ፈልግ

ቤተሰብ ተሰባስበው፣ ቤተሰብ ተሰባስበው፣ 

“ቤተሰባችን” የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አዎንታዊ ገጽታው ምንድነው?

ክቡራት እና ክቡራን የ “ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን እንደ ምን ሰንብታችኋል። በዛሬው ሳምንታዊ የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ተለያዩ አገሮች በመሰራጨት ላይ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ያስከተላቸውን አንዳንድ አዳዲስ አዎንታዊ ክስተቶችን ለመመልከት እንሞክራለን።

የጽሑፉ አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን።

ከጥቂት ወራት ወዲህ ኮሮና ቫይረስ የተባለው ወረርሽኝ በዓለማችን ውስጥ ቀዳሚ መነጋገሪያ ርዕሥ ሆኗል። በየአገራቱ የሚገኙ ብዙሃን መገናኛዎች ሰፋ ያለ ጊዜን በመስጠት ዜጎች ከወረርሽኙ ራሳቸውን መከላከል እንዲችሉ ለማድረግ ጠቃሚ ምክሮችን በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ። ከማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ ከጤና ባለሞያዎች የተቀበሏቸውን ጠቃሚ ምክሮች ለቤተሰቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው እና ለጎረቤቶቻቸው በማካፈል ላይ ይገኛሉ። ዓላማውም ከማኅበራዊ ሚዲያዎች እና ከጤና ባለሞያዎች የሚነገሩንን የወረርሽኙ መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የራሳቸውን እና የሌሎችን ሕይወት ከሞት ማትረፍ ነው።

ባሁኑ ጊዜ ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኝ የኮሮና ቫይረስ ብቻ አይደለም። ከሰው ልጅ ባሕል እና እምነት መዳከም ካስከተላቸው ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውሶች በተጨማሪ የተፈጥሮ መዛብት በማስከተልልይ ያለው አደጋ እና ጥፋት የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን እና በውስጧ የሚኖሩ ፍጥረታት በሙሉ እያስጨነቀ ይገኛል። የኮሮና ቫይረስን ያህል በጥቂት ቀናት ውስጥ ብዙ የሰው ሕይወት ለሞት አደጋ አላጋልጡም እንጂ በየጊዜው የሞት አደጋን የደቀኑ እንደ ኮሌራ፣ ማጅራት ገትር፣ ኢቦላ እና “ኤች አይ ቪ ኤድስ” ቀንደኛ ከሚባሉ ተላላፊ በሽታዎች መካከል ጥዊቶቹ ናቸው።

የዚህ ጽሕፍ ዓለማ ስለ ተለያዩ የበሽታ ዓይነቶች እና የሚያስከትሉትን ጉዳቶች ለመዘረዘር ሳይሆን የወቅቱ አስጨናቂ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያመጣቸውን አንዳንድ አዳዲስ ክስተቶችን በጥቂቱ ለማስታወስ ነው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችሶኮስ ሰኞ መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ. ም. ዕለት በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት ስብከተ ወንጌል በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ብንገኝም መልካም ጎኑን መመልከቱ ጥሩ ነው ማለታቸው ይታወሳል። በመሆኑም ወረርሽኙ በቤታችን፣ በአካባቢያችን፣ በማሕበረሰባችን እና በዓለማችን ያስከተላቸውን አንዳንድ አዎንታዊ ገጽታዎችን መመልከቱ መልካም ይሆናል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ ሲባል የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል። የመንግሥት ሆነ የግል መሥሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የስፖርት ማዕከላት፣ የአምልኮ ሥፍራዎች እና ሰዎች በብዛት የሚገኙባቸው ቦታዎች ላልተወሰነ ጊዜ አገልግሎትን እንዲያቋርጡ ተደርገዋል። ከዚህ በፊት ከወላጆቻቸው፣ ከወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ጋር አብረው ለመዋል ዕድል ሳያገኙ የቆዩ በርካታ የቤተሰብ አባላት አብረው በመሆን ጥሩ ቤተሰባዊ አንድነትን ፈጥረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ የተለዩትን ጓደኛን፣ ዘመድን እና ጎረቤትን ከቤታቸው ሆነው በስልክ ጥሪ እና በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል ሊገናኙ ችለዋል። በለይቶ ማቆያ ማዕከላት የሚገኙ ሰዎች እንዲያርፉ በተደረጉበት ሥፍራ ሆነው ዛሬ ከመቼም ጊዜ በበለጠ ከወላጆቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው እና ከሚያቋቸው ሰዎች የስልክ ጥሪዎችን በመቀበል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።  ይህ አጋጣሚ የሰዎችን ማኅበራዊ ግንኙነት በማሳደግ በመካከላቸው ያለውን ቤተሰባዊ አንድነት፣ የእርስ በእርስ መተሳሰብ እና መረዳዳት ሊያሳድግ እና ሊያበረታታ መቻሉ ታውቋል።  

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ተለዩ የዓለማችን ክፍል በዛመት ከጀመረ ወዲህ በርካታ አገሮች ፋብሪካዎቻቸውን እና ግዙፍ የማምረቻ ተቋሞቻቸውን ዘግተዋል። ዓለም አቀፍ ይውመጓጓዣ መንገዶችን፣ የአውሮፕላን በረራዎችን እና የመርከብ ጉዞዎችን ማገዳቸው ይታወሳል። በዚህ የተነሳ የአየር እና የውሃ ብክለቶች በእጅጉ መቀነሳቸው ተስተውሏል። የሰውን ልጅ ጨምሮ አዕዋፍ እና አስርዕት ከቀድሞ የተሻለ ጤናማ የሆነ ንጹሕ አየር በመተንፈስ ላይ እንገኛለን። “ስካይ” የተባለ ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ በሕዝባዊት ሪፓብሊክ ቻይና ውስጥ በአየር ብክለት ምክንያት እስከ መቶ ሺህ የሚጠጋ የሰው ሕይወት በጨቅላ ዕድሜ ክልል የሚሞት መሆኑን ገልጾ ቻይና ለኤኮኖሚ ዕድገት የምታደርገውን ሩጫ በመጠኑ እንኳ ብትቀንስ ኖሮ የሟች ሰው ቁጥር በእጅጉ የሚቀንስ መሆኑን አስታውቋል። በኦስሎ የሚገኝ የአየር ለውጥ ጥናት ማዕከልም በበኩሉ “የቅሪተ አካል ነዳጅ ጥቅምን መቀነስ ቢቻል ኖሮ የአየር ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል እና ውጤቱንም በዓለም ዙሪያ በግልጽ መመልከት ይቻል ነበር” ብሏል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለቤተሰብ አንድነት ብቻ ሳይሆን ከቤተሰብ ውጭ ተራርቀው የሚገኙትን የአንድ አገር ሕዝቦችን እያቀራረበ ይገኛል። በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው ተሰድደው ባዕድ አገር የሚኖሩ ዜጎች ሕዝባቸውን ከዚህ ወረርሽኝ ለማትረፍ የሚችሉትን የገንዘብ፣ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ፣ የጉልበት እና የእውቀት እርዳታን ሰብስበው መላካቸው አለኝታነትን፣ በአንድነት የመቆም አስፈላጊነን ከምን ጊዜብ በበለጠ እንዲረዱት አድርጓቸዋል።  

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሕይወት ላይ እያስከተለ ያውን አደጋ ብቻ ተመልክቶ በፍርሃት እና በጭንቀት መኖር ሳይሆን በዓለማችን ሕዝቦች መካከል ያስከተለውን አንድነት እና መረዳዳት ማስታወሱ ተቋርጦ የቆየውን ሰብዓዊ አንድነት መልሶ ለመገንባት መንገድ ከፍቷል። ወረርሽኙ በባሕሪው የአገራትን፣ የመንግሥታትን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን እና የግለሰቦችን ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ እና ያለዚህ መተባበር በሽታውንም መቆጣጠር የማይቻል መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል።

ክቡራት እና ክቡራን የ “ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን በዛሬው የ “ቤተሰባችን” ዝግጅት የርኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተላቸውን አንዳንድ አዎንታዊ ገጽታዎችን ለማጋራት ሞክረናል። ከእነዚህ እላይ ከተጠቀሱት አዎንታዊ የሆኑ ማኅበራዊ ገጽታዎች በተጨማሪ በየቤታችን፣ በየአካባቢያችን የሚታዩ የመልካም ስነ ምግባር መገለጫ የሆኑ እሴቶችን በማስተዋል ተግባራዊ ልናደርግ ይገባል እያልን የዛሬውን ጽሑፍ በዚህ እናጠቃልላለን። በሚቀጥለው ሳምንት እስከምንገናኝ በምንኖርበት አካባቢ እግዚአብሔር ምሕረቱን፣ ሰላሙን እና ፍቅሩን ይስጠን።

11 April 2020, 18:02