ፈልግ

የእናቶች ቀን አከባበር፣ የእናቶች ቀን አከባበር፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እናቶችን በጸሎታቸው አስታወሱ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ግንቦት 2/2012 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የእናቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ባቀረቡት ጸሎት በመላው ዓለም የሚገኙ እናቶችን ምስጋና እና ፍቅር በተሞላ ልብ አስታውሰዋቸዋል። ቅዱስነታቸው በሞት የተለዩ እናቶችንም አስታውሰዋል። እናቶች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተጠቁትን ተቀብለው የሚያበረክቱት የማስታመም እና የመንከባከብ አገልግሎት ከፍተኛ መሆኑን፣ ወ/ሮ ኪያራ ጃካርዲ፣ በኮቪድ 19 ወቅት፣ አዲስ የቤተሰብ እና የአገልግሎት ዘርፍ ሙከራ ክፍል ተጠሪ ገልጸዋል።

የቫቲካን ዜና፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ሚያዝያ 9/2012 ዓ. ም. ነፍሰ ጡር ሴቶችን በማስታስወስ ጸሎት ማቅረባቸው ሲታወስ፣ የጸሎታቸው ዓላማም ለልጆቻቸው የወደ ፊት ሕይወት በማሰብ የተጨነቁ እናቶችን ለማጽናናት መሆኑ ታውቋል። የእናቶች በዓል በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች መከበር የተጀመረው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ከ1800 ዓ. ም. አጋማሽ በሰሜን አሜሪካ ሲሆን ለዚህም ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት ጁሊያ ዋርድ ዉ የተባሉ የሰላም ተሟጋች፣ የቤት እመቤት እና በሌሎች እናቶች ጥረት መሆኑ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር በ1914 ዓ. ም. በጊዜው የሰሜን አሜሪካ ፕሬዚደንት በነበሩ ዉድ ሮው ዊልሰን፣ ግንቦት ወር በገባ በሁለተኛው እሑድ ብሔራዊ የእናቶች ቀን እንዲሆን ብለው ማወጃቸው ይታወሳል።

በጣሊያን የእናቶች ቀን በይፋ መከበር የተጀመረው በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ሲሆን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር በታህሳስ ወር 1958 ዓ. ም. ሴናተር ራውል ዘካሪ በመንግሥት ምክር ቤት ለውይይት አቅርበው በግንቦት 8 እንዲከበር ቢወሰንም፣ ቀኑን እንደገና በማሻሻል ከ2000 ዓ. ም. ጀምሮ የግንቦት ወር በገባ በሁለተኛው እሑድ እናቶች ከልጆቻቸው ጋር አብረው እንዲያከብሩት መወሰኑ ይታወሳል። ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ በቤተሰብ ደረጃ ከፍተኛ ወጭ እና ዝግጅት ተደረጎ የሚከበር በዓል መሆኑን፣ “በሳክሮ ኩዎሬ” ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ፣ የማኅበረሰብ እና የባሕል ጥናት ተመራማሪ የሆኑት መምህርት ኪያራ ጃካርዲ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።

መምህርት ኪያራ እንደገልጹት፣ በእነዚህ ወራት ውስጥ፣ አዋቂ፣ ሕጻን፣ ወንድ፣ እና ሴት ሳይቀር ሁላችንም የተገነዘብነው ነገር ቢኖር፣ እናቶች ለኮሮና ቫይረስ ሕሙማን የሚያደርጉት እንክብካቤ፣ ሰብዓዊ ርህራሄ እና የማስታመም አገልግሎት ከፍተኛ መሆኑን ተመልክተናል ብለው፣ በዚህ አስጨናቂ ወቅት እናቶች በማበርከት ላይ የሚገኙት ሰብዓዊ አገልግሎት ከወረርሽኙ በኋላ ለሚኖረን ማኅበራዊ ኑሮ መልካም መልስ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጀመሪያ ወቅት ላይ የነበረውን ሁኔታ ያሳታወሱት መምህርት ኪያራ፣ በየመንደሩ የነበረው ጸጥታ አስደናጋጭ እንደነበር ገልጸው ፣ ሁለተኛ ዙር ደንብ ከታወጀበት ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ሰዎች በየአካባቢው ብቅ ማለት መጀመራቸውን ገልጸዋል። ከወረርሽኙ በፊት በነበረው ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የተሳሳተ አካሄድ እንደነበር መገንዘብ ችለናል ያሉት መምህርት ኪያራ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ችግር እናቶችም ሆኑ አባቶች እርስ በእርስ በመተጋገዝ፣ አንዱ የሌላውን የሥራ ድርሻ በመመልከት ልዩነትን ሳይፈጥሩ ለመላው ቤተሰብ ሕይወት ሲሉ ልጆችን በማስተማር፣ መንፈሳዊ ምክሮችን በመስጠት፣ ቀኑን በመተጋገዝ ማሳለፍ ይገባል ብለዋል። ችግር እና ጭንቀት በበዛበት ባሁኑ ወቅት እነዚህን መልካም የሆኑን ማኅበራዊ እሴቶችን መጋራት አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል።

እናቶች በቤት ውስጥ እና ከቤት ውጭ በሚኖራቸው የሥራ ውጥረት ምክንያት ጫና እንዳይበዛባቸው ፣ ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ፣ ትምህርት ቤቶች የማይከፈቱ ከሆነ እናቶች እቤት ሆነው ሕጻናትን ለመንከባከብ የሚገደዱ መሆኑን ያስታወቁት መምህርት ኪያራ፣ ይህም በእናቶች ላይ የሥራ ጫናን ሊፈጥር የሚችል መሆኑን አስረድተው፣ እናቶች በሚሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ሰብዓዊነትን በማሳየት በትክክል የሚያከናውኑ ከሆነ የእናትነትን ሃላፊነት መወጣት የሚችሉ መሆኑን ገልጸዋል። በማከልም የእናትነት ሚና ሰፊ እና የሌሎችንም ችግር መካፈልን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል። በፖለቲካው ዓለም እና በባሕል ዘርፍም ሴቶች የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ መቋረጥ እንደሌለበት አሳስበዋል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በቤተሰብ ውስጥ አዲስ የኑሮ ዘይቤን ለመለማመድ ችለናል ያሉት መምህርት ኪያራ፣ በዚህ መሠረት በቤተሰብ መካከል የሥራ ክፍፍል በማድረግ አባቶችም የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመጋራት በቤተሰብ መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲያድግ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። ምናልባትም በቀን ውስጥ በርካታ ሰዓትን ውጭ ማሳለፍ ጊዜን ማባከን ይሆናል ያሉት መምህርት ኪያራ፣ በተለያዩ ማሕበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ከቤት ሆኖ መልዕክቶችን በመለዋወጥ እና ስብሰባዎችን በማካሄድ የተለያዩ  ሥራዎችን መሥራት የሚቻል መሆኑን መምህርት ኪያራ አስረድተው ፣ በቤተሰብ መካከል የሥራ ድርሻን እንደገና በማጤን፣ የእናቶችን ሚና ከሌሎች የቤተሰብ አባላት ጋር አንድ በማድረግ፣ ልዩነትን ሳይፈጠሩ ሰብዓዊ አንድነትን ማሳደግ የሚቻል መሆኑን መምህርት ኪያራ አስረድተዋል።

ይህን ዜና በድምጽ ማድመጥ ከፈለጉ የተጫወት ምልክትን ይጫኑ፣
11 May 2020, 14:42