“ቤተሰባችን” የቤተሰብ ሕይወት በሁሉም ዘርፍ እንዲያድግ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።
ቤተሰብ፣ በሁለት ተቃራኒ ጾታዎች የጋብቻ ትስስር ወይም ስምምነት ተጀምሮ እያደገ የሚመጣ ማኅበራዊ ተቋም ነው። ለማኅበራዊ እድገትም አስፈላጊ የሰው ሃይል እና እውቀት የሚገኝበት ተቋም ነው። ቤተሰብ የሰው ኃይል እና ዕውቀት ማፍራት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ በመልካም ሥነ ምግባር የሚታነጽበት፣ ፍቅርን፣ ደስታን፣ ቸርነትን እና ርህራሄን የሚማሩበት የመጀመሪያ ትምህርት ቤትም ጭምር ነው። ቤተሰብ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መልካም ፈቃድ የሚጀምር እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያድግ፣ ተመሳሳይ የሕይወት መንገድ ካሏቸው ሌሎች የቤተሰብ ማሕበራት ጋር በመደመር፣ ሰፊው እና በቁጥር በርካታ የሆነው ሕብረተሰብ እንዲመሠረት ያደርጋል። “ቤተሰብ ይበልጥ ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው፣ ለባሕሪውም የሚስማማ በመሆኑ አስፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው። የበርካታ ቤተሰብ አንድነት፣ ሰዎች ከግለሰቦች አቅም በላይ የሆኑ ዓላማዎችን ከግብ ለማድረስ እና ተባብረው ለመሥራት ያላቸውን ዝንባሌ ያሳድጋል” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 1882)።
የቫቲካን ዜና፤
ከማኅበራዊ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ቤተሰብ፣ ሌሎች ማሕበራዊ ተቋማት እንዲመሠረቱ የበኩሉን አስተዋጽዖን በማበርከት ላይ ይገኛል። ማሕበራዊ ተቋማት የምንላቸውን የመንግሥት፣ የትምሕርት፣ የኤኮኖሚ እና የሐይማኖት ተቋማት ቀዳሚ ዓላማ ማሕበራዊ ሕይወት በእውቀት፣ በሃብት፣ በግብረገብ እና በኑሮ ደንቦች በመታገዝ፣ የሰዎች ሰላም፣ ፍቅር እና ብልጽግና እንዲረጋገጥ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖን ያበረክታሉ። ማሕበራዊ ተቋማትም ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲቆሙ ለማድረግ ከተፈለገ ከሁሉ በፊት ቤተሰብ በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። ቤተሰብ በጥበብ ፣ በገንዘብ አቅም፣ ፍቅርን ቀዳሚ ባደረገ ሥነ ምግባር እየተመራ ዘላቂነቱ የሚረጋገጥ ከሆነ ለማሕበራዊ እድገት እና ደህንነት መረጋገጥ የሚያበረክተው እገዛ ከፍተኛ ነው። የተደላደለ ማኅበራዊ እድገት ላይ የሚገኝ ቤተሰብ ከራሱ አልፎ በችግር ውስጥ የሚገኙትን የማሕበረሰብ ክፍሎች በመርዳት እና በማቋቋም ትልቅ እገዛን ማበርከት ይችላል።
የቤተሰብ ሕይወት በተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ሊጠቃ ወይም ሊደናቀፍ ይችላል። ድህነት፣ በሽታ፣ አመጽ፣ ጦርነት፣ የመብት ጥሰት፣ ጭቆና፣ ብዝበዛ፣ መገለል፣ የተፈጥሮ አደጋ እና ሌሎች ማኅበራዊ ችግሮች የቤተሰብን ሕይወት አደጋ ውስጥ ሊጥሉት ይችላል። በኅብረተስብ መካከል የሚገኙ ማኅበራዊ ተቋማት እና የግለሰቦች ኅብረት ያስፈለበት ዋናው ምክንያት ቤተሰብን የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ በመወጣት ወደ ተሻለ ሕይወት እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ነው። ቤተሰብ የኅብረተሰብን ሕይወት እና ደህንነት የመንከባከብ እና የማሳደግ ጠቀሜታው ከፍተኛ በመሆኑ ኅብረተሰብ ቤተሰብን የመደገፍ እና የማጠናከር ዓይነተኛ ሃላፊነት አለበት።
በዛሬው ዓለማችን ሰዎችን፣ በተለይም ድሃ ማኅበረሰብን የሚያጋጥም ደስታ፣ ተስፋ፣ ሐዘን ሆነ ስቃይ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ደስታ እና ተስፋ፣ ሐዘን እና ስቃይ በመሆኑ፣ በኢየሱስ ስም የተመሠረተው ይህ ማኅበር በመንፈስ ቅዱስ በመመራት ወደ እግዚአብሔር አብ ዘንድ በሚያደርገው ጉዞ ወቅት በችግር ውስጥ የሚገኙትን ለመርዳት የሚጋብዝ መልዕክት ተቀብለዋል። በመሆኑም መላው የክርስቲያን ማኅበረሰብ በችግር ውስጥ የሚገኙትን ከችግራቸው ለማውጣት፣ የአጋርነት ተልዕኮን በተግባር የመግለጽ ግዴታ ይሰማዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ (Gaudium et spes 1) ወይም ደስታ እና ተስፋ በሚለው ሐዋርዊ ቃለ ምዕዳን ቁ. 1
የቤተሰብ ሕይወት ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ የሚያግዙ የተለያዩ መንገዶች አሉ። ቤተሰብን በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት እና በመልካም ሃሳብ መደገፍ ይቻላል። የቤተሰብ አባላት ራሳቸውን በገንዘብ፣ በእውቀት እና በመልካም አስተሳሰብ ማዘጋጀት የሚችሉባቸው ጠንካራ ማኅበራዊ ተቋማት፣ በሚኖሩበት አካባቢ ሊኖሩ ይገባል። የቤተሰብ ተቋም፣ የትምህርት ተቋም፣ የሐይማት ተቋም እና የመዋዕለ ነዋይ ተቋም የእያንዳንዱን ሰው መልካም አኗኗር ለማረጋገጥ የተመሠረቱ ናቸው።
ቤተሰብ በፍቅር፣ በደስታ፣ በሰላም እና በቸርነት የተሞላ ሕይወት ለመኖር የተጠራ ቢሆንም ከተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ተለይቶ ሊኖር አይደለም። በአካባቢያችንም ያየን እንደ ሆነ በርካታ ቤተሰብ በሕመም፣ በረሃብ፣ በእርዛት፣ በአመጽ፣ በጥላቻ እና በስደት ችግር ውስጥ ይገኛል። የባለ ትዳሮች መለያየት ወይም የጋብቻ መፍረስ፣ ልጆች ያለ አሳዳጊ በየቦታው ተበታትነው ፣ አዛውንት ያለ ጧሪ እና ደጋፊ ብቻቸውን ቀርተው እናያለን። ቤተሰብን ሊደርስበት የሚችል የማሕበራዊ ችግሮች መነሻ እንደ አካባቢው ሊለያዩ ይችላል። ለምሳሌ በቤተሰብ ውስጥ ወጣቶች ላይ የሚንጸባረቁ የስነ ምግባር ቀውስ ስንመለከት ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተማር እና በመልካም ሥነ ምግባር የማነጽ፣ የመምከር፣ የመገሰጽ፣ በመልካም ሥነ ምግባር እንዲያድጉ የማገዝ ሃላፊነት አለባቸው። በቤተሰብ ውስጥ የልጆች መልካም አስተዳደግን በተመለከተ በእርግጥ የወላጅ ጥረት ብቻውን በቂ አይደለም። ትምህርት ቤቶች፣ የሐይማኖታዊ ተቋማት እና መላው ማሕበረሰብ ለወጣቶች መልካም አርዓያ በመሆን እውቀትን ከማስጨበጥ ባለፈ መልካም ስነ ምግባርን እና የባሕል እሴቶችን የማውረስ አደራ እና ሃላፊነት አለባቸው።
ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር መጋቢት 25/2019 ዓ. ም. በጣሊያን፣ ሎሬቶ ከተማ ወደ ሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተ መቅደስ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ ምዕመናን የቤተሰብን አስፈላጊነት ከልብ እንዲረዱ አሳስበው በማከልም እግዚአብሔር አብ ሰላም እና ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚገኝበት መልካም ዜና ወደ ዓለም እንዲመጣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መምረጡን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በመቀጠል፣ እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዝቅተኛ፣ ትሁት እና ደፋር፣ ድሃ እና ደግ የሆኑ፣ ለሕይወታቸው ሳይጨነቁ መልካም ዜናን ወደ ዓለም የሚያደርሱ ሰዎችን እግዚአብሔር በዘመናችንም እንደሚያዘጋጅ ገልጸዋል።
በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ በሚገኝ ዓለማችን ውስጥ በእውነተኛ ፍቅር ላይ በተመሠረተ ጋብቻ ሕይወት የሚገኙ ባል እና ሚስት፣ ወንጌልን ወደ ዓለም የማዳረስ እጅግ አስፈላጊ ተልዕኮ እንዳለባቸው አስረተው፣ በመሆኑም በእግዚአብሔር እቅድ የተመሰረተውን የቤተሰብ ሕይወት ታላቅነት በድጋሚ መረዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ቤተሰብ በማኅበረሰብ ሕይወት ውስጥ የሚያበረክቱት አገልግሎት መተኪያ የሌለው መሆኑንም አስረድተዋል።
የቤተሰብን ሕይወት ጠንካራ እና ዘላቂ ለማድረግ የወላጆች ጥረት ብቻውን በቂ አይደልም። ልጆች የእናት እና የአባት ውለታን ሳይዘነጉ ወላጆቻቸውን በገንዘብ፣ በጉልበት እና በዕውቀት እና በሃሳብ ድጋፋቸውን የመግለጽ ሞራላዊ ግዴታ አለባቸው። የሚበሉትን፣ የሚጠጡትን፣ የሚለብሱትን እና የሚኖሩበትን አጥተው የሚሰቃዩ ወላጆች ብዙ ናቸው። በበሽታ ወድቀው የአልጋ ቁራኛ የሆኑ እና አቅመ ደካማ የሆኑ ወላጆች ብዙ ናቸው። በችግር ውስጥ የሚገኙ ወላጆችን ለመርዳት ልጆች የተለያዩ አቅጣጫዎችን መመልከት ያስፈልጋል። የአንድ ቤተሰብ አባላት እርስ በእርስ ለመተጋገዝ ከፈለጉ ከሁሉ አስቀድሞ በመልካም ግንኙነት ውስጥ የሚገኙ ሊሆኑ ይገባል። በቤተሰብ መካከል መልካም ግንኙነት ካለ እርስ በእርስ በመተጋገዝ ችግሮችን በጋራ መወጣት ይቻላል።
በቤተስብ መካከል መልካም ግንኙነት ካለ ልጆች በራስ የመተማመን ስሜታቸው ከፍተኛ ከመሆኑ በላይ አእምሮአቸው መልካም አስተሳሰብ እንዲኖር ያደርጋል። ወላጆች በልጆቻቸው በኩል የሚነሱ የአመጋገብ፣ የዕረፍት እና የባሕርይ ለውጥ ችግሮችን ቶሎ ብለው ለማቃለል ዕድልን ያገኛሉ። በመልካም ግንኙነት ውስጥ የሚገኝ ቤተሰብ አባላት አንዱ ሌላውን በእርጋታ በማዳመጥ፣ የሃሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም በክብር ተቀብሎ ማስተናገድ ይችላል። በቤተሰብ መካከል መደማመጥ ሊኖር ይገባል ሲባል ወላጆች የልጆቻቸውን ሃሳብ፣ ስሜት እና ፍላጎት የማይጋሩ ከሆነ፣ ልጆችም የወላጆቻቸውን ሃሳብ፣ ምክር እና ፍላጎት የማይጋሩ ከሆነ፣ በመካከላቸው ያለው መተማመን እና ፍቅር ሊቀንስ ይችላል።
የቤተሰብ ሕይወት የሚገኝበትን ደረጃ በማጤን አስፈላጊውን እንክብካቤ የሚሰጡ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ተቋማት ቢኖሩም በቤተሰብ መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍቅርን እና ኅብረትን በማሳደግ፣ ሊያጋጥመው የሚችለውን አደጋ በጋራ በመቋቋም ዘላቂነት እንዲኖረው ለማድረግ ቀዳሚ ተዋናይ የሚሆኑት የቤተሰብ አባላት ናቸው። በመሆኑም እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሚችለውን ድጋፍ በማድረግ የቤተሰብን ሕይወት ወደ መልካም ደረጃ ማድረስ፣ ሰላምን፣ ኅብረትን እና መረዳዳትን በማሳደግ ሊደርስበት ከሚችለው ችግር መከላከል ያስፈልጋል።
አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን ነኝ።