ፈልግ

በምዕራብ አፍሪካ አገሮች በሚቀሰቀስ አመጽ ምክንያት ሕጻናት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው፣ በምዕራብ አፍሪካ አገሮች በሚቀሰቀስ አመጽ ምክንያት ሕጻናት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው፣ 

በሦስት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ውስጥ አምስት ሚሊዮን ሕጻናት ዕርዳታን ይሻሉ።

በምዕራብ አፍሪካ፣ ሰሃል አገሮች መካከል በሦስቱ፥ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር የሚገኙ ወደ አምስት ሚሊዮች የሚጠጉ ሕጻናት ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት አስታወቀ። በቡርኪና ፋሶ፣ በማሊ እና በኒጀር ውስጥ የሚቀሰቀሱ አመጾችን ተከትሎ ጥቃት የሚደርስባቸው ሕጻናት ቁጥር ሊያድግ እንደሚችል የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. በአንዳንድ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች በተቀሰቀሰው አመጽ፣ ደህንነታቸው ያሰጋቸው ከ670,000 ሕጻናት በላይ የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ መገደዳቸውን ድርጅቱ አስታዉቋል። በማሊ ውስጥ ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. በ571 ሕጻናት ላይ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸሙን፣ በ2018 ዓ. ም. በ544 ሕጻናት ላይ፣ በ2017 ዓ. ም. በ386 ሕጻናት ላይ ጥቃት መድረሱን የድርጅቱ ሪፖርት አስታውቋል። የድርጅቱ ሪፖርት በማከልም በምዕራብ አፍሪካ የሰሃል አገሮች በሚባሉ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር፣ ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. በተቀሰቀሱት አመጾች፣ ከ3,300 በላይ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን፣ ይህም ከ2017 ዓ. ም. ከተመዘገበው ስድስት እጅ በልጦ መገኘቱን፣ በ650,000 ሕጻናት እና በ16,000 መምህራን ላይ ጉዳት ማስከተሉን የድርጅቱ ሪፖርት አመልክቷል። የድርጅቱ ሪፖርት እንዳስታወቀው በያዝነው የጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ዓ. ም. በመካከለኛው የሰሃል አገሮች ውስጥ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆናቸው፣ ከ709,000 በላይ ሕጻናት ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚጋለጡ መሆናቸውን ገልጾ፣ ለእነዚህ ሕጻናት አስቸኳይ የነፍስ አድን እርዳታ ያስፈልጋቸዋል በማለት ጥሪውን አቅርቧል።

በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ተወካይ የሆኑት ወይዘሮ ማሪ ፔር ፖይሬር እንዳስታወቁት በመካከለኛው የሰሃል አገሮች ውስጥ በሕጻናት ላይ በሚፈጸም በደል እና ስቃይ ምክንያት ሕጻናት እጅግ በሚያሳዝን ሕይወት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል። በመካከለኛው የሰሃል አገሮች ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት የሚገደሉ፣ የሚታረዱ እና የሚደፈሩ መሆናቸውን ወይዘሮ ማሪ ፔር ፖይሬር አስታውቀው በእነዚህ አገሮች ውስጥ ለሚኖሩ ሕጻናት አስቸኳይ የሕይወት ደህንነት አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ተናግረዋል። በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” ይፋ ባደረገው መልዕክቱ መንግሥታት፣ የመንግሥት ወታደራዊ ሃይሎች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ታጣቂ ቡድኖች እና ሌሎች በግጭት ውስጥ የሚገኙ አካላት በመኖሪያ ቤታቸው፣ በትምህርት ቤት እና በሕክምና ማዕከላት በሚገኙ ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እንዲያቆሙ በማለት አሳስቧል። የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ በማከልም መንግሥታትን ጨምሮ የሕጻናት ሕይወት የሚያሳስባቸው ወገኖች በሙሉ ለሕጻናት አስፈላጊውን ጥበቃ እዲያደርጉላቸው፣ ማሕበራዊ አገልግሎትን ማዳረስ የሚቻልባቸውን መንገዶች እንዲያመቻቹላቸው ጠይቆ፣ ማህበራዊ ትብብር ግጭትን ለመከላከል የሚረዳ መሆኑን አስረድቷል።  

በሰሃል አገሮች ውስጥ በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት የሚከሰት መፈናቀል እና የሕይወት ድህንነት መጓደል፣ ለሕጻናት እና ለቤተሰቦች የሚደረግ የተመጣጣኝ ምግብ እና የሕክምና እርዳታ ማዳረስ አገልግሎት በወጉ እንዳይደርሳቸው ትልቅ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ድርጅቱ አክሎ አስታውቋል። ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትም እየቀነሰ መምጣቱን የገለጸው የሕጻናት መርጃ ድርጅቱ፣ ከሕዝቦቿ መካከል አምስት ከመቶ የሚሆኑ ከመደበኛ መኖሪያቸው ተፈናቅለው በሚገኙባት በቡርኪና ፋሶ፣ ካለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. እስከ 2019 ዓ. ም. ድረስ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አሥር ከመቶ መቀነሱን አስታውቆ በአንዳንድ አካባቢዎችም እስከ አርባ ከመቶ የሚሆኑ ነዋሪዎቿ ንጹሕ የመጠጥ ዉሃ አቅርቦት የሌላቸው መሆኑን አስረድቷል።

በተበባሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “ዩኒሴፍ” በሰሀል የአፍሪካ አገሮች በሆኑት ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር ውስጥ ከሌሎች መሰል የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በእነዚህ አገሮች ውስጥ ለሚኖሩ ሕጻናት አስቸኳይ የትምህርት፣ የሕክምና፣ የተመጣጣኝ ምግብ፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እና ጥራቱን የጠበቀ የመጸዳጃ አገልግሎቶችን ለቅረብ የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቆ፣ አመጾች የሚከሰቱባቸውን ሦስቱ አገሮችን፣ ቡርኪና ፋሶን፣ ማሊን እና ኒጀርን ለመደገፍ 208 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልገው መሆኑን አስታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
28 January 2020, 17:05