በቻድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ረሃብን ለማስወገድ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
በአፍሪቃ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተጠቁ አገሮች መካከል ዝቅተኛ ቁጥር ባስመዘገበች ቻድ፣ ወረርሽኙ እንዳይዛመት በማለት መንግሥት ተቋማትን ለመዝጋት መወሰኑ ታውቋል። በአንዳንድ አገሮች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑ ሲነገር በአፍሪቃ አህጉር ግን ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል አንዳንድ ጥናቶች መጠቆማቸው ታውቋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ቁጥር ያጠቃቸው አፍሪቃ አገሮች ደቡብ አፍሪቃ፣ አልጀሪያ፣ ካሜሩን፣ ግብጽ፣ ጋና፣ አይቮሪ ኮስት፣ ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ እና ናይጀሪይ መሆናቸው ሲነገር ቻድን ጨምሮ በአነስተኛ ቁጥር የተጠቁ አገሮች መኖራቸው ታውቋል። ቻድ ዕድሜአቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በከፍተኛ ቁጥር የሚሞቱባት፣ በወሊድ ጊዜም በዓለም ከፍተኛ ቁጥር የእናቶች ሞት የተመዘገበባት አገር መሆኗ ታውቋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እስካሁን በቻድ ከሰባ በላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጠቂዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 33ቱ መሉ በሙሉ ከወረርሽኙ ያገገሙ እና አምስቱ መሞታቸው ታውቋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በምስራቅ ቻድ፣ ቤቢዴዪ ከተማ የሚገኝ ቅዱስ ዮሴፍ ሆስፒታል ዳይሬክተር የሆኑት ኮምቦናዊ፣ ሲስተር ኤልሳቤጥ ራኡል እንዳስታወቁት፣ እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ እስካሁን የበሽታው ምልክት ያልታየ መሆኑን አስረድተዋል። አካባቢው ቆላማ ከመሆኑ የተነሳ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያልታየ ቢሆንም ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ወረርሽኞች መኖራቸውን ሲስተር ኤልሳቤጥ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል።
የቻድ መንግሥት ከዓለም የጤና ድርጅት ባገኘው ድጋፍ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰዱን ያስታወቁት ሲስተር ኤልሳቤጥ ከእርምጃዎችም መካከል ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ማቆሙን ገልጸው ፣ በተለይም ከካሜሩን ጋር የሚያገናኘውን ድንበር እና የአውሮፕላን ጣቢያውን መዝጋቱን አስረድተዋል። እርሳቸው የሚመሩት የቅዱስ ዮሴፍ ሆስፒታል የጤና ባለሞያዎች፣ ሐኪሞች እና ረዳቶቻቸው ስለ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሰፋ ያለ ግንዛቤን ለሕሙማን እና ለዜጎች መስጠታቸውን ገልጸዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል የቻድ መንግሥት ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰዱን የገለጹት ሲስተር ኤልሳቤጥ፣ በአገሩ በቂ የሕክምና ቁሳ ቁስ በማይገኝበት ባሁኑ ወቅት፣ የወረርሽኙን መዛመት ለመቀንስ ሕዝቡ ማሕበራዊ ርቀትን እና ንጽሕናን በመጠበቅ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። የሕክምና መገልገያ መሣሪያ ዕጥረት መኖሩን ያስረዱት ሲስተር ኤልሳቤጥ፣ ከውጭ የሚገኙትን መሳሪያዎችን በፍጥነት ወደ አገር ለማስገባት እንቅፋት ያጋጠማቸው መሆኑን አስረድተዋል። ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጨማሪ አገሪቱ በምግብ እጥረት የምትሰቃይ መሆኗን የገለጹት ሲስተር ኤልሳቤጥ፣ አርሶ አደሩ ምርት እንዳያስገባ፣ ከቤቱ እንዳይወጣ የሚል የመንግሥት ትዕዛዝ ችግር የፈጠረባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።