ፈልግ

የሜክሲኮ ስደተኛ ወላጅ ቤተሰብ ከልጆቻቸው ጋር ሲገናኝ፣ የሜክሲኮ ስደተኛ ወላጅ ቤተሰብ ከልጆቻቸው ጋር ሲገናኝ፣ 

“ወላጆች ልጆቻቸውን ማዳመጥ ያስፈልጋል”

ክቡራት እና ክቡራን የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎቻችን በዚህ ሳምንታዊው “የቤተሰባችን” ዝግጅት በኩል ቤተሰብን ከሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ውስጥ በመምረጥ ይጠቅማሉ ያልናቸውን ትምህርቶችን እና አስተያየቶች  ስናቀርብላችሁ ቆይተናል። በዚህ ርዕሳችንም ወልጆች ለልጆቻቸውን ሃሳብ ኣና ንግግር ትኩረትን በመስጠት ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ የሚገልጽ ጽሑፍ እናቀብላችኋለን።

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን ነኝ።

ወላጆች ለልጆቻቸው ተገቢውን እንክብካቤ እና የቅርብ ክትትል በማድረግ መልካም አስተዳደግ እንዲኖራቸው  ማድረግ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት ሰላማዊ እና አስደሳች እንዲሆን ያደርጋል። በእርግጥ በልጆች መልካም አስተዳደግ የወላጆች ሃላፊነት ከፍተኛ ቢሆንም ከወላጅ ቤተሰብ ጎን ለጎን፣ የትምህርት ተቋማት፣ ሐይማኖታዊ ተቋማት እና መላው ማሕበረሰብ የበኩሉ ተጨማሪ ድርሻ አለው። እውቀትን፣ መልካም ስነ ምግባርን እና መልካም የባሕል እሴቶችን ለወጣቶች እና ለአዳጊ ልጆች ማስተላለፍ፣ የእያንዳንዱ ማህበራዊ ተቋን ሃላፊነት ነው። ለመልካም አስተዳደግ የሚያግዝ ጥሩ ትምህርት እና ስነ ምግባር ከወላጆቻቸው ያገኙ ልጆች ለሚያሳድጓቸው ወላጅ ቤተሰብ፣ ለሚኖሩበት ማሕበርሰብ እና ለራሳቸው ጥሩ ህይወትን ያዘጋጃሉ።

በመልካም ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ቤተሰብ አባል መሆን ያስደስታል። በቤተሰብ መካከል የእርስ በእርስ መደማመጥ ካለ፣ ቤተሰብን ሊያጋጥም የሚችል ችግር በጋራ መወጣት ከተቻለ፣ በእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ውስጥ መተማመንን በማምጣት ውስጣዊ ሰላምን ይፈጥራል። በቤተስብ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ሌሎች በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን ሊያስገኝ ይችላል። በቤተስብ መካከል መልካም ግንኙነት ሲኖር ልጆች በራስ የመተማመን ስሜታቸው ከፍተኛ ከመሆኑ በላይ አእምሮአቸው መልካም አስተሳሰብ እንዲኖር ያደርጋል። ወላጆች በልጆቻቸው በኩል የሚነሱ የአመጋገብ፣ የዕረፍት እና የባሕርይ ለውጥ ችግሮችን ቶሎ ብለው ለማቃለል ዕድልን ያገኛሉ። በመልካም ግንኙነት ውስጥ በሚገኝ ቤተሰብ ውስጥ መደማመጥ እና አንዱ ሌላውን በቀላሉ የመረዳት አቅም ስለሚኖር ግጭት ወይም አለመግባባት ሲፈጠር በቀላሉ ለመፍታት ያስችላል። በመልካም ግንኙነት ውስጥ ያለ ቤተሰብ፣ በመካከሉ ያለውን የሃሳብ ልዩነት በክብር ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ ትዕግስት ይኖረዋል። በመልካም ግንኙነት ውስጥ የሚገኝ ቤተሰብ አባላት፣ ከቤተሰብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራስ ጋርም መልካም እንዲኖር የማድረግ ችሎታ ይኖራቸዋል።     

በበርካታ በማደግ ላይ ባሉት አገሮች የሚገኙ ወላጆች፣ የልጆቻቸውን ሃሳብ፣ ስሜት እና ፍላጎት፣ ጊዜን እና ዕድልን ሰጥተው ለማዳመጥ ያላቸው ፍላጎት አነስተኛ ነው። በዚህ የተነሳ በርካታ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያላቸው እምነት እና ፍቅር እየቀነሰ ይሄዳል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ልጆች ለወላጆቻቸው የሚያሳዩት የታዛዥነት እና የትህትና ፍላጎት ከሌሎች ያልተስተካከሉ ስነ ምግባሮች ጋር በመደመር በመካከላቸው ያለውን  ግንኙነት ሊያበላሽ ይችላል። ወላጆች ልጆቻቸው ለሚያቀርቡት ጥያቄዎች በቂ መልስ መስጠት ባይችሉም፣ ስሜታቸውንም በሚገባ ለመረዳት ቢቸገሩም ፣ ጊዜን እና ዕድልን ሰጥተው ማዳመጥ መልካም ይሆናል። ወላጅ ቤተሰብ ከሚታወቅበት መልካም ስነ ምግባራት መካከል አንዱ የልጆቻቸውን ሃሳብ እና ንግግር ጊዜን በመስጠት ማዳመጥ ነው። ልጆች በወላጆቻቸው ዘንድ ተደማጭነት እንዳላቸው በሚገባ ካወቁ ልባቸውን ይበልጥ ለወላጆቻቸው ክፍት ሊያደርጉ ይችላሉ። ለሕይወታቸውም ጠንካራ መሠረት የሚሆን ምክር እና እውቀት ከወላጆቻቸው ሊያገኙ ይችላሉ።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ክርስቶስ ሕያው ነው” በሚል አርዕስት፣ መጋቢት 16/2011 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው በኩል ለዓለም ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ወጣቶች ጠንካራ መሠረት ያለው ሕይወት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል ማለታቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በማከልም የወጣቶች ሕይወት ሥር እንደሌለው ዛፍ መሆን የለበትም። አንዳንድ ዛፎች በረጅሙ ያድጋሉ። አረንጓዴ እና የሚያማምሩ፣ መልካም መዓዛ ያላቸው አበባዎችን ያብባሉ። አንዳንድ ጊዜ ጥላ ሆነው ወደ ግንዳቸው ለሚጠጉት ጥሩ የጸሐይ መከላከያ ሆነው ያገለግላሉ። የአስተዳደጋቸውን ሁኔታ በሚገባ ላልተረዳ ሰው በእርግጥ ጥሩ ዛፍ መስለው ይታያሉ።

ነገር ግን ሃይለኛ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ ከውድቀት ለመዳን የሚግዛቸው፣ ወደ መሬት ውስጥ ጠለቅ ብሎ የገባ ሥር ካለመኖራቸው የተነሳ በቀላሉ ይወድቃሉ። የአንዳንድ ወጣቶች ሕይወት ይህን ይመስላል። ወጣቶች ለወደፊት ሕይወታቸው ተስፋ እና መመኪያ የሚሆን ነገር ሳይጨብጡ አድገው በማይበት ጊዜ ያሳዝነኛል። ወጣቶች እውቀት እንዲኖራቸው ያስፈልጋቸዋል፣ ወጣቶች ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ወጣቶች መልካም ስነ ምግባር እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ወጣቶች ጤናማ አእምሮ እና የአካል ብቃት ሊኖራቸው ይገባል። በአጠቃላይ ወጣቶች በማንነታቸው የሚመኩበት ነገር ሊኖራቸው ያስፈልጋል ብለዋል።

ወላጆች ልጆቻቸውን በሚገባ ማዳመጥ ቤት ውስጥ እና ከቤት ውጭ እየሆነ ላለው ነገር በቂ መረጃ እንዲኖር ያግዛል። ወላጆች ልጆቻቸውን ማዳመጥ በመካከክላቸው መከባረር እንዲኖር ያግዛል። የወላጆች እና የልጆች እርስ በእርስ መደማመጥ የችግሮች ማቃለያ የመጀመሪያ ደረጃ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን በሚገባ የሚያዳምጡ ከሆነ፣ እንዴት ማሳደግ እንደሚችሉ ያውቃሉ። ወላጆች ልጆቻቸው እንዲያዳምጧቸው የሚፈልጉ ከሆነ፣ አስቀድመው እነርሱ ያዳምጧቸው። በወላጆች ዘንድ ተደማጭነትን ያገኘ ልጅ ሌሎችን ማዳመጥ ይማራል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
29 February 2020, 16:22