ፈልግ

በጣሊያን ቤርጋሞ ከተማ የጸሎተ-ፍትሐት ሥነ ሥርዓት ጥቂት የቤተስብ አባላት በተገኙበት ሲፈጸም፣ በጣሊያን ቤርጋሞ ከተማ የጸሎተ-ፍትሐት ሥነ ሥርዓት ጥቂት የቤተስብ አባላት በተገኙበት ሲፈጸም፣ 

“ቤተሰባችን” የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በጣሊያን፣ ክፍል 2

ክቡራት እና ክቡራን የ “ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን እንደ ምን ሰንብታችኋል። በዛሬው ሳምንታዊ የ “ቤተሰባችን” ዝግጅት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በጣሊያን የሚል ርዕስ ክፍል ሁለት እናስነብባችኋለን።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን።   

ከጥቂት ወራት ጀምሮ ዓለምን እጅግ እያስጨነቀ የሚገኝ ጉዳይ ምንድነው ተብሎ ቢጠየቅ ቀዳሚ መልስ “የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ነው” የሚል እንደሚሆን አያጠራጥርም። በማኅበራዊ መገናኛዎች በኩል ስለ ኮሮና ቫይረስ ብዙ ከመወራቱ በላይ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ፍጥነት ዓለምን እያዳረሰ መምጣቱ የወረርሽኙን አደገኛነት እጅግ አጉልቶታል። ወረርሽኙ ዓለምን ማዳረስ ብቻ ስይሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሰው ልጅ ሕይወት በአጭር ጊዜ ውስጥ መቅጠፉ የበሽታውን አሳሳቢነት ከፍ አድርጎታል።

ዓለምን እያስጨነቃት የሚገኝ የኮሮና ቫይረስ ብቻ አይደለም። በጋራ የምንኖርባት ዓለማችን የተጨነቀችባቸው ጉዳዮች በርካቶች ናቸው። እንደ ኮሮና ቫይረስ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ዓለምን በማዳረስ የብዙዎችን ሕይወት ለሞት አያጋልጡ እንጂ በየጊዜው የሰውን ሕይወት ለሞት የሚዳርጉ እንደ ኮሌራ፣ ማጅራት ገትር፣ ኢቦላ እና “ኤች አይ ቪ ኤድስ” ቀንደኛ ከሚባሉ ተላላፊ በሽታዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።  

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሰሜናዊ ጣሊያን ግዛቶች እንዴት ሊስፋፋ ቻለ? ይህን ያህል በርካታ የሰው ሕይወት እንዴት ለሞት ተዳረገ የሚሉት እና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተዋል። ነገሩ እንዲህ ነው፥ በጥር ወር መጀመሪያ ላይ በሰሜን ጣሊያን ክፍለተ ሀገራት የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በአስቸኳይ እንዲዘጉ በማለት ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአቶ ጁሴፐ ኮንተ ሃሳብ ቀርቦላችው ነበር። ምክንያቱም በሰሜን ጣሊያን ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ፋብሪካዎች ተቀጥረው የሚሰሩ ቻይናዊያን ቤተሰብ ልጆች የብርሃነ ልደቱን እና የአውሮፓዊያኑ አዲስ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ ከታኅሳስ ወር አጋማሽ እስከ ጥር ወር መጀመሪያ ድረስ ወደ ቻይና የተለያዩ ክፍላተ ሀገራት ሄደው ነበር። እነዚህ ተማሪዎች ከእረፍት ተመልሰው ወደ ትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ተነጥለው እንዲቆዩ የሚል ሃሳብ ቀርቦ ነበር።       

ይሁንና የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትት አቶ ጁሰፔ ኮንተ ጉዳዩን የክልሎቹ የጤና እና ትምህርት ቢሮዎች ተመልክተው ውሳኔን እንዲሰጡ የሚል ትዕዛዝ ቢያስተላልፉም ከክልሎቹ የትምህርት እና የጤና ቢሮዎች የተወሰደ ምንም ዓይነት ውሳኔ አለመኖሩ ይነገራል። በእነዚህ ጊዜያት መካከል የቫይረሱ ወረርሽኝ በስፋት የሚስፋፋበትን ዕድል አግኝቶ ለዚህ አሰቃቂ አደጋ ዳርጓቸዋል የሚል ግምት በስፋት አለ። ወረርሽኙ ገና ሳይዛመት ለማስቆም የነበረው ዕድል ተግባራዊ ሳይሆን ቢቀርም ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በማለት አንዳንድ ጠቃሚ እርምጃዎችን መንግሥት መውሰድ መጀመሩ ይታወሳል። ከእነዚህ ፈጣን እርምጃዎች መካከል ጥቂቶቹ፥ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እና የግል ድርጅቶችን መዝጋት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የስፖርት ማዕከላት፣ የአምልኮ ሥፍራዎች፣ ባጠቃላይ ሰው በብዛት የሚገኙባቸው ቦታዎች እንዲዘጉ ማድረግ፣ ቤተሰብ ጊዜያቸውን በቤት ውስጥ እንዲሳልፉ ማድረግ።

ጥር 12 ቀን 2012 ዓ. ም. የቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ መንግሥት ከፍተኛ ልዑካን የጣሊያን መንግሥት ባዘጋጀው የባሕል እና ቱሪዝም በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ጣሊያን መጥተው ነበር። የቻይና ባለ ስልጣናት በወቅቱ ለጣሊያን አቻዎቻቸው በሰጡት ከባድ ማስጠንቀቂያ፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ከሕዝብ ጆሮ ደብቆ ማቆየት ከፍተኛ ነውር እንደሆነ ተናግረው ነበር። በዚህ ማስጠንቀቂያ ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ የወደቁት የጣሊያን መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ምን ማድረግ ይኖርብናል በማለት ራሳቸውን መጠየቅ ጀመሩ። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወ/ሮ ሳንድራ ዛምፓ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ሙሉ በሙሉ መዘጋት አለባቸው በማለት የግል አስተያየታቸውን ሰነዘሩ። የማምረቻ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችንም መንግሥታዊ እና የግል ድርጅቶችን መዝጋት የአገሪቱን ኤኮኖሚ ወደ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንደሚያስገባ፣ ዜጎችንም ለረሃብ የሚያጋልጥ መሆኑን ቢገልጹም የኮሮና ቫይረስ ከሚያስከትለው ጉዳት ጋር ሲያመዛዝኑት ምንም እንዳልሆነ ተገነዘቡ። 

የጣሊያን መንግሥት የኮሮና ቫይረስ በቻይና ውስጥ እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ የሕይወት መጥፋት በቁም ነገር አልተመለከተውም ነበር። ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ደግሞ ቫይረሱ በጣሊያን ውስጥ እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ የሕይወት መጥፋት እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ ከግምት ውስጥ አላስገባውም ነበር። የጣሊያን ሪፓብሊክ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ጁሰፔ ኮንተ የወረርሽኙን አስከፊነት በማጉላት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አገራቸውን ከባድ ማኅበራዊ ቀውስ ሲያጋጥማት ይህ የመጀመሪያ ነው ብለዋል። ይህን ካሉ በኋላ መንግሥታቸው የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ለዜጎቻቸው አሳውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥር 21/2012 ዓ. ም. በወሰዱት እርምጃ ከቻይና ወደ ጣሊያን የሚደረጉ የአውሮፕላን በረራዎች እንዲቆሙ አድርገዋል።

በሰሜን ጣሊያን ለኮሮና ቫይረስ መዛመት ዋና ምክንያት ሆኗል የተባለው የ38 ዓመት ዕድሜ ጎልማሳ ትክክለኛ ሕመሙ እስኪታወቅ ድረስ ሆስፒታል ገብቶ በተለያዩ ሐኪሞች የህክምና ዕርዳታ ሲደረግለት መቆየቱ ይነገራል። ህመሙ ታውቆ በእርግጥም የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መሆኑ እስከታወቀበት ጊዜ ድረስ ከብዙ ጓደኞቹ እና ከሌሎች ሰዎች ጋርም ለሥራ ጉዳይ ሲገናኝ መቆየቱ ተነግሯል። በእነዚያ ቀናት ውስጥ ብቻ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ ስለ መያዛቸው ምንም ዓይነት ማረጋገጫ አያስፈልግም። ቫይረሱ ለዓለማችን እንግዳ በመሆኑ የተነሳ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ህመማቸውን በማቅለል ብዙዎችን ሊበክሉ ችለዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በጣሊያን ውስጥ እንዴት ሊስፋፋ ቻለ? ለሚለው ጥያቄ ይህን ያህል መረጃ ከተገኘ ከዚህ መረጃ መማር የምንችለው ጠቃሚ ምክር ደረቅ ሳል፣ ትኩሳት ወይም ማስነጠስ ሲጀምር የተለመደ ነው ወይም ይተዋል በማለት ሳንዘናጋ አካባቢያችን ወደ ሚገኘው ጤና ጣቢያ በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራ ማድረግ ይኖርብናል። ከዚህም በተጨማሪ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል የሚሰጡ ምክሮችን ሳያቋርጡ ተግባራዊ ማድረግ ራስን ሆነ ሌላውን ከቫይረሱ ጥቃት ከመከላከል በላይ ወረርሽኙ በአጭሩ እንዲቋረጥ ያደርጋል።

04 April 2020, 21:23