ፈልግ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሳልቫ ኪር፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሳልቫ ኪር፣ 

የፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር የሰላም ሃሳብ በተቃዋሚዎቻቸው ውድቅ መደረጉ ተገለጸ።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት የሆኑት ክቡር አቶ ሳልቫ ኪር፣ በደቡብ ሱዳን የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረት ያቀረቡት ሃሳብ በተቃዋሚ የፖለቲካ ወገኖች በኩል ተቀባይነትን ሳያገኝ መቅረቱ ታውቋል። ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ደቡብ ሱዳንን በአሥር ክፍላተ ሃገራት በመከለል ወደ ፌዴሬሽን ሥርዓት እንዲመለሱ በማለት ያቀረቡትን ሃሳብ ዓማፅያኑ ቡድኖች ውድቅ ማድረጋቸው ታውቋል። የአማጽያኑ ተቃውሞ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር የካቲት 22/2012 ዓ. ም. ድረስ ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ለመመስረት የተገባውን የሰላም ስምምነት ቀነ-ገደብንም ውድቅ ማድረጉ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ የደረሰባትን ደቡብ ሱዳን፣ ከእርስ በእርስ ጦርነት በማውጣት ወደ ሰላም ጎዳና ለማሸጋገር ጥረቶች ሲደረጉ መቆየቱ ይታወቃል። ለስድስት ዓመታት ያህል በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ከ 380,000 ሰዎች በላይ መሞታቸው እና ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ መድረሱ ታውቋል። በስደት የሚኖሩ የቀድሞ የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚደንት ክቡር ሪክ ማቻርም በበኩላቸው በደቡብ ሱዳን የሦስት አስተዳደራርዊ ክልሎች፣ እነርሱም ሩዌንግ፣ ፒቦር እና አበይ ምሥረታን ተቃውመዋል። ከእነዚህ ሦስት አካባቢዎች መካከል፣ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል የምትገኝ እና በነዳጅ ዘይት ክምችት የምትታወቅ የሩዌንግ ክፍለ ሃገር በሁለቱም ጎሳዎች፣ ማለትም በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ጎሳ በሆነው በዲንቃ እና በሪክ ማቻር ጎሳ በሆነው በኑዌር ጎሳ መካከል ብዙ ሕይወት የጠፋበትን የእርስ በእርስ ጦርነት ሲያስነሳ መቆየቱ ታውቋል።

የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበር የሰላም ሽምግልና፣

የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና የፖለቲካ ተቃዋሚ እንቅስቃሴዎች በአገራቸው የተቀሰቀሰውን ጦርነት ለማስቆም በሚያስችል ስምምነት ላይ በመድረስ ጥር 4/2012 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው የሰላም ስምምነት ሰነድ በፊርማቸው ማረጋገጣቸው ይታወሳል። በስምምነቱ ላይ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታትን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት እና የአውሮፓ ህብረት መገኘቱ ይታወሳል። በደቡብ ሱዳን ለተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት ዋና ምክንያት በሆኑ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ የሚወያይ ስብሰባ በሚቀጥለው የጎርጎሮሳዊያኑ መጋቢት ወር በሮም ለማካሄድ ቀጠሮ መያዙ ታውቋል። የስብሰባው ዓላማ ከዚህ በፊት በተሰማሙበት የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊነት ላይ የሚነጋገር ሲሆን የስብሰባው ተሳታፊዎችም ከሁለቱ ወገኖች የተወጣጡ የጦር አበጋዞች መሆናቸው ታውቋል።      

የደቡብ ሱዳን የሐይማኖት አባቶች እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት በጋራ ከሚያዚያ 2-3/2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን የሁለት ቀን ሱባኤ ማድረጋቸው ይታወሳል። በዚህ ሱባኤ ማጠቃለያ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባሰሙት የመዝጊያ ንግግር እንደገለጹት “ሰላም፣ ብርሃን እና ተስፋ ደቡብ ሱዳን ውስጥ እውን ሊሆኑ ይችላሉ” በማለት አስተንትኖዋቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በወቅቱ በዚያው የተገኙ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በአገሪቷ ሰላምን ለማውረድ ቁርጠኛ ሆነው እንዲሠሩ በማለት በእግር ሥር ወድቀው ጫማዎቻቸውን በመሳም መማጸናቸው ይታወሳል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
17 February 2020, 15:28