዳዳት ሲባል ከሰዎች ጋር ብቻ የሚደረግ መረዳዳት ሳይሆን በምድሪቱ ላይ ከሚገኙ ሌሎች ፍጥረታት ጋር መደጋገፍን ይጠይቃል። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በደል የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች በድህነት ሕይወት እየተሰቃዩ የሚገኙ መሆኑን ርቀን ሳንሄድ በአቅራቢያችን ማየት እንችላለን። ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች፣ የአንድ ቤተሰብ ልጆች መሆናችንን ማወቅ ይኖርብናል። የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ስቃይ የሁላችን ስቃይ ነው። የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ደስታ እና ብልጽግና የሁላችን ደስታ እና ብልጽግና መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያመጣው የጽሞና ጊዜ የርህራሄ ጊዜ፣ የተራቡትን የምናበላበት፣ የተጠሙን የምናጠጣበት፣ የታረዙትን የምናለብስበት፣ የታመሙትን የምናክምበት፣ ያዘኑትን እና ተስፋ የቆረጡትን የምናጽናናበት ፣ መጠለያ አልባ ለሆኑት መጠለያን የምንሰራበት፣ ለተናቁት እና ለተገለሉት ሰብዓዊ ክብራቸውን መልሰን የምንሰጥበት፣ ለተጨነቁት ነጻነትን፣ ፍትህን ለተነፈጉት ፍትህን የምናመጣበት ጊዜ ነው። የተሻለች ዓለም መገንባት ከፈልግን እያንዳንዳችን የበኩላችንን መልካም ድርሻ ማበርከት ይኖርብናል። ይህን የማናደርግ ከሆነ የደረሰብን መከራ እና ስቃይ እንዲሁም ጭንቀት፣ በምድራችን ውስጥ የፍጥረታት ጩሄት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይሄዳል እንጂ አይቀንስም።

በዚህ የጽሞና ጊዜ የምናስበው ሌላው ስለ ተስፋ ነው። የደረሰብን መከራ ዘለዓለማዊ አይደለም። ሁሉም ነገር መጀመሪያ እና መጨረሻ አለው። ለዘለዓለም የሚኖር፣ በተስፋ ቃሉ የጸና፣ ሕይወትን የሚሰጥ፣ ከልጆቹ ጫንቃ ስቃያቸውን የሚያስወግድ፣ ይህን ለማድረግ ኃይል ያለው እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት አድማጮቻችን፣ አሁን በምንገኝበት የጽሞና ጊዜ ማሰብ ስላለብን ሦስት ነገሮች፣ ምሕረት፣ ርህራሄ እና ተስፋን በማስመልከት ያቀረብነውን በዚህ እንፈጽማለን፣ ሳምንት በሌላ ርዕሥ እስከምንገናኝ ሰላምን፣ ጤናን እና ፍቅርን የምመኝላችሁ የፕሮግራሙ አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን ነኝ።

ይህን ዝግጅት በድምጽ መከታተል ከፈለጉ “ተጫወት” ምልክትን ይጫኑ፣
02 May 2020, 20:28