የሮም ከተማ ምዕመናን በሕመም የሚሰቃዩትን በጸሎት አስታወሱ።
የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ እና በሀገረ ስብከቱ የጤና እንክብካቤ ሐዋርያዊ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ተወካይ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ሪካርዲ፣ ምዕመናኑ በሕመም ስቃይ ውስጥ የሚገኙትን በጸሎታቸው እንዲያስታውሱ አደራ ብለው ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ወርሃዊ የጸሎት ሥነ ሥርዓት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ሪካርዲ በንግግራቸው እንዳስታወቁት በሕመም ከሚሰቃዩት ጎን መሆን ማለት በቃል ወይም በስነ ልቦና ሳይሆን በየትም ቦታ ሆነው በጸሎት ማስታወስን እና ማሰላሰልን ይመለከታል ብለዋል። ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ በመሆኑ እኛም ልንከተለው ይገባል በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ የካቲት 3/2012 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለውን 28ኛ ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን እና የሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ከቅዱስ ወንጌል ክፍል “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ” (ማቴ. 11፡28) መጥቀሳቸው ገልጸዋል።
በስውር የሚሰቃዩ ሕሙማን ብዙ ናቸው፣
በሮም ከተማ ውስጥ በስውር የሚሰቃዩ በርካታ ሕሙማን መኖራቸውን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ሪካርዲ፣ እነዚህ ሕሙማን አስተዋሽን አጥተው በየቤታቸው ውስጥ በስቃይ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰው፣ የከተማው ቁምስናዎች በመተባበር ለሕሙማን አዲስ የእንክብካቤ አገልግሎት እና ድጋፍ እንዲያደርጉ በማለት ሀገረ ስብከቱ ጥሪ የሚያቀርብ መሆኑን ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ሪካርዲ በማከልም ከዚህ ወር ጀምሮ በየወሩ 3ኛ ቀን በሮም ከተማ በሚገኙ ቁምስናዎች ለሕሙማን የጸሎት ሥነ ሥርዓት የሚፈጸም መሆኑን ገልጸው በጸሎት ሥነ ሥርዓቱም ሕሙማን በአካል የሚገኙ መሆናቸውን አስረድተው ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ሰብዓዊ ዕርዳታንም ለማድረግ መታሰቡን ገልጸዋል። ይህም ሕሙማንን በልባችን ማስታወስ ብቻ ሳይሆን፣ ምንም እንኳን በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም ማሕበራዊም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወትን ከተቀረው ማሕበረሰብ ጋር በንቃት መሳተፍ የሚችሉ መሆናቸው አስረድተዋል። በሮም ከተማ በሚገኙ ቁምስናዎች ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለሕሙማን በሚደረግ ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ ያላቸውን የሕይወት ምስክርነት የሰጡ በርካታ ሰዎች መኖራቸው ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ሪካርዲ ጠቅሰዋል። የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ሪካርዲ፣ ምዕመናን በዚህ ከመጨነቅ ይልቅ በማሕበረሰብ መካከል እየተስፋፋ ለመጣው የማግለል ባሕርይ መጨነቅ ያስፈልጋል ብለዋል። ብዙን ጊዜ ሕሙማንን ለመፈወስ ከማሰብ ይልቅ የበሽታውን ዓይነት ለማወቅ ብዙ ምርምር እና ጥናት ይደረጋል ያሉት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ሪካርዲ፣ አንድ ሰው በሕመም፣ በእርጅና፣ ወይም ስደተኛ በመሆኑ ምክንያት ለማሕበርሰቡ ምንም ጥቅም እንደማይሰጡ ይታሰባል ብለው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው እያንዳንዱ ነፍስ የእግዚአብሔር ፍጥረት በመሆኑ ወደዚህ ዓለም ከመጣበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ አስፈላጊው እንክብካቤ፣ ክብር እና ጥበቃ ሊደረግለት ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውሰዋል።
የሮም ሀገረ ስብከት ምዕመናን የሚያደርጉት የመንፈሳዊ ንግደት ጉዞ፣
በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ ወደሚገኝ የመለኮታዊ ፍቅር ወይም “ዲቪን አሞሬ” ቤተክርስቲያን ቀጣይነት ያለው ዓመታዊ መንፈሳዊ ጉዞን ለማድረግ ዕቅድ መውጣቱን ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ሪካርዲ አስታውቀዋል። በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ታስቦ የሚውለውን የሕሙማን ቀን በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ስም ለማድረግ መታቀዱን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ሪካርዲ፣ ዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀንን፣ “የስቃይ ፈውስ” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ይፋ በማድረግ ያስጀመሩትም ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በዚህ ቃለ ምዕዳናቸው፣ በሰዎች ላይ የሚደርስ ስቃይ ከቅዱስ ወንጌል ምስክርነት አንዱ እና ከፍተኛው ነው ማለታቸውን አስታውሰዋል።
በሮም ከተማ የአዕምሮ ሕሙማን ቁጥር እያደገ መምጣቱ ከቤተክርስቲያን ተግዳሮቶች አንዱ ነው፣
በሮም ከተማ ውስጥ የአዕምሮ ሕሙማን ቁጥር እያደገ መምጣቱን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ሪካርዲ፣ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ በሮም ከተማ ከሚገኙ ሕሙማን መካከል ከግማሽ በላይ በአእምሮ ሕመም እንደሚጠቁ ገልጸው ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህም እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ቤተክርስቲያን ከምን ጊዜም በበለጠ ለእነዚህ የማኅበረሰብ ክፍል በቂ ሐዋርያዊ አገልግሎትን ለማበርከት የሚያስችላትን ዝግጅት ማድረግ ይገባል ብለዋል። የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ እና በሀገረ ስብከቱ የጤና እንክብካቤ ሐዋርያዊ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ተወካይ በንግግራቸው ማጠቃለያ፣ ስለ ሕሙማን ሲነገር መስማት ወይም በአደባባይ ላይ አይቶ ማለፍ ሳይሆን ወደ የመኖሪያቸው ሄደው መጎብኘት እንደሚያስፈልግ፣ ማንኛውንም ዓይነት ዕርዳታ ሲለምኑ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ እንጂ ፊት መንሳት እንደማያስፈልግ አደራ ብለዋል።