ፈልግ

“ቤተሰባችን” “ቤተሰባችን” 

የቤተሰብ አብሮነት መተሳሰብን እንጂ ጭንቀት መፍጠር የለበትም።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ከቻይና ውሃን ከተማ ተነስቶ ወደ ዓለም ዳርቻ በመሰራጨት ላይ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ የዓለም ሕዝብን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መጣሉ ይታወቃል። በሽታው ወደተለያዩ አገሮች መሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየቀኑ በርካታ ሰዎችን ለሞት እየዳረገ መሆኑን የተለያዩ አገራት መንግሥታት ይፋ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ አገራት የወረርሽኙን አደገኛነት ለሕዝቦቻቸው ከማሳወቅ በተጨማሪ ሕዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እና በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ላይ ይገኛል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዕለት ቀለብ የሚሸመትባቸው እና ሕዝባዊ አገልግሎቶችን ከሚሰጡ ማዕከላት በስተቀር የመንግሥት እና የግል መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ የትምህርት ተቋማት፣ የስፖርት ማዕከላት፣ የአምልኮ ሥፍራዎች፣ ሬስቶራንቶች እና ሰው በብዛት የሚገኙባቸው ቦታዎች በሙሉ እንዲዘጉ ትዕዛዝ የሚያስተላልፉ አገሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደግ ላይ ይገኛል። በርካታ የአውሮፓ አገሮችም ዜጎቻቸው በሚኖሩበት አካባቢ ያለ በቂ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡ በማድረግ፣ የወጡ ካሉም ከበድ ያለ የገንዘብ ቅጣት የሚጣል መሆኑን አስጠንቅቀዋል።  የግድ መውጣት ካለባቸውም በፖሊስ የተዘጋጀ ቅጽ በመቀበል ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወሩበትን ምክንያት በግልጽ ማሳወቅ እና ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። የበሽታውን መዛመት ለማስቀረት ተብሎ በየአገራቱ በሚገኙ የጤና ተቋማት በኩል የግል ንጽሕና አጠባበቅ ጨምሮ ሌሎች በርካታ ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ በማለት የተለያዩ ጥንቃቄዎች እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።

ለሕዝብ ደህንነት ሲባል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች ሲዘጉ፣ የትምህርት ተቋማትም የማስተማር አገልግሎታቸውን ላልተወሰነ ጊዜ ሲያቋርጡ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ጠዋት ወጥተው ማታ ወደ ቤት ይመለሱ የነበሩ የቤተሰብ አባላት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ወደ ቤት እንዲመለሱ እና ጊዜያቸውን ከተቀሩት የቤተሰብ አባላት ጋር እንዲያሳልፉ ይገደዳሉ ማለት ነው። ኮሮና ቫይረስ በፍጥነት በመዛመት በርካታ ሰዎችን ለሞት መዳረጉ ሄዶ ሄዶ በማሕበራዊ ሕይወት እና በኤኮኖሚ ላይ የሚያስከተለው ቀውስ ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። የበሽታውን አስክፊ ገጽታ ብቻ የምንመለከት ከሆነ የሚያጽናን እና ተስፋን የሚሰጥ ነገር ከማግኘት ይልቅ ራሳችንን ለበለጠ ፍርሃት እና ጭንቀት እንጋብዛለን። ከዚህ አስጨናቂ ክስተት ምን በጎ ነገር ሊገኝ ይችላል ብሎ ግራ እና ቀኝ መመልከቱ ሊጠቅም ይችላል የሚል ሃሳብ አለኝ።

የአንድ ቤተሰብ ኣባላት ከዚህ በፊት ከሚያደርጉት በተለየ መልኩ በሽታው ባስከተለው ስጋት ምክንያ ረዘም ያለ ጊዜን አብረው በሚያሳልፉበት ጊዜ በመካከላቸው ምን ሊያድግ ይችላል የሚለውን በጥልቀት መመልከት መልካም ይሆናል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችሶኮስ ሰኞ መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ. ም. ባቀረቡት ስብከተ ወንጌል በኮሮና ቫይረስ መዛመት ምክንያት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ብንገኝም መልካም ጎኑን መመልከት ያስፈልጋል ብለው ቤተሰብ አንድ ላይ የመሆን አጋጣሚን በሚያገኙበት ጊዜ በመካከላቸው ያለውን ቤተሰባዊ ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መረዳዳት እና ትውውቅ በማሳደግ የቤተሰብ ሕይወት ትርጉምን ይበልጥ እንዲያውቁ ያግዛል ብለዋል። በመሆኑም ይህ መልካም አጋጣሚ በከንቱ ማለፍ የለበትም ብለው፣ ቤተሰብ እርስ በእርስ ፍቅርን፣ ርህራሄን እና መተሳሰብን የሚገላለጡበትን አዲስ መንገድ እንዲያውቁ በማለት ጸሎታቸውን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ አቅርበዋል።              

በሥራ እና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች ቤተሰብ ተለያይቶ የሚቆይ ከሆነ የቤተሰብ ሕይወት ትርጉም ሊዳከም፣ በመካከላቸው ሊኖር የሚገባ መዋደድ ሊቀዘቅዝ ይችላል። በተለይ ባል እና ሚስት ሳይራራቁ አብረው የመቆየት ልምድ በመካከላቸው ያለውን ፍቅር እና መተማመን ከጊዚው ወደ ከማሳደግ በተጨማሪ ለሌሎች የቤተሰብ አባላት ወይም ልጆቻቸው መልካም ምሳሌ እንዲያሆኑ ያደርጋቸዋል። ከወላጆቻቸው ጋር ሆነው የሚያድጉት ልጆች ከወላጆቻቸው ብዙ መልካም እሴቶችን እየተማሩ የማደግ ዕድል ይኖራቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን መልካም ሥነ ምግባርን፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶችን በማስተማር ወይም በማስተላለፍ ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ። ለመልካም አስተዳደግ የሚያግዝ ጥሩ ትምህርት ከወላጆቻቸው የቀሰሙ ልጆች ከሚያሳድጓቸው ወላጅ ቤተሰብ ተርፈው በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ አገልግሎቶች ውስጥ ተሰማርተው ለሚኖሩበት ማሕበርሰብ የሚያበረክቱት ውጤታማ ተግባር ብዙ ነው።

የቤተሰብ አባላት በሕብረት የሚሆኑበትን አጋጣሚ በሚያገኙበት ጊዜ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የደግነት፣ የፍቅር እና የርህራሄን ተግባር አንዱ ለሌላው በመግለጽ እውነተኛ የቤተሰብ አባልነትን ማረጋገጥ ይገባል። ልጆች ለወላጆቻቸው መታዘዝን የሚማሩበት፣ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መልካም ግንኙነትን በመፍጠር ጊዜያቸውን መልካም ተግባርን በማከናወን እንዲያሳልፉ፣ ከተላላፊው በሽታ ራሳቸውን መከላከል የሚችሉበትን መንገድ በመከተል ለጤናቸው ትኩረት እንዲሰጡ ማገዝ ያስፈልጋል። ለኮሮና ቫይረስ የተጋለጠ የቤተሰብ አባል በሚገኝበት ጊዜ በቤተሰብ መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ጭንቀት እና ውጥረት ለመቀነስ መሞከር፣ አንዱ ሌላውን በማጽናናት አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረግ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
21 March 2020, 17:11