ፈልግ

“ቤተሰባችን” “ቤተሰባችን”  

“ቤተሰብን መታደግ ያስፈልጋል”

ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎቻችን በዚህ ሳምንታዊ ዝግጅት አማካይነት በቤተሰብ ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ ይጠቅማሉ ብለን ያሰብንውን አስተምህሮችን፣ ምክሮችን እና አስተያየቶችን ስናቀርብ ቆይተናል። ዛሬ በቀረበው ጽሑፋችን የቤተሰብን ሕይወት መታደግ በሚል ርዕሥ አጭር የሚከተለውን ጽሑፍ አቅርበንላችኋል፥

የቤተሰብ ሕይወት በማኅበራዊ ጥናት ውስጥ ከፍተኛ ትኩረትን ያገኘ የኑሮ ዘርፍ ነው። ለቤተሰብ የሚሰጡ ትርጉሞች ጥቂት አይደሉም። ማሕበራዊ አደረጃጀቱን፣ ባሕላዊ እና ኤኮኖሚያዊ እድገቱን በማገናዘብ ለቤተሰብ የሚሰጡ ትርጉሞች ብዙ ቢሆንም መሠረታዊ ትርጉሙ ተመሳሳይ ነው። በእውነተኛ ፍቅር ላይ ተመስርቶ ዘላቂነቱን ያረጋገጠ ቤተሰብ ለኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖን ያበረክታል።

ቤተሰብ ከራሱ አልፎ በሌሎች ማሕበራዊ ተቋማት ውስጥ ዋና ተዋናይ በመሆን የሰው ሃይል እና እውቀት የሚገኝበት፣ መልካም የስነ ምግባር እሴቶች የሚቀሰምበት ፣ የደስታ እና የነጻነት ሕይወት የሚጀመርበት ተቋም ነው። የቤተሰብ ሕይወት በእውነተኛ ፍቅር ላይ በሚመሠረትበት ጊዜ ለጠቅላላ ማሕበራዊ ሕይወት የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ነው። ከሁሉም በላይ ልጆች እውነተኛ ፍቅርን የሚማሩበት፣ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶችን የሚቀስሙበት ቀዳሚ ትምህርት ቤት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ቤተሰብ መንፈሳዊ እና ማሕበራዊ እሴቶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት።

ቤተሰብ በተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች፣ ከእነዚህም መካከል የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች፣ ማሕበራዊ ልዩነቶች እና ኢፍትሃዊ የተፈጥሮ ሃብት ክፍፍል ሲያጋጥመው ዘላቂነቱ ላይ እክል ሊደርስበት ይችላል። ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚከሰቱ ልዩ ልዩ ማሕበራዊ ችግሮች ምክንያት የቤተሰብ ሕይወት ፈተናዎች ቢገጥሙትም ዘላቂ እንዲሆን የሚያደርጉ ቋሚ የተፈጥሮ ሕጎች አሉት። ከህጎቹ መካከል አንዱ “ቤተሰብን በእውነተኛ ፍቅር ላይ መመስረት ያስፈልጋል” የሚል ነው።

በማሕበረሰብ መካከል ያለውን ማሕበራዊ ግንኙነት በተመለከተ የቤተሰብ አባላት እና እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል አንዱ ለሌላው በሚሰጠው አክብሮት ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የጋብቻ ሕይወት መሥራች የሆነውን እግዚአብሔር እንድንወድ፣ ባልንጀሮቻችንን እንደ ራሳችን አድርገን እንድንወድ፣ የፍቅር ሕይወትን የሚያስተምሩ ወላጆቻችንን እንድንወድ፣ ሕዝባዊ አደራ ለተጣለባቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት እንድንታዘዝ እና እንድናከብራቸው፣ ተማሪዎች መምህራኖቻቸውን፣ ሠራተኞች አሰሪዎቻቸውን ማክበር እንደሚገባቸው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ በቁጥር 2199 ላይ ያሳስባል። በማከልም እያንዳንዱን ቤተሰብ የማሕበረሰብ አካል እንደመሆኑ መጠን ልጆች፣ ወላጆች፣ ዜጎች እና የመንግሥት ባለስልጣናት ለአገራቸው ማበርከት ያለባቸው ተግባር ምን መምሰል እንዳለበት፣ እንዴት መከናወን እንዳለበት አቅጣጫን በማስቀመጥ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራራቀ ለሚገኝ ማኅበረሰብ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማቅረብ ላይ ይገኛል።       

የቤተሰብን ፖለቲካዊ ፣ ማሕበራዊ ፣ መንፈሳዊ እና ባህላዊ ሕይወትን ያላገናዘቡ ሕጎች እና ደንቦች መጽደቃቸው ለቤተሰብ ሕይወት እንቅፋት ሲፈጥሩ ይታያል። ለበርካታ ዘመናት የጋብቻ ሕይወት መልካም ውጤት እንዲያመጣ የበኩሉን አስተዋጽዖን ሲያበረክት የቆየው የተፈጥሮ ሕግ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሲሸረሸር እና ማሕበራዊ ሕይወትን አደጋ ላይ ሲጥል ይታያል።   ቤተሰብ የሚተዳደርበት የጋብቻ ሕግ በአዲስ የእግዚአብሔርን እቅድ የማይከተል፣ ሕጉንም በሚያፈርስበት ጊዜ የሚያስከትለውን አደጋ መገመት ይቻላል። በአዲስ መልክ የሚረቀቁ ኢፍትሐዊ የሆኑ ሕጎች እና ደንቦች ጋብቻን የሚጻረሩ ሆነው ሲገኙ ማሕበረሰቡ በእነዚህ ሕጎች ላይ ቅሬታን በመግለጽ ያለመቀበል መብቱ የተጠበቀ መሆን አለበት። በዛሬው ዓለማችን ባለ ትዳሮች በፖለቲካዊ እና በማሕበራዊ ሕይወት በመሳተፍ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽዖ ለማበርከት  ከተፈለጉ የጋብቻን ሕይወት በማስመልከት ከቤተክርስቲያን በኩል የሚቀርቡ መንፈሳዊ አስተምህሮን በሚገባ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ለማሕበረሰብ ጥቅም እና አገልግሎት የቆሙ ትዕዛዛትን እና ሕጎችን ማክበር እና ማስከበር ክርስቲያናዊ ጥሪ እና ግዴታ መሆኑ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ በቁ. 2199 ላይ ያስገነዝባል። 

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ጽሑፍ አንባቢዎቻችን፣ “የቤተሰብን ሕይወት መታደግ” በሚል ርዕሥ የቀረበው አጭር ጽሑፍ በዚህ ተፈጸመ። በሚቀጥለው ሳምንት በሌላ ርዕሥ እስከምንገናኝ ሰላምን፣ ፍቅርን እና ጤናን የምመኝላችሁ፣ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን ነኝ።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
14 March 2020, 18:18