ፈልግ

ወጣት ጥንዶች በቫቲካን በር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ መሪነት ምስጢረ ተክሊል ሲፈጽሙ ወጣት ጥንዶች በቫቲካን በር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ መሪነት ምስጢረ ተክሊል ሲፈጽሙ  

የወጣቶች ቅድመ ጋብቻ ዝግጅት መስፈርቶች

ክፍል  ሁለት

የወጣቶችን ቅድመ ጋብቻ ዝግጅት አስመልክቶ እንደ መስፈርት ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ ጥቂት ነጥቦችን ከዚህ በታች እናያለን፡፡

ለአካለ መጠን መድረስ

የዕድሜ መጨመር በሰውነት ላይ የሚያመጣቸው ለውጦች አሉ፡፡ ዕድገት ከእናት ማኅጸን ጀምሮ ይካሄዳል፡፡በተለይ የአካል ዕድገት በልጅነት ወቅት ከነበረው ሁኔታ ይልቅ በወጣትነት ጊዜ የተለየ ገጽታ ይኖረዋል፡፡ይህም ሲባል የአካል ዕድገት በወጣትነት ጊዜ ወደ ሙላት ይደርሳል ማለት ነው፡፡ከዚህ ዕድገት ጋር ተያይዞ የተቃራኒ ጾታ ፍላጎትም ይጀምራል፡፡ወንድና ሴት ለፍቅር ግንኙነት ይፈላለጋሉ፡፡ይህ ማለት በተፈጥሮ በሰውነታቸው ውስጥ የተቀመጠው እምቅ የተቃራኒ ጾታ ፍላጎት ጊዜውን ጠብቆ ብቅ ይላል ማለት ነው፡፡ፍላጎቱ በራሱ ጤናማ ነው፡፡

አዘጋጅ እና አቅራቢ አሸናፊ ደበላ-ቫቲካን

የፍቅር ፍላጎት መምጣትና የአካል ዕድገት መኖር ግን ለብቻው ለጋብቻ ዝግጁ መሆንን አያመለክትም፡፡ ቢያንስ ዕድሜያቸው 18ና ከዚያ በላይ መሆን አለበት፡፡ምክንያቱም ከዚህ ዕድሜ በፊት የሚመሠረት ጋብቻ በሕግ ፊትም ተቀባይነት የለውም፡፡

 

የኢኮኖሚ አቅም መኖር

ጋብቻ በአካል ብቻ ሳይሆን በአእምሮ፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚና በሌሎችም የሕይወት ዘርፎች የበሰሉና ኃላፊነት የሚወስዱ ወንድና ሴት የሚጣመሩበት ኅብረት ነው፡፡በዚህ ዕድሜ አካባቢ ታዳጊ ወጣቶች በአካላቸው ተፈጥሯዊ የሆነውን የፆታ ፍላጎታቸውን ለመፈጸምና ለማርካት ደርሰዋል እንጂ በሌሎች የሕይወት ገጽታዎች ገና መብሰል ይቀራቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱን የኢኮኖሚ ብስለትን እንውሰድ፡፡ የ 18 ዓመት ዕድሜ አካባቢ ታዳጊ ወጣቶች በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በኢኮኖሚ በወላጆቻቸው ላይ ጥገኞች ናቸው፡፡ ከዚያም ኮሌጅ ገብተው ለመማር ከ3-7 ዓመት ሊፈጅባቸው ይችላል፡፡ የኮሌጅ ትምህርት ካገኙና ሥራ ከያዙ የራሳቸውን የገቢ ምንጭ ያገኛሉ፡፡አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሁለቱም የገቢ ምንጭ ካላቸው ወይም የአንዱ የገቢ ምንጭ ሁለቱን ማኖር የሚያስችል ከሆነ ማግባት ይችላሉ፡፡

በኢኮኖሚ ራስን መቻል የሚለው ሐሳብ በእርግጥ አንጻራዊ ነው፡፡በጋብቻ ሊጣመሩ ያሰቡ ወንድና ሴት ለመሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው የሚሆኑ ነገሮችን ማግኘት የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆን ለጋብቻ ጅማሬ በቂ ነው፡፡ጋብቻ ሃብታም በመሆን የሚጀመር ሳይሆን በዝቅተኛ ገቢ ላይ ተጀምሮ ሃብቱ ቀስ በቀስ በሁለቱ ጥረት ሊመጣ የሚችል ነው፡፡

የአዕምሮ ብስለትና የማኅበራዊ ግንኙነት ክህሎት

ለጋብቻ ግንኙነት ዘላቂነት አስተዋጽዖ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል አንዱ የጥንዶቹ (ወንድና ሴት) የአእምሮ ብስለትና የማኅበራዊ ግንኙነት ክህሎት መኖር ነው፡፡ይህ ዓይነቱ ብስለት ደግሞ ዕድሜ በመቁጠር ብቻ ላይመጣ ይችላል፡፡ ሆኖም ዕድሜ ራሱ ትምህርት ቤት በመሆኑ (የተለያዩ ነገሮችን ከውጣ ውረድ ለመቅሰም ዕድል ስለሚሰጥ) የዕድሜ መጨመር፣ የአእምሮ ብስለትና የማኅበራዊ ግንኙነት ክህሎትን ለማዳበር መልካም አጋጣሚዎች ይኖራሉ፡፡

በለጋ ዕድሜ ከማግባት በሃያዎቹ አጋማሽ አካባቢ ማግባት፣ የጋብቻ ግንኙነትን ለማጣጣምና ግንኙነቱን ዘላቂ ለማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ብቁ ያደርጋል፡፡

ልጅ ለመውለድና ለማሳደግ

ከአካል ዕድገት አንጻር ወንድና ሴት ከጉርምስና ዕድሜ ጀምረው ልጅ መውለድ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ከአካል ዝግጅት፣ ከጤንነት፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሌሎች ምክንያቶች አንጻር በተለይ ለሴቶች ጥሩ ልጅ የመውለጃ ዕድሜ ከ18 እስከ 35 ዓመት መሃል ያለው ጊዜ ነው፡፡

እንግዲህ ከላይ በተጠቀሱ ነጥቦች ስር ወጣት ወንዶችና ሴቶች በአብዛኛው እስከ 20ዎቹ አጋማሽ አካባቢ በትምህርት ላይ ይሆናሉ፡፡ ራሳቸውን ችለው ቤተሰብ ለመመስረት ሁለንተናዊ ብቃት የሚኖራቸው በዚህ ወቅት ነው፡፡

ልጅ ከመውለድ አንጻር ከዝቅተኛ ተገቢ ዕድሜ 18 መጀመር ቢመረጥም የሁኔታዎች አለመመቻቸት ስለሚኖር በዚህ ጊዜ ማድረጉ ብዙ ተግዳሮቶች አሉት፡፡ ራስን የመቻል አቅም ከመጣ በኋላም ደግሞ ወደ ከፍተኛ ጫፍ (35 አመት) ከፍ ማድረጉ አይመረጥም፡፡ልጅ መውለድ ብቻ ሳይሆን የማሳደግም ኃላፊነት ስለሚኖር ተጋቢዎቹ በለጋ የጎልማሳነት ዕድሜያቸው ልጆቹን ለማሳደግ የአካል፣ ስሜትና ስነ-ልቦናዊ ዝግጁነት ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ አግብቶ ልጅ መውለድ የሚፈልጉ ወጣቶች ይህን ነጥብ ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይረዳቸዋል፡፡

በተገቢ ዕድሜ የማግባት ጥቅሞች

  •  በሃያዎቹ አጋማሽ አካባቢ የሚያገቡ ወንዶችና ሴቶች በጋብቻ ሕይወታቸው ከሌሎቹ ይልቅ ደስተኞች ይሆናሉ፡፡
  •  በወጣትነት ዕድሜያቸው የሚያገቡ ጥንዶች ከማያገቡት ይልቅ ሃብት የማፍራት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ገቢና ሃብታቸውም እየጨመረ ይሄዳል፡፡
  • ለጤንነት አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች የመጋለጥ ዕድል ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ በወጣትነታቸው ወቅት ያገቡ ወንዶችና ሴቶች ጤንነታቸውን ጠብቀው የመኖር መልካም አጋጣሚዎችን ያገኛሉ፡፡
  • በወጣትነት (20ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ማለት ነው) የሚያገቡ ጥንዶች ተፈጥሯዊ የሆነውን የፆታ ፍላጎታቸውን ማርካት ይችላሉ።  መልካም የወሲብ ሕይወት ይኖራቸዋል፡፡ ዕድሜ ሲጨምር የሰውነት ኃይልም እየቀነሰ ስለሚሄድ እንደ ትኩስ የወጣትነት ጊዜ ይህንን የመለማመድ ዕድሉ ይቀንሳል፡፡
  • ጥንዶቹ በተለያዩ የሕይወት ውጣ ውረዶች (ለምሳሌ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ባለው የግንኙነት መፍረስ) ሕይወታቸው ሳይቆስል ወደ ጋብቻ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ ከሌሎች ግንኙነቶች ወደ ጋብቻ ይዘው የሚመጡት ‹‹ችግር›› ላይኖር ይችላል፡፡
  • አንዱ ሌላውን የመቅረጽ ዕድሉ ይሰፋል፡፡ በዚህ የወጣትነት ጊዜ ሁለቱም ተሰርተው ስላላለቁ፣ ይቀራረጻሉ፣ በረጅም ርቀት መልካም ጓደኛሞች ይሆናሉ፡፡
  • ጤናማ ልጆችን በጊዜ ወልዶ በጊዜ ለማሳደግ መልካም ዕድል ይፈጥራል፡፡ ዕድሜ ከገፋ በኋላ ልጆችን መውለድ የሚቻል ቢሆንም ወላጆች ልጆቹን ለማሳደግ የሚኖራቸው ጉልበት ይቀንሳል፡፡ በወላጆችና በልጆች መካከል የዕድሜ መራራቅም የትውልድ ክፍተትን በጣም ይፈጥራል፡፡
24 January 2020, 16:03